ባለፉት ስድስት ዓመታት የመንገድ ግንባታ 550 በመቶ ዕድገት አሳይቷል

– በባቡር ትራንስፖርት 60 በመቶ ወጪን መቀነስ ተችሏል
– በአየር ትራንስፖርት ከዓለም ሀገራት ጋር ተወዳዳሪ ለመሆን እየተሠራ ነው

ድሬዳዋ፡- ባለፉት ስድስት ዓመታት የተከናወኑ የመንገድ ግንባታ ሥራዎች ካለፉት 20 እና 30 ዓመታት ከተሠራው ጋር ሲነጻጸር ከ550 በመቶ በላይ ዕድገት ማሳየቱን የኢትዮጵያ ኮንስትራክሽን ሥራዎች ኮርፖሬሽን አስታወቀ። የበባቡር ትራንስፖርት በአየር እና በመኪና ሊያስወጣ የሚችለውን ወጪ 60 በመቶ መቀነስ ማስቻሉን አመለከተ።

ሰሞኑን “ስለኢትዮጵያ መሠረተ ልማት” በሚል በኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት አዘጋጅነት በድሬዳዋ ከተማ በተካሔደው ስለኢትዮጵያ መድረክ ላይ የኮርፖሬሽኑ ዋና ሥራ አስፈጻሚ ኢንጂነር ዮናስ አያሌው እንዳመለከቱት፤ ሀገራዊ የመንገድ ግንባታ ባለፉት ስድስት ዓመታት ቀደም ሲል ከነበረበት 26 ሺህ ኪሎ ሜትር ወደ 275 ሺህ ኪሎ ሜትር አድጓል። ይህም በመቶኛ ሲሰላ ከ550 በመቶ በላይ ነው።

በሀገር አቀፍ ደረጃ በፍጥነት ካደጉ/ እያደጉ ከመጡ መሠረተ ልማቶች የመንገድ መሠረተ ልማት ተጠቃሽ መሆኑን ያስታወቁት ዋና ሥራ አስፈፃሚው፤ ከሀገሪቱ ሥፋት እና ከመንገድ መሰረተ ልማት አስፈላጊነት አንፃር አሁንም በዘርፉ ብዙ መስራት እንደሚቀር አመልክተዋል።

አፍሪካዊ በሆነ መስፈርት በአንድ ሺ ካሬ ሜትር ስኩዌር 204 ኪሎ ሜትር ወይም 37 በመቶ አማካኝ የመንገድ ሽፋን ሊኖር እንደሚገባ የጠቆሙት ኢንጂነር ዮናስ፤ ከዚህ ቁጥር ጋር ሲነፃፀር አሁንም የመንገድ መሰረተ ልማታችን ወደ ኋላ የቀረ ነው ብለዋል። በቀጣይ በተለይ ክልሎችን ከክልሎች፤ ከተማን ከከተማ እንዲሁም የገጠሩን አካባቢ እርስ በእርስ ለማገናኘት የሚያስችሉ የመንገድ መሠረተ ልማቶች በስፋት እንደሚሠሩ ጠቁመዋል።

ከአዲስ አበባ ጅቡቲ የተገነባው 759 ኪሎ ሜትር የሚሸፍነው የባቡር መሰረተ ልማት ሰዎችን ከማመላለስ በተጨማሪ የወጪ እና ገቢ ምርቶችን በማመላስ ረገድ እያደረገ ያለው አስተዋጥኦ ከፍተኛ እንደሆነ አመልክተዋል። ምርቶችን በአየር እና በመኪና ለማጓጓዝ የሚያስወጣውን ወጪ ከ60 በመቶ በላይ መቀነስ ማስቻሉንም ጠቁመዋል።

ከወጪ ቅነሳው በተጨማሪ፣ በመኪና እና በአየር መንቀሳቀስ የማይችሉ ትልልቅ ቁሶችን በባቡር ማጓጓዝ ማስቻሉን አመልክተው፣ ከጅቡቲ በተጨማሪ ወደ ሌሎች አገራት የባቡር መሰረተ ልማትን ማስፋፋት እንደሚገባ ጠቁመው፤ ለዚህም የተለያዩ ውይይቶች እየተደረጉ መሆናቸውን አስታውቀዋል።

ከአየር መሠረተ ልማት አንፃር አሁን ላይ በሀገር አቀፍ ደረጃ 50 ኤርፖርቶች አሉ። ከእነዚህ ውስጥ 22ቱ መደበኛ አገልግሎት እየሠጡ ናቸው፤ አራት እና አምስት የሚሆኑትን ዓለም አቀፍ ደረጃዎችን እንዲያሟሉ ዕቅድ ተይዞ እየተሠራ መሆኑን አመልክተዋል ።

በአፍሪካ ደረጃ ትልቅ እና ብዙ ሕዝብ ማስተናገድ የሚችል ኤርፖርት በቢሾፍቱ መገንባት የተጀመረ መሆኑን አስታውሰው፤ ይህ የኢትዮጵያን የአየር ትራንስፖርት እጅግ ዘመናዊ እና ከሌሎች የዓለም አገራት ጋር ተወዳዳሪ ማድረግ የሚያስችል እንደሚሆን ገልጸዋል።

ከውሃ ትራንስፖርት ጋር ተያይዞ ኢትዮጵያ እየተጠቀመች ያለችው የጅቡቲን ወደብ መሆኑን በማስታወስ፤ የሌሎች አገሮችንም ወደቦች ለመጠቀም ከፍተኛ ጥረት እየተደረገ መሆኑን አስታውቀዋል ። በአገር ደረጃ የባሮ ወንዝ በመጠቀም የውሀ ትራንስፖርትን ለማስፋት እየተሰራ ነው፤ እንደሌሎች ሀገራት የውሃ ትራንስፖርቱ አድጎ መጓጓዣ እንዲሆን ተሠርቷል ማለት ግን አይቻልም ብለዋል። በቀጣይ በሰፊው ሊሠራበት የሚገባ እና ትኩረት የሚሻ ጉዳይ መሆኑንም አመላክተዋል።

እነዚህን መሠረተ ልማቶች እርስ በእርስ ማስተሳሰር እንደሚያስፈልግ ያመለከቱት ዋና ሥራ አስፈፃሚው፤ የባቡር መሠረተ ልማት ከመንገድ ወይም ከአየር ትራንስፖርት ጋር፤ የአየር ትራንስፖርት እንደዚሁ ከመንገድ ትራንስፖርት ጋር ማስተሳሰር ወሳኝ መሆኑን አስታውቀዋል፤ ትራንስፖርትን ከማሳለጥ ጋር ተያይዞ በዋናነት ማቀናጀትን በተመለከተ በሰፊው ሊሠራ እንደሚገባ አስገንዝበዋል።

በምሕረት ሞገስ

አዲስ ዘመን ሰኞ ሰኔ 16 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You