ለ55 ዓመታት በቴክኒክ የተካኑ ኢንጂነር

ዜና ሀተታ

ኢንጂነር ዳንኤል መብራቱ የዳን ቴክኖክራፍት እና የሊፍት ቴክኖሎጂ ድርጅት ባለቤት ናቸው። እንዲህ እንደዛሬው የቴክኒክና ሙያ ትምህርት በደንብ ትኩረት ባላገኘበት ጊዜ ነበር በ1965 ዓ.ም ከባህርዳር ፖሊ ቴክኒክ ኢንስቲትዩት ተመርቀው ክህሎትን እና ሥራ ፈጣሪነትን ተቀዳሚ ግባቸው በማድረግ ላለፉት 52 ዓመታት በፈጠራ ሥራ ላይ የተሠማሩት።

ኢንጂነር ዳንኤል የወር ደመወዝተኛ ለመሆን የመንግሥት ተቋማትን በሮች እየዞሩ ማንኳኳትን አልፈለጉም። ከዩኒቨርሲቲ እንደተመረቁ በትንሽ ካፒታል የራሳቸውን ፈጠራ ተጠቅመው ወደ ሥራ የገቡት። በዚህም ከራሳቸው አልፈው ለበርካቶች መትረፍና ሥራ መፍጠር ችለዋል።

በዚህ ረጅም ጉዟቸው የቢሮ እቃዎችን ከማምረት እስከ ሊፍት ማምረት ደርሰዋል፤ ለ350 ሺህ ሰዎችም የሥራ ዕድል ፈጥረዋል። በወቅቱ ኮምፒውተር ባለመኖሩ የተማሩትን የመካኒካል ሙያ በቀላሉ ወደ ተግባር ለመቀየር እንዲህ እንደዛሬው ቀላል አልበረም። ‹‹ወፍ አንደ ሀገሯ ትጮሃለች›› እንዲሉ ሥራዎቻቸውን በወረቀት ላይ በመንደፍ ወደ ቴክኖክራፍት ሙያ እንደገቡ ይናገራሉ።

ኢንጂነሩ ወደ ጃፓን፣ ኮሪያ እና አውሮፓ ሀገራት በተለያዩ ጊዜያት ለሥራ እና ስልጠና የሄዱባቸው አጋጣሚዎች እንዳሉ ይገልጻሉ። በጉዟቸው ሁሉ ለሀገራቸው የሚጠቅም እና ችግርን ሊፈታ የሚችል ቴክኖሎጂን መቅሰም የምንጊዜም ተግባራቸው እንደሆነ ያስረዳሉ።

በዚህም ላይ በርካታ ጥናቶችን በማድረግ ዕውቀትን ወደ ተግባር መቀየር የሚያስችሉ ተሞክሮዎችን በማድረግ ለራሳቸው እና ለሌሎች የሚተርፍ ሥራ መሥራታቸውን ይገልጻሉ።

ኢንጂነሩ ኢትዮጵያ ውስጥ ለመጀመሪያ ጊዜ የቴክኖክራፍት አምራች በመሆን ለቢሮ እና ለሆስፒታሎች እንዲሁም ለትምህርት ቤቶች አገልግሎት የሚሰጡ ሎከሮች፣ ሞደርን ስፔስ ሴቪንግ ፋይል ካብኔቶች፣ ሀገር ውስጥ እንዲመረቱ አድርገዋል። አሁንም በማምረት ላይ ይገኛሉ። በዚህ ሙያ ብቻ ከእርሳቸው ልምድ የቀሰሙ በርካታ ሰዎች የራሳቸውን ተመሳሳይ ማምረቻ ቦታ ከፍተው ሥራ ላይ እንዲሰማሩም ምክንያት ሆነዋል።

ድርጅታቸውን በየጊዜው በማሳደግ አሁን ላይ የውጭ የሊፍት ቴክኖሎጂ በሀገር ውስጥ ምርት በመተካት ከፍተኛ አስተዋጽኦ ያለው ሥራ እየሠሩ ይገኛሉ። በሊፍት ቴክኖሎጂ ከአፍሪካ ሀገራት ጋር ብቁ ተወዳዳሪ በመሆን ምርታቸውን ወደ ውጭ መላክ መጀመራቸውንም ነው የገለጹልን።

ኢንጂነሩ ጂቡቲ እና ሶማሌ ላንድ ላይ የሊፍት ቴክኖሎጂ ምርቶቻቸው እንደሚገኙ ይናገራሉ፤ ምርታቸውን ከእነዚህ ሀገራት በተጨማሪ ወደ ሌሎች አፍሪካ ሀገራት ለመላክ በቂ ዝግጅት እና የገበያ ትስስር ማድረጋቸውንም ያስረዳሉ፤ ለዚህም በቂ ስልጠና የወሰዱ፤ በሙያው የተካኑ የሊፍት ጥገና እና ተከላ ሠራተኞች እንዳሏቸው ይገልጻሉ።

ሥራ በትንሹ ቢጀመርም በመታተር ከተሠራ ወደ ከፍተኛ ደረጃ የሚደረስ በመሆኑ በተለይ በቴክኒክና ሙያ የተመረቃችሁ፤ ከእኔ ተሞክሮ ተምራችሁ ፤ ሥራን ሳትንቁ ጊዜውን በዋጀ ቴክኖሎጂ በመታገዝ የራሳችሁን ዐሻራ በማስቀመጥ፤ ለራሳቹ እና ለሀገራቹ ምሳሌ መሆን ትችላላችሁ ሲሉ ለተመራቂዎች መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል።

የሥራ እና ክህሎት ሚኒስትር ሙፈሪያት ካሚል በቴክኒክና ሙያ ተማሪዎች ምርቃ መርሃ-ግብር ላይ ተገኝተው ኢንጂነር ዳንኤል ላለፉት 55 ዓመታት ላበረከቱት የሥራ ፈጠራ እና የቴክኖሎጂ ሽግግር የክብር ካባ በማልበስ የመጀመሪያውን የሙያ ዕውቅና ሰጥተዋል።

ኢንጂነሩ ሥራ ከመፍጠር ባሻገር ችግር ፈቺ የሆኑ ምርቶች ላይ ትኩረት በማድረጋቸው እንዲሁም በተሰማሩበት መስክ ሁሉ የሀገራቸውን ስም ይዘው በመጓዝ እና ፋይዳውን በማሰብ ያደረጉትን ከፍተኛ ጥረት አድንቀዋል።

ሚኒስትሯ በንግግራቸው፤ የበርካታ ዓመታት ፅናት ይዘው፤ ዛሬ ላይ ሌላኛውን አዲስ ምዕራፍ ለመጀመርና ለማዘመን በድጋሚ መዘጋጀታቸው ዘመኑ ከበፊቱ ይልቅ ለፈጠራ እና ለሥራ ፈጣሪዎች ምቹ መሆኑን ያመላክታል ብለዋል።

ኢንስቲትዩቱ ጊዜውን የዋጀ ሥራ መሥራት እንደሚቻል ለተመራቂዎች እና ሥራው ላይ ላሉትና ብዙ ላልተነገረላቸው ዕውቅና በመስጠት እና በማነቃቃት፤ ዘርፉ ለወጣቶች ሳቢ እንዲሆን የተጀመረውን ጥረት አጠናክሮ መቀጠል እንደሚያስፈልግ ሚኒስትሯ ገልጸዋል።

ሔርሞን ፍቃዱ

አዲስ ዘመን ማክሰኞ ሰኔ 17 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You