ከ20 ቢሊዮን ብር በላይ ተመላሽ እንዲሆን ቢጠየቅም የተመለሰው 2 ነጥብ 9 ቢሊዮን ብቻ ነው

አዲስ አበባ፡- በኦዲት ግኝት ወደ መንግሥት ካዝና እንዲመለስ አስተያየት ከተሰጠበት 20 ነጥብ 4 ቢሊዮን ውስጥ ተመላሽ የተደረገው 2 ቢሊዮን 914 ሚሊዮን 760 ሺህ 469 ብር (14 ነጥብ 2 በመቶ ) ብቻ መሆኑን ዋና ኦዲተር ገለጸ፡፡

በፌዴራል ዋና ኦዲተር መሥሪያ ቤት ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የፌዴራል መንግሥት መሥሪያ ቤቶች የ2016 በጀት ዓመት የሂሳብ የፋይናንሺያል የሕጋዊነት እና የክዋኔ ኦዲት ሪፖርት አቅርቧል፡፡

ዋና ኦዲተር መሠረት ዳምጤ ለምክር ቤቱ ባቀረቡት ሪፖርት፤ በ2015 በጀት ዓመት እና ከዚያ በፊት በተከናወኑ የኦዲት ሪፖርቶች መሠረት ርምጃ የተወሰደ መሆኑን ለማጣራት ኦዲት ሲደረግ በጠቅላላ እንዲመለስ አስተያየት ከተሰጠበት ብር 20 ቢሊዮን 488 ሚሊዮን 520 ሺህ ውስጥ 2 ነጥብ 9 (14 ነጥብ 2 በመቶ) ብቻ ተመላሽ መደረጉን ተናግረዋል፡፡

በሌላ በኩልም በኦዲት ግኝቱ 23ሺህ 230 ዩኤስ ዶላር እንዲመለስ አስተያየት ቢሰጥበትም ተመላሽ የሆነው 30 ዩኤስ ዶላር ብቻ መሆኑን ገልጸዋል

በግኝቱ ላይ በተሰጠው አስተያየት መሠረት ርምጃ ከወሰዱት መካከል አምስት የገቢዎች ሚኒስቴር ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤቶች ብር 1 ቢሊዮን 682 ሚሊዮን 985ሺህ 836 ፤ በጉምሩክ ኮሚሽን በ4 ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤቶች ብር 655 ሚሊዮን 291ሺህ ፣ የወልቂጤ ዩኒቨርሲቲ ብር 1 ሚሊዮን 490ሺህ 932፣ የሃረሚያ ዩኒቨርሲቲ ብር 17 ሚሊዮን 102ሺህ 289 በዋነኝነት የሚጠቀሱ መሆናቸውን ዋና ኦዲተሯ ገልጸዋል፡፡

እንደ ዋና ኦዲተሯ ማብራሪያ፤ በ2015 እና ከዚያ በፊት የተሟላ የሰነድ ማስረጃ ሳይቀርብላቸው ለተፈጸሙ ክፍያዎች በተሰጠው የማሻሻያ ሃሳብ መሠረት የተሟላ የሰነድ ማስረጃ የቀረበላቸው መሆኑን ለማረጋገጥ ኦዲት ሲደረግ በ26 መሥሪያ ቤቶች ማስረጃ ሊቀርብለት ከሚገባው በጠቅላላው 3 ቢሊዮን 622 ሚሊዮን 741ሺህ ብር ውስጥ 1 ቢሊዮን 949 ሚሊዮን 879 ሺህ 569 ( 54 በመቶ ) ማስረጃ የቀረበለት ሲሆን ቀሪው ከ 1 ነጥብ 6 ቢሊዮን ብር በላይ ማስረጃ ያልቀረበበት መሆኑን ማረጋገጥ ተችሏል፡፡

በግኝቱ ላይ ርምጃ ከወሰዱት መካከል የመስኖ እና ቆላማ አካባቢ ሚኒስቴር ብር 1 ቢሊዮን 584 ሚሊዮን 935 ሺህ 217 (99ነጥብ 5 በመቶ) ፣ የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር ብር 136 ሚሊዮን 999 ሺህ 117 (35 በመቶ)፣ ጅማ ዩኒቨርሲቲ ብር 116 ሚሊዮን 32ሺህ 664 (97 በመቶ) ፣ የአደጋ ስጋት ሥራ አመራር ኮሚሽን ብር 56 ሚሊዮን 178 ሺህ 158 (መቶ በመቶ ) ቡሌ ሆራ ዩኒቨርሲቲ ብር 22 ሚሊዮን 577 ሺህ 165 (44 በመቶ)፣ የኢትዮጵያ ስፖርት አካዳሚ ብር 21 ሚሊዮን 524 ሺህ 497 (90 በመቶ) ርምጃ በመውሰዳቸው በዋነኛነት ይጠቀሳሉ ብለዋል፡፡

በተጨማሪም በ2015/2016 በጀት ዓመት ተሠርተው ለመንግሥት ወጪ አስተዳደርና ቁጥጥር ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ተለይተው ከቀረቡለት የፋይናንሻልና ሕጋዊነት ኦዲት እና የክዋኔ ኦዲት ውስጥ 20 ይፋዊ የሕዝብ ስብሰባዎችን የባለድርሻ አካላትን ባሳተፈ መልኩ እና 15 የመስክ ምልከታዎች አካሂዷል፡፡ በዚሁ መሠረትም ይፋዊ ውይይቱ በሚደረግበት ወቅትም የኦዲት ግኝቱን ባህሪ መነሻ በማድረግ አቅጣጫዎች የተቀመጡ ሲሆን በ2015 በጀት ዓመት ሂሳባቸው ኦዲት ከተደረገው የፌዴራል ተቋማት መካከል ነቀፌታ የሌለባቸው ተቋማት በገንዘብ ሚኒስቴር አማካይነት በ2017 ለ12 ተቋማት የእውቅና እና የምስጋና ደብዳቤ መሰጠቱን አውስተዋል፡፡

በመክሊት ወንድወሰን

አዲስ ዘመን ረቡዕ ሰኔ 18 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You