የቱሪዝም ዘርፉን ከቴክኖሎጂ ጋር የማስተሳሰር ሥራ እየተሠራ ነው

አዲስ አበባ፡- ከቱሪዝም የሚገኘውን ተጠቃሚነት ለማሳደግ ዘርፉን ከቴክኖሎጂ ጋር የማስተሳሰር ሥራ እየተሠራ እንደሚገኝ ቱሪዝም ሚኒስቴር ገለጸ።

የቱሪዝም ሚኒስትር ወይዘሮ ሰላማዊት ካሳ የኦሮሚያ ክልል ቱሪዝም ኮሚሽን የቱሪዝምና የቴክኖሎጂ ፎረም ትናንት ባካሄደበት ወቅት እንደገለጹት፤ እንደ ሀገር የቱሪዝም ዘርፉ ከኢኮኖሚ ምሰሶዎች እንደ አንዱ ተወስዶ የተለያዩ የፖሊሲ ድጋፎች ቢደረጉለትም ከቴክኖሎጂ ጋር የማስተሳሰር ጉዳይ አሁንም እንደ ተግዳሮት የሚወሰድ ነው። ምንም እንኳን በተለያዩ ሀገራት ያሉ ቴክኖሎጂዎችን ለመጠቀም ጥረት የሚደረግ ቢሆንም፤ ሀገር በቀል የሆኑ፤ የኢትዮጵያን ማህበረሰብ፣ ቅርስ፣ ማንነት እና ባህል በአግባቡ ተረድተው ለዓለም ለማስተዋወቅ የሚያስችሉ የቴክኖሎጂ ውጤቶች በሚፈለገው ልክ አለመኖሩ ለዚህ እንደምክንያት የሚነሳ መሆኑን ጠቁመዋል።

የቱሪዝም ዘርፉ ለኢኮኖሚው ካለው የጎላ ጠቀሜታ ባለፈ ለሀገር ገጽታ ግንባታ ትልቅ ጠቀሜታ እንዳለው ታምኖበት እየተሠራ መሆኑን ገልጸው፤ ከዚህ ቀደም ተዘንግቶ የነበረውን ዘርፉን ከቴክኖሎጂ ጋር ማስተሳሰር ሥራ ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ እየሠራ ይገኛል ብለዋል።

መሥሪያ ቤቱ በአዲሱ የቱሪዝም አዋጅ ዘርፉን በቴክኖሎጂ ለመደግፍ የሚያስችሉ መመሪያዎችን ማውጣቱን ጠቁመው፤ እነዚህን መመሪያዎች ተግባራዊ ከማድረግ ባሻገር ሥራ ፈጣሪዎች ቱሪዝምን በቴክኖሎጂ ከመደፍ አንጻር የሚያመጡትን አዳዲስ ሃሳብ ወደ ተግባር ለመቀየር በሚያደርጉት ጥረትም ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ ለመደገፍ ዝግጁ መሆኑን አመልክተዋል።

የቴክኖሎጂ ዓላማ ሕይወትን ማቅለል መሆኑን ያወሱት ወይዘሮ ሰላማዊት፤ ከሌሎች የዓለም ሀገራት ኢትዮጵያን ለመጎብኘት የሚመጡ ጎብኚዎች በሚኖራቸው ቆይታ ነገሮችን በቀላል ለመከወን የሚያስችሉ ቴክኖሎጂዎችን መፍጠር ፋይዳው ብዙ ነው። ከዚህ አንጻር አዳዲስ የፈጠራ ሃሳቦችን ይዘው ደጋፊ ያጡትን ቴክኖሎጂ ፈጣሪዎችን ማበረታታት ከሁሉም ባለድርሻ አካላት እንደሚጠበቅም ጠቁመዋል።

የኦሮሚያ ቱሪዝም ኮሚሽን ምክትል ኮሚሽነር አቶ ነጋ ወዳጆ በበኩላቸው እንደተናገሩት፤ ኢትዮጵያ ከአፍሪካ ግዙፍ አየር መንገድ እንዳላት ሀገር እንዲሁም፤ የተለያዩ በርካታ የቱሪዝም ሀብቶች ያሏት ሀገር ቢትሆንም፤ ከዘርፉ በሚፈለገው ልክ ገቢ እያገኘች አይደለም።

የዓለም ቱሪዝም ድርጀት እ.አ.አ በ2019 ባወጣው መረጃ ከሀገሪቱ አጠቃላይ ሀገራዊ ምርት አንድ 10ኛውን ቱሪዝም ነው የሚሸፍነው። ከሥራ አንጻርም የበለጠ መሥራት ከተቻለ የሚገኘውን ጥቅም ማሳደግ ይቻላል ብለዋል።

ከቱሪዝም ዘርፍ የሚገኘውን ጠቀሜታ ከማሳደግ አንጻር በቴክኖሎጂ መደገፍ ትልቅ ጠቀሜታ አለው ያሉት አቶ ነጋ፤ በክልሉ ዘርፉን ዲጂታላይዝ የማድረግ ሥራ ከተጀመረ አምስት ዓመት የተቆጠረ ሲሆን፤ ከ80 ቴራባይት በላይ የቱሪዝም አካባቢዎችን በፎቶ እና በተንቀሳቃሽ ምስል ለመያዝ መቻሉን ገልጸዋል።

በዚህም የተለያዩ ድረ-ገጾችን በማልማት በፎቶዎች አማካኝነት ያሉትን የቱሪዝም ሀብቶች ለዓለም የማስተዋወቅ ሥራ እየተሠራ መሆኑን ጠቁመው፤ ባለፉት አራት ዓመታት ሁለት መንደሮችን ዓለም አቀፍ የቱሪዝም መንደር አድርጎ ማስመዝገብ መቻሉን ተናግረዋል።

ዓመለወርቅ ከበደ

አዲስ ዘመን ማክሰኞ ሰኔ 17 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You