
አዲስ አበባ፡- ኢኮትሬድ/ ECOTRADE/ ፕሮጀክት ኢትዮጵያ በአፍሪካ አህጉራዊ ነፃ የንግድ ቀጣና ንቁ ተዋናይ እድትሆን እንደሚያግዝ የንግድ እና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስትር ካሳሁን ጎፌ (ዶ/ር) ገለጹ።ከአውሮፓ ህብረት በተገኘ 6 ሚሊዮን ዩሮ የሚተገበር ኢኮትሬድ የተሰኘ ፕሮጀክት ትናንት ይፋ ተደርጓል፡፡
ሚኒስትሩ በመርሃግብሩ ላይ እንዳሉት፤ የኢትዮጵያን ንግድና ኢኮኖሚ ትስስርን በግሉ ዘርፍ የነቃ ተሳትፎና የእሴት ሰንሰለት ለማጠናከር እየተሠራ ነው።ኢኮትሬድ ፕሮጀክትም ቀጣይነት ያለው የንግድ ትስስርን ለማረጋገጥና ኢትዮጵያ በአፍሪካ አህጉራዊ ነፃ የንግድ ቀጣና ንቁ ተዋናይ እንድትሆን ያግዛል፡፡
ፕሮጀክቱ የግሉን ሴክተር አቅም ግንባታ፣ የንግድ ፖሊሲዎችን ከአፍሪካ አህጉራዊ ነፃ የንግድ ቀጣና የንግድ ሥርዓቶች ጋር ማጣጣም እና ቀጣናዊ የንግድ ግንኙነትን ማጠናከር ላይ ያተኮረ መሆኑን ጠቅሰው፤ በተለይም ለአነስተኛ እና መካከለኛ ኢንተርፕራይዞች እና በሴቶች ለሚመሩ የንግድ ድርጅቶች ላይ ትኩረቱን አድርጎ እንደሚሠራ ገልጸዋል፡፡
የኢኮ ትሬድ (ECOTRADE) ፕሮጀክት የአፍሪካ አህጉራዊ ነፃ የንግድ ቀጣና ትግበራን አካታችና የዘርፎች ብዝሃነት እንዲረጋገጥ ትልቅ ፋይዳ እንዳለው አመልክተው፤ የግሉን ሴክተር ማሳተፍ፣ የንግድ ሂደት የእሴት ሰንሰለቶችን ማቀናጀት ላይ አተኮሮ ይሠራል።በተጨማሪም የጥናትና ምርምር ሥራዎችን በመደገፍ ትክክለኛ ውሳኔ መስጠት የሚያስችል ሥርዓት ለመፍጠር እንደሚረዳ ጠቁመዋል፡፡
ኢትዮጵያ አካታች፣ ተወዳዳሪ እና ቀጣይነት ያለው ኢኮኖሚያዊ እድገትን ለማስመዝገብ እየሠራች መሆኑን ጠቁመው፤ የቀጣናውን ኢኮኖሚያዊ ትብብር እንዲጠናከር እየሠራች ነው።
የአውሮፓ ህብረትና ሌሎችም ባለድርሻዎች የኢትዮጵያ የጀመረችውን ጉዞ ለመደገፍ ለወሰዱት ርምጃ ምስጋና አቅርበዋል፡፡
በኢትዮጵያ የአውሮፓ ህብረት አምባሳደር ሶፊ ፍሮም ኤመስበርገር በበኩላቸው፤ የአፍሪካ ነጻ የንግድ ቀጣና ትግበራ እውን መሆን ለአህጉሪቱ ኢኮኖሚያዊ እድገት ትልቅ ሚና ይኖረዋል ብለዋል፡፡
የአውሮፓ ህብረት ከንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስቴር ጋር በመተባበር ይፋ ያደረገው የኢኮትሬድ ፕሮጀክት ኢትዮጵያ በአፍሪካ ነጻ የንግድ ቀጣና ያላትን ተሳትፎ እንደሚያጠናክር አንስተው፤ ለሴቶች እና ወጣት ሥራ ፈጣሪዎች እዲሁም ለአነስተኛና መካከለኛ ኢንተርፕራይዞች ትልቅ አቅም እንደሚፈጠር ጠቁመዋል።
የግሉን ዘርፍ አቅም ማጠናከር፣ የልማት ሥራ ትግበራዎችን እና ቀጣናዊ የንግድ ትብብር ማሳደግ ላይ ትኩረት ተደርጎ እንደሚሠራም አመልክተዋል፡፡
ፕሮጀክቱ ቀጣናዊ የእሴት ሰንሰለትን ለማቀናጀት የሚያስችሉ የንግድና የትራንስፖርት መሠረተ ልማቶችን ማጠናከር፣ በተቋማት መካከል የእሴት ሰንሰለት እና የንግድ ፖሊሲ የማልማት አቅምን መገንባት ላይ ትኩረት እንደሚያደርግ የተጠቀሰ ሲሆን፤ ለሚቀጥሉት አራት ዓመታት እንደሚዘልቅ ተመላክቷል፡፡
ፋንታነሽ ክንዴ
አዲስ ዘመን ቅዳሜ ሰኔ 14 ቀን 2017 ዓ.ም