
ዜና ሀተታ
አንጋፋነት ባስቆጠሩት እድሜ ብቻ የሚለካ ሳይሆን የካበተ ልምድና ተሞክሮን ያጣመረ ውጤታማ ሥራ መሥራትን የሚፈልግ ስለመሆኑ አያጠያይቅም። ከእዚህ ባሻገር የካበተ ልምድን ተጠቅሞ በእውቀት ላይ የተመሠረተ ሀገራዊ ፋይዳቸው የጎላ የምርምር ሥራዎች በመሥራት እረገድም የላቀ አበርክቶ ሊኖርም የግድ ይላል።
በተለይ የማህበረሰቡን ችግሮች ሊፈቱ የሚችሉ፣ አገልግሎት አሰጣጥን የሚያሳልጡ ዘመናዊ አሠራሮች በመፍጠር ቀዳሚ ሆኖ መገኘት ከአንጋፋነት የሚጠበቅ ነው። የ70ና የ100 ዓመታት የካበተ እውቀትና ልምድን ተጠቅሞ ለሌሎች አርአያ የሚሆን ከትውልድ ወደ ትውልድ ሊተላለፍ የሚችል ጽኑ መሠረት ማቆም አስፈላጊ ስለመሆኑም አይጠያይቅም።
ባሳለፍነው ሳምንት መጨረሻ አንጋፋው የጎንደር ዩኒቨርሲቲ የተመሰረተበትን 70ኛ ዓመትና የማስተማሪያ ሆስፒታሉን 100ኛ ዓመት ምስረታ በዓል አስመልክቶ አርአያነቱን ያስመሰከረበት በተግባር የተገለጡ ለሌሎች አርአያ ሊሆኑ የሚችሉ 22 ፕሮጀክቶችን በመገንባት አስመርቋል። እነዚህ ፕሮጀክቶቹንም ከተለያዩ ሚዲያዎች ከተወጣጡ ጋዜጠኞች ቡድን ጋር በመሆን የመጎብኘት እድሉን አግኝተናል።
ፕሮጀክቶቹን ተዘዋውረን እንደተመለከትነው በምርምር የታገዙ ናቸው። የመማር ማስተማር ሂደቱን ከማገዝ ባሻገር በጤናው ዘርፍ የሚሰጡ አገልግሎቶችን የሚያሻሽሉና የሚያሳልጡ፤ ዩኒቨርሲቲው ያለውን ፕሮጀክቶች የመምራትና የመፈጸም አቅም በጉልህ ያሳዩም ናቸው።
ከእነዚህም 22 ፕሮጀክቶች መካከል የካንሰር ጨረር ሕሙማን ማዕከል፣ የኦክስጅን ማምረቻና ህክምና ማዕከል፣ የፈሳሽ ቆሻሻ ማጣሪያ ማዕከል፣ የቅድመ ህክምና ላብራቶሪ ህንጻ፣ የደረቅ ቆሻሻ ማቃጠያ ማዕከል፣ የሰው ሰራሽ እግር ማምረቻ ማዕከል፣ የድንገተኛ ሕክምና ማዕከል፣ የውስጥ ደዌና የጽኑ ሕሙማን ሕክምና መስጫ ማዕከል፣ የመረጃና ደህንነት ቴክኖሎጂ ማዕከል፣ የማህበረሰብ አቀፍ ሬዲዮ፣ የንጽህ መጠጥ ውሃ ፕሮጀክት፣ የእርሻ መካናይዜሽን ፕሮጀክት ተጠቃሽ ናቸው።
የጎንደር ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንት ዶክተር አስራት አጸደወይን ፕሮጀክቶቹን አስመልክቶ በሰጡት ማብራሪያ፤ ፕሮጀክቶች ባለፉት ሁለትና ሦስት ዓመታት የተጠናቀቁ ቢሆንም የዩኒቨርሲቲውን የ70ና የ100ኛ ዓመታት ምስረታ በዓል ምክንያት በማድረግ በአንድነት እንዲመረቁ አድርጓቸዋል።
ከእነዚህ መካከልም አምስት የሚሆኑት ቀደም ሲል ባሉት አመራሮች የተጀመሩ ሲሆን፤ እነዚህን የማጠናቀቅና የማስቀጠል ሥራ መሥራቱን ጠቅሰው፤ ቀሪዎቹ 17 የሚሆኑ አዳዲስ ፕሮጀክቶች በመሆናቸው አሁን ባሉት አመራሮች ተጀምረው የተጠናቀቁ ስለመሆናቸው ገልጸዋል።
ዩኒቨርሲቲው ፕሮጀክቶቹን በአራት ሚሊዮን ብር ወጪ ያስገነባቸው መሆኑን የጠቀሱት ፕሬዚዳንቱ፤ ፕሮጀክቶቹ የመማር ማስተማሩ፣ ምርምርና በተለይ የሆስፒታል አገልግሎት ለማሳለጥ ከፍተኛ አስተዋጽኦ የሚያበረክቱ መሆናቸውን ይገልጻሉ። የአገልግሎት አሰጣጥ ጥራትም የሚጨምሩ ከመሆናቸው ባሻገር ተደራሽነት በማስፋትና የመቀበል አቅም ለማሳደግ ከፍተኛ ሚና አላቸው ሲሉም ይናገራሉ።
ፕሮጀክቶቹ አብዛኛውን በሆስፒታሉ የሚገኙ እንደመሆናቸው የሆስፒታሉን የጤና ትምህርት የመቀበል አቅም ለመጨመር ያላቸው ጠቀሜታ የጎላ ነው ያሉት ፕሬዚዳንቱ፤ 22ቱም ፕሮጀክቶች አሁን ላይ ዘመኑ የሚፈልገውን ጥራት የሚያመጡና የመማር ማስተማር ሂደት ምቹ መደላድሎችን የሚፈጥሩ ናቸው።
ፕሮጀክቶቹ ዩኒቨርሲቲውን በአፍሪካ ከምርጥ የምርምር ዩኒቨርሲቲዎች አንዱ ለመሆን የያዘውን እቅድ ለማሳካት፣ አገልግሎቱን ይበልጥ ለማዘመን፣ የላቀ ትውልድና ሀገር ግንባታ ዐሻራቸውን እንዲያኖር ጉልህ አበርክቶ እንደሚኖራቸው አመልክተዋል።
የጎንደር ዩኒቨርሲቲ የአስተዳደርና ልማት ምክትል ፕሬዚዳንት አቶ ልጅአለም ጋሻው በበኩላቸው፤ አብዛኛዎቹ ፕሮጀክቶች ከማህበረሰብ አገልግሎት፣ ከሕክምና፣ ከመማር ማስተማርና ከምርምር ጋር የተገናኙ መሆናቸውን ተናግረዋል። አክለውም የዩኒቨርሲቲውን ተቋማዊ አቅም በማሳደግ ረገድ ከፍተኛ አበርክቶ እንዳላቸው ይገልጻሉ።
ዩኒቨርሲቲው በተለይ በሕክምና ዘርፍ የረጅም ዓመታት ልምድ ያካበተ መሆኑን ጠቅሰው፤ አስር የሚሆኑት ፕሮጀክቶች የሕክምናው ዘርፍ አገልግሎት አሰጣጥ በማዘመን ረገድ ከፍተኛ ሚና የሚጫወቱ ናቸው ብለዋል።
በተለይ የካንስር ጨረር ሕክምና ማዕከሉ የተሟላ ዘመናዊ ማሽን የተገጠመለትና ብቁ የሆኑ ባለሙያዎች ያሉት ነው ያሉት ምክትል ፕሬዚዳንቱ፤ ማዕከሉ ሕክምና መስጠት መጀመሩ ዘርፈ ብዙ ጠቀሜታ እንዳለው ገልጸዋል።
በጎንደር ከተማ ካለው የመጠጥ ውሃ ችግር የተነሳ ዩኒቨርሲቲው የችግሩ ተጋላጭ መሆኑን ጠቁመው፤ ዩኒቨርሲቲው የመጠጥ ውሃ ማቅረብ የሚያስችል ፕሮጀክት ወደ ሥራ በማስገባት የመጠጥ ውሃ ችግሩን መቅረፍ መቻሉን ይገልጻሉ። ሌሎችም ፕሮጀክቶች ዘርፈ ብዙ ጠቀሜታ ያላቸው ስለመሆናቸው ይናገራሉ።
በወርቅነሽ ደምሰው
አዲስ ዘመን ሰኞ ሰኔ 16 ቀን 2017 ዓ.ም