“ጦርነትን በትንሽ ኪሳራ በድል የሚወጣ ሠራዊት እየተገነባ ነው” – ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ ጁላ

አዲስ አበባ፦ ጦርነትን ሳይዋጋ ከሩቅ የሚያስቀር፤ ከተፈጠረም በትንሽ ኪሳራ በድል የሚወጣ ሠራዊት እየተገነባ መሆኑን የጦር ኃይሎች ጠቅላይ ኤታማዦር ሹም ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ ጁላ አስታወቁ።

የመከላከያ ዋር ኮሌጅ ትናንት በመደበኛ ኮርስ ያሠለጠናቸውን ከፍተኛ መኮንኖች ባስመረቀበት ወቅት ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ፤ አሁን ላይ ጦርነትን በትንሽ ኪሳራ በድል የሚወጣ ሠራዊት እየተገነባ ነው ብላዋል።

የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት ግዴታውን በውጤታማነት የሚፈጽም፣ ዓለም አቀፍ የጸጥታ እና የደህንነት ሁኔታን ታሳቢ ባደረገ መልኩ የተገነባ ፕሮፊሽናል ሠራዊት መሆኑን አመልክተው፤ የመከላከያ አመራሮች የዘመኑን የቴክኖሎጂ እድገትና ስልጣኔ የሚመጥን አቅም በመላበስ ሠራዊቱን በተገቢው መንገድ መርቶ ወደ ድል ማብቃት እንደሚጠበቅባቸው አሳስበዋል።

አሁን ላይ ሠራዊቱ ሀገራዊ፣ ቀጣናዊ እንዲሁም ዓለም አቀፋዊ የደህንነት እና የጸጥታ ተለዋዋጭ ሁኔታን በመረዳት፣ አቅሙ እና የዘመኑን ቴክኖሎጂ ታጥቆ፣ በፈተና ውስጥ ይበልጥ እየጸና ኢትዮጵያን ማሻገሩን ገልጸዋል።

ሀገራችን ተልዕኮውን በላቀ ብቃት መፈጸም የሚችል በእውቀትና በክህሎት የጎለበተ ሠራዊት ያስፈልጋታል፤ ተገንብቷልም ብለዋል። ሠራዊቱ የታጠቀውን የዘመኑን ቴክኖሎጂ በወታደራዊ ኢንዱስትሪዎችና በጥናትና ምርምር ማሳደግ እንደሚገባውም ጠቁመዋል።

ተመራቂዎች በእዚህ ወቅት ሀገራችን እያጋጠሟት ካሉ የውስጥ ግጭቶችና በቀጣናው ሊያጋጥሙ ከሚችሉ ትንታኔዎች በመነሳት ዝግጁነቱ የጎለበተና ሳይዋጋ ማሸነፍ የሚችል ሠራዊት ከመፍጠር አኳያ የጎላ ሚና መጫወት እንዳለባቸውም አመልክተዋል።

የቀጣናውን ነባራዊ ሁኔታ በተገቢው መንገድ መገንዘብ እንደሚገባ ጠቁመው፤ ሠራዊቱ የባሕር በርን ጨምሮ የኢትዮጵያን ብሔራዊ ጥቅሞች ለማስጠበቅ በሚደረገው ጥረት የበኩሉን አስተዋጽኦ እየተወጣ ይገኛል ብለዋል።

መንግሥት ፊቱን ወደ ልማት በማዞር ግዙፍ ፕሮጀክቶችን እያሳካ የሀገሪቷን ከፍታ እያረጋገጠ መሆኑን አመልክተው፤ የሠራዊቱ አመራሮች ሕዝቡን የሚጠቅም የልማት ሥራዎች ተሳትፎ እንዲያደርጉ አሳስበዋል።

በእለቱ ኮሌጁ በ3ኛ ዙር መደበኛ ኮርስ ያሠለጠናቸውን ከፍተኛ መኮንኖች በዲፕሎማና በማስተርስ ዲግሪ በደማቅ ሥነ-ሥርዓት አስመርቋል። በሥነ ሥርዓቱ ላይ የጦር ኃይሎች ጠቅላይ ኢታማዦር ሹም ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ ጁላን ጨምሮ ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች ተገኝተዋል፤ ብልጫ ውጤት ላስመዘገቡ ተመራቂ አመራሮች ሰርተፊኬትና ሽልማት ተበርክቷል።

በጋዜጣው ሪፖርተር

አዲስ ዘመን ሰኞ ሰኔ 16 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You