
አዲስ አበባ :- የመሬት ዘርፉን እና በዘርፉ የሚስተዋሉ ብልሹ አሠራሮችን የሚያስቀር ሥርዓት እያበለጸገ መሆኑን የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የመሬት ይዞታ ምዝገባና መረጃ ኤጀንሲ ገለጸ።
በኤጀንሲው የተቀናጀ የመሬት ነክ መረጃ ማልማት፣ ማደራጀትና ማስተዳደር ዳይሬክተር ኤልያስ ኢብራሂም ለአዲስ ዘመን እንደገለጹት፤ የመሬት ዘረፋን ጨምሮ በዘርፉ የሚስተዋሉ ሌብነት እና ብልሹ አሠራርን ማስቀረት የሚያስችል ሥርዓቶች እያበለጸገ ነው።
ሲስተሙ ተጠናቅቆ ወደ ሥራ ሲገባ፣ ባለይዞታዎች ይዞታቸውን በሚመለከት በማንኛውም ጊዜ የትኛውንም ዓይነት መረጃ ቤታቸው ሆነው ማግኘት እንደሚችሉ አስታውቀዋል። ባለይዞታዎች መረጃ በቀላሉ ማግኘት የሚችሉበትን ሥርዓት መፍጠር ከተቻለ፤ ዘርፉ ለሌብነትና ብልሹ አሠራር ያለውን ተጋላጭነት ማስቀረት እንደሚችልም አመልክተዋል።
የሲስተሙ መበልጸግና ተግባራዊ መደረግ ብልሹ አሠራርን ይቀርፋል፤ የመሬት ወረራን ያስወግዳል። ወደ ፍርድ ቤት የሚሄዱ ብዙ የድንበር ይገባኛል ክርክሮችንም በማስቀረት የፍርድ ቤት ጫናንም ይቀንሳል ብለዋል።
ኤጀንሲው እያበለጸገ የሚገኘው ሲስተም የመሬት ስፋቱ ፣ ባለይዞታው በሕግ የተሰጠው መብት፣ ክልከላ እና ኃላፊነትን የሚያመላክት ፣ ከመንገድ፣ ከግንባታ ፍቃድ አንጻር፣ አካባቢው ላይ እንዲለማ የሚፈልገውን እና የሚከለከለውን ያካተተ መሆኑንም ጠቁመዋል።
ኅብረተሰቡ በእዚህ ደረጃ በቂ መረጃ ካገኘ ከማንም ጋር ድርድር ውስጥ የመግባት አጋጣሚ አይፈጠርም፤ ብልሹ አሠራርና ሌብነት አይኖርም፤ ባለጉዳዩ አገልግሎት ለማግኘት ማሟላት የሚገባው መስፈርት ምን እንደሆነ ማወቅ ከቻለ ለሌሎች ድርድሮች በር አይከፍትም ብለዋል።
የሲስተሙ መበልጸግ እንደ ሀገር በከተማው በመሬት ጉዳይ ለሚወሰኑ ማናቸውም ውሳኔዎች ትልቅ ግብአት እንደሚሆን አመልክተው፤ ኤጀንሲው የመሬት ነክ መረጃ ብቻ ሳይሆን የማህበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ መረጃዎችን ከኅብረተሰቡ እና ከሚመለከታቸው ተቋማት በመሄድ ይሰበስባል። እነዚህንም ከመሬት ጋር በማስተሳሰር ለውሳኔ ሰጪ አካላት ጭምር ያቀርባል ብለዋል።
ካዳስተር ሲረጋገጥና ምዝገባ ሲከናወም አጎራባቾችን በማስማማት እና በማግባባት ይከናወናል። አጎራባቾች ባይስማሙ መፍትሔ እንዲያገኙ ወደ መብት ፈጣሪ ይላካሉ። ተረጋግጦ የሚመዘገበው ተግባቦት ስለሆነ የፍርድ ቤቶችን አላስፈላጊ ጫና እንዲሁም የደንበኞችን አላስፈላጊ እንግልትን እንደሚያስቀር አስታውቀዋል ።
ብዙ ነገሮች በጅምር ደረጃ ላይ እንደሚገኙ ያመለከቱት፤ እንደተቋም መረጃ የማሰባሰብ ሥራ እየተሠራና ከተለያዩ ተቋማት መረጃ እየተሰባሰበ እንደሚገኝ አመልክተዋል። ከስፔስ ሳይንስ፣ ከጂኦ ስፓሽያል፣ ከፕላን እና ልማት ቢሮ፣ ከመሬት ይዞታ ልማት ቢሮ፣ ከውሃ ልማት፣ ከመንገዶች መረጃዎችን የማሰባሰብ ሥራ በመሠራት ላይ እንደሆነ አስታውቀዋል። በአብዛኛው እየተሠራበት የነበረው መሬት ነክ መረጃዎች ላይ እንደነበር አመልክተው፤ በቀጣይ ደግሞ የማህበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ መረጃዎች ላይ በስፋት እንደሚሠራ አስታውቀዋል።
በዘላለም ግዛው
አዲስ ዘመን ማክሰኞ ሰኔ 24 ቀን 2017 ዓ.ም