እያንዳንዱ ዜጋ በባሕር በር ጉዳይ ላይ መነጋገር እንደሚኖርበት ተጠቆመ

አዲስ አበባ፣ እያንዳንዱ ዜጋ በባሕር በር ጉዳይ በቂ ግንዛቤ ይዞ መነጋገር እንደሚኖርበት የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ይግባኝ ሰሚ ፍርድ ቤት ምክትል ፕሬዚዳንት ወይዘሮ ፍራኦል ቶሎሳ አስታወቁ። የባሕር በር ጥያቄው አሁን ላይ ማንሳቱ ተገቢነት እንዳለው አመለከቱ።

ወይዘሮ ፍራኦል ለአዲስ ዘመን ጋዜጣ እንዳስታወቁት፣ በሀገሪቱ ውስጥ ብዙ የምንለያይባቸው ሃሳቦች ቢኖሩም የባሕር በር ጉዳይ ብሔራዊ ጥቅሞቻችን የምናረጋግጥበት ትልቁ አሁናዊና አንገብጋቢ ሀገራዊ አጀንዳ ነው ።

የባሕር በር ጉዳይ ልክ እንደ ዓባይ የጋራ አጀንዳችን ነው ያሉት ወይዘሮ ፍራኦል፤ ጥያቄው ተገቢውን ምላሽ እንዲያገኝ እያንዳንዱ ዜጋ በጉዳዩ ላይ በቂ ግንዛቤ ይዞ መነጋገር እንደሚኖርበት አሳስበዋል፡፡

በሀገሪቱ በፍጥነት እያደገ ያለውን ኢኮኖሚ እና የሕዝብ ቁጥር መሸከም የሚችል የባሕር በር ያስፈልጋል፣ የሀገሪቱ መሪዎች ጥያቄውን ያነሱት ጉዳዩ የሕዝብ አጀንዳ እና ብሔራዊ ጥቅሞቻችን መሠረት ያደረገ በመሆኑ ነው ብለዋል።

የባሕር በር ያለው ሀገር በዓለም አቀፍ ደረጃ የሚኖረውን ተፅዕኖ ተገንዝቦ መረባረብ እንደሚያስፈልግ ያመለከቱት ወይዘሮ ፍራኦል፤ አሁን ላይ ሀገሪቱ የባሕር በርን ጉዳይ ዋንኛ አጀንዳ አድርጋ መንቀሳቀሷ ተገቢነት እንዳለው አስታውቀዋል። ፈጣን ምላሽ እንደሚፈልግም ጠቁመዋል።

በዓለም አቀፍ ሕጎች ውስጥ የባሕር በር ጥያቄ መች መነሳት እንዳለበት የተቀመጠ ነገር ባይኖርም፤ ሀገራት ጥያቄውን ከራሳቸው ነባራዊ ሁኔታ ላይ ተመሥርተው ሊያነሱ እንደሚችሉ አመልክተዋል።

በሀገሪቱ ካለው ተጨባጭ እውነታ አኳያ የባሕር በር ጥያቄ አንገብጋቢ እንደሆነ አምና አሁን ላይ ጥያቄውን አንስታለች ያሉት ወይዘሮ ፍራኦል፣ ጥያቄው ጊዜውን የዋጀ እንደሆነም ጠቁመዋል።

ሀገሪቱ የባሕር በር ሳይኖራት እስከአሁን መቆየቷ ኢኮኖሚያዊ፣ ፖለቲካዊና ማኅበራዊ ችግሮች እንዲያጋጥማት አድርጓል ያሉት ምክትል ፕሬዚዳንቷ፣ ለጥያቄው ምላሽ ለማግኘት ሰላማዊ አማራጮችን እየተከተለች መሆኑ የሚበረታታ ነው ብለዋል።

ሀገሪቱ ሁልጊዜ ለችግሮች ዲፕሎማሲያዊ መንገድን እንደምትመርጥ ያመለከቱት ወይዘሮ ፍራኦል፤ የባሕር በር ጥያቄዋ ምላሽ እንዲያገኝ የምትፈልገው በሰላማዊ የዲፕሎማሲ መንገድ መሆኑን ዓለምአቀፍ ማኅበረሰቡ ሊረዳው እንደሚገባም አስገንዝበዋል።

የባሕር በር ጥያቄ ዓለምአቀፋዊ መብት ነው። በተለይም በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት በኩል የወጡ ሕጎች እንደሚያሳዩት የባሕር በር የሌላቸው ሀገራት፤ በተለይም እንደ ኢትዮጵያ ያሉ በተለያዩ መንገዶች የባሕር በር ያጡ ሀገራት የራሳቸው የባሕር በር የማግኘት ሙሉ መብት አላቸው ብለዋል።

በሕጎቹ ሀገራቱ የባሕር በር በስምምነት ወይም በድርድር የባሕርበር የሚያገኙበት ዕድል ስለመኖሩ ተደንግጓል። የባሕር በር ያላቸው ሀገራትም የባሕርበር የሌላቸው ሀገራት የባሕር በር እንዲኖራቸው ሁኔታዎችን የማመቻቸት ግዴታ እንዳለባቸው ተቀምጧል ብለዋል።

ኢትዮጵያ አሁን ያነሳችው የባሕር በር ጥያቄ፤ ዓለምአቀፋዊ መብትን መሠረት ያደረገ ብቻ ሳይሆን የሕዝቦቿን መብት የማስከበር ጉዳይ እንደሆነ አመልክተዋል።

የባሕር በር ጉዳይ ለአንድ ሀገር ወሳኝ ነው። በኢኮኖሚ ዓይን ብንመለከተው በየዓመቱ ለወደብ የሚወጣን ወጪ በመቀነስ፣ የሀገሪቱን ሁለንተናዊ ልማት ያፋጥናል ከዛም ባለፈ፤ ዘላቂ ሰላምን ለማረጋገጥ ሁነኛ መፍትሔ ይሆናል ብለዋል።

በጽጌረዳ ጫንያለው

አዲስ ዘመን ረቡዕ ሰኔ 18 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You