ከ1 ነጥብ 2 ቢሊዮን ብር በላይ ያለአግባብ ክፍያ የፈጸሙ ተቋማት ለሕግ ቀረቡ

አዲስ አበባ፡- የዋና ኦዲተር መሥሪያ ቤት ለሦስት ዓመታት ከ1 ነጥብ 2 ቢሊዮን ብር በላይ ያለሕግ አግባብ ክፍያ የፈጸሙ ተቋማት ላይ የልዩ ኦዲት ምርመራ በማድረግ ለሕግ ማቅረቡን አስታወቀ።

የዋና ኦዲተር መሥሪያ ቤት ምክትል ዋና ኦዲተር አቶ አበራ ታደሰ ለአዲስ ዘመን እንዳስታወቁት፤ ከ1 ነጥብ 2 ቢሊዮን ብር በላይ አሠራር እና መመሪያን ያልተከተሉ ክፍያዎችን በፈጸሙ ተቋማት ላይ የልዩ ኦዲት በማድረግ እና ተጠያቂነትን ሊያስከትሉ የሚችሉ ፋይሎችን በማደራጀት ለፌዴራል ፖሊስ ወንጀል ምርመራ አስተላልፏል።

ለዋና ኦዲተር መሥሪያ ቤት በሕግ ከተሰጡት ሥልጣኖች መካከል የሕጋዊነት ኦዲት፣ የክዋኔ ኦዲት፣ የፋይናንስ ኦዲት፣ የአይቲ ኦዲት እና የልዩ ኦዲት ማድረግ እንደሆነ አመልክተው፤ እንዳስፈላጊነቱም ሌሎች ተጨማሪ ኦዲቶችንም በተቋማት ላይ ያደርጋል ብለዋል።

በፋይናንስ ኦዲት ግኝቶች መሠረት ልዩ ኦዲት በማድረግ ለሚፈጠሩ ምዝበራዎች ተጠያቂዎችን ለሕግ እንዲቀርቡ የማድረግ ሥልጣን እንዳለው ጠቁመዋል። ይህን ታሳቢ በማድረግም በ13 ተቋማት ላይ የ2015 እና 2016 ዓ.ም የልዩ ኦዲት ሥራ መሥራቱን አስታውቀዋል።

ከ13ቱ ተቋማት ሦስቱ የአሠራር ክፍተት ተገኝቶባቸው ልዩ ኦዲት እንደተደረገባቸው፤ አስሩ ተቋማት ደግሞ 437 ሚሊዮን 817ሺ 612 ብር ከግዥ መመሪያ እና ከሕግ አሠራር ውጪ ከፍለው እንደተገኙ አመልክተዋል። 2016/17 ዓ.ም ስምንት መሥሪያ ቤቶች 770 ሚሊዮን 527ሺ 849 ብር ከሕግ ውጪ በመክፈላቸው ልዩ ኦዲት ተደርጎባቸው ለሕግ መቅረባቸውንም ጠቁመዋል።

ወንጀሎቹ በአበል መልክ ከአበል መመሪያ ውጪ የተከፈሉ፣ ለሕንጻ ግንባታ ያላአግባብ ወጪ የተደረጉ፣ ከመመሪያ ውጪ ግዥ የተፈጸሙ እና በገቢ ሊሰበሰቡ ሲገባቸው ያልተሰበሰቡ መሆናቸውን አስታውቀዋል፤ ልዩ ኦዲት ከተደረገባቸው ተቋማት ውስጥ ሁለቱ የፖለቲካ ፓርቲዎች መሆናቸውን ገልጸዋል።

በተቋሙ ከ1መቶ በላይ የልዩ ኦዲት ጥቆማዎች ቢኖሩም ባለው የሰው ኃይል እጥረት ሁሉንም ለማዳረስ አልተቻለም ያሉት ምክትል ዋና ኦዲተሩ፤ አሁን ላይ የልዩ ኦዲት ሥራ ከአራት ባልበለጡ ቡድኖች እየተከናወነ መሆኑን አመልክተዋል። ሥራዎችን በሰፊው ለመከወን እና ቡድኑን ለማጠናከር መዋቅሮችን የማሻሻል ሥራ እየተሠራ እንደሆነም ገልጸዋል።

እንደ ምክትል ዋና ኦዲተሩ ገለጻ፤ የልዩ ኦዲት ሥራዎች የሚከናወኑት ምስጢራዊነታቸው ተጠብቆ ነው። ዓላማው ቀጥተኛ ተጠያቂነትን ማስፈን በመሆኑ ውጤታቸው ለምክር ቤት አይቀርብም። ፍርድ ቤቶቹም የሰው ምስክር ሲያስፈልጋቸው ኦዲተሮች የሚቀርቡበት ነው። የፍርድ ውሳኔ ከተላለፈባቸው በኋላ ግን ውሳኔው በሚዲያዎች ለማህበረሰቡ ይተላለፋል።

በዋና ኦዲተር መሥሪያ ቤት የኦዲት ሥራዎች ከተጠናቀቁ በኋላ በወንጀል እና በፍትሐብሔር የሚጠየቁ ግለሰቦችን የመለየቱን ሥራ አቃቤ ሕግ ሊያከናውኗቸው የሚገቡ መሆናቸውንም ጠቁመዋል። በእዚህ ረገድ የተቋማት መናበብ እና መቀናጀትም አስፈላጊ መሆኑን አስታውቀዋል። ቅንጅቱም ተጠያቂነትን ለማስፈን ትልቅ ሚና እንደሚኖረው አመልክተዋል።

ዋና ኦዲተር ኦዲት አድርጎ ሲጨርስ ለምክር ቤት የሚያቀርብ መሆኑንም ገልጸዋል። ተቋሙ የራሱ የሆነ ፍርድ ቤት የሌለው በመሆኑ የኦዲት ሥራዎች ሲጠናቀቁ ውጤቱን ለምክር ቤት ከመስጠት ባሻገር፤ ለፌዴራል ፖሊስ ወንጀል ምርመራ፣ ለፍትሕ ሚኒስቴር እና ለሌሎች ባለድርሻ አካላት ያሳውቃል፤ ፍርድ የማሰጠት ሥራውንም ባለድርሻ አካላቱ የሚከታተሉት ይሆናል ብለዋል።

በኦዲት ግኝቶች ላይ የሚፈጸሙ ስህተቶችን መነሻ በማድረግ ምክረ ሃሳብ ለሁሉም ኦዲት ተደራጊ መሥሪያ ቤቶች ይሰጣል ያሉት ምክትል ዋና ኦዲተሩ፤ የፍትሕ ሚኒስቴር ባደረገው ጥናት በተቋማቱ የአቅም፣ የተጠያቂነት፣ የቅንጅት እና የአሠራር ሥርዓት ክፍተቶች መኖራቸው መረጋገጡን አስታውቀዋል። ክፍተቶቹን ለመድፈን የሚያስችሉ ሥራዎች በቀጣይ እንደሚሠሩም ገልጸዋል።

በመክሊት ወንድወሰን

አዲስ ዘመን ሰኞ ሰኔ 16 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You