ሀገሩን የሚወድ ብቁ ዜጋ ለማፍራት ስካውት ማህበራትን መደገፍ ይገባል

አዲስ አበባ፡- ሀገሩን የሚወድ ብቁ ዜጋ ለማፍራት ለስካውት ማህበራት ድጋፍ እየተደረገ መሆኑን የአዲስ አበባ ስካውት ኮሚሽን ገለጸ፡፡

የአዲስ አበባ ስካውት ኮሚሽን ኮሚሽነር ሁልጌኛ ሁንዴሳ ለአዲስ ዘመን ጋዜጣ እንደገለጹት፤ ስካውት ማለት ትምህርታዊ የሆነ የወጣቶች እንቅስቃሴ ነው። በፈቃደኝነት ላይ የተመሠረተ ከፖለቲካ ተግባር ነጻ የሆነ፣ በዘር፣ በቀለም፣ በሃይማኖትና በጎሳ ልዩነት የማያደርግ ዓለም አቀፍ የወጣቶች እንቅስቃሴ ነው። ብቁ፣ ንቁ፣ ከሱስ የጸዳ እና ጠንካራ ዜጋ ለማፍራት ለማህበራቱ ድጋፍ ሊደረግ እንደሚገባ ተናግረዋል፡፡

የስካውት እንቅስቃሴ ዋና ዓላማ በአካል የጠነከረ፣ በመንፈስ የዳበረ፣ በአዕምሮ የላቀ በራሱ የሚተማመን ታላቅ ታናሹን የሚያከብር ትውልድ እና ሀገሩን የሚወድ ዜጋ ማፍራት መሆኑንም ገልጸዋል፡፡

በአሁኑ ጊዜ በትምህርት ቢሮ ፈቃድ በየትምህርት ቤቱም የስካውት ክበቦች እየተቋቋሙ ቢሆንም የሚያቋቁሙት መምህራን የስካውት ስልጠናን ያልወሰዱ መሆናቸው ተገቢውን ውጤት ለማምጣት አስቸጋሪ እንደሚሆንም ተናግረዋል። መንግሥትም እዚህ ላይ ትኩረት በመስጠት ለማህበሩ ድጋፎችን በማድረግ በቅንጅት ሊሠራ እንደሚገባም ገልጸዋል።

በማህበራቱ የሚገቡ ወጣቶች በትምህርታቸው የደከሙ እና በሥነምግባራቸው ወጣ ያሉ ቢሆኑም ስልጠናውን ከወሰዱ በኋላ ሙሉ በሙሉ ለውጥ የሚመጡ መሆኑንም ተናግረዋል። የስካውት ሰልጣኝ ሥራን የማይንቅ ብቁ አምራች መሆኑንም በተለያየ ጊዜ ማስመስከሩንም ጠቁመዋል፡፡

የአዲስ አበባ ስካውት ከመንግሥት እና ከሌሎች በጎ ፈቃደኛ ግለሰቦች ድጋፍ ቢያገኝ በ2025 ዓ.ም 1 ሚሊዮን ብቁ የስካውት ሰልጣኝ አባላትን የማፍራት እቅድ እንዳለውም ኮሚሽነር ሁንጌኛ ገልጸዋል። ለስካውት ማህበራት ድጋፍ ማድረግ ማለትም የነገን ኢትዮጵያን ዛሬ መገንባት ማለት መሆኑንም ተናግረዋል።

የስካውት ማህበር በኢትዮጵያ የተመሠረተው በአጼ ኃይለሥላሴ ዘመን መሆኑን የሚናገሩት ኮሚሽነሩ፤ የኢትዮጵያ መንግሥት ለስካውት እንቅስቃሴ ሰፊ ትኩረት ሰጥቶ በመንቀሳቀሱ ኢትዮጵያ የዓለም የስካውት ማህበር አባል ሀገር ለመሆን መብቃቷን አብራርተዋል።

እንደ ኮሚሽሩ ገለጻ፤ እንቅስቃሴውም በደርግ ዘመን ተቋርጦ የነበረና፤ የወጣቶች ስካውት እንቅስቃሴ ከደርግ መንግሥት መውደቅ በኋላ የመደራጀት መብትን በመጠቀም እንደአዲስ ተቋቁሟል። በስካውት የሚሰለጥኑ ወጣቶች የማንበብ ልምዳቸው የዳበረ፣ ጥሩ ተናጋሪ እና ሀገራቸውን የሚወዱ ዜጎች ናቸው። በሁለተኛው የጣሊያን ወረራ ጊዜም 160 ስካውቶች በጦርነቱ ላይ ተሳታፊ በመሆን ለሀገራቸው ያላቸውን ፍቅር አሳይተዋል ሲሉ አውስተዋል፡፡

የስካውት ስልጠና ከወታደራዊ ስልጠና ጋር ተመሳሳይነት ያለው መሆኑን ጠቁመው፤ ስልጠናውን የሚወስዱ ወጣቶችም ከሶስት እስከ ስድስት ወር እንደሚፈጅባቸው እና የሚመረቁትም ስልጠናቸውን በተግባር መከወን ሲችሉ ብቻ እንደሆነ ገልጸዋል።

ስካውት የሰለጠነ ወጣት እና ታዳጊ የመጀመሪያ ደረጃ የህክምና ርዳታን መስጠት የሚችል፣ የትራፊክ ፍሰቱን ማሳለጥ ሚችል በጎ ፈቃደኛ እና በአጠቃላይ ሀገሩን ለማልማት በሥነምግባር የታነጸ ትውልድ መሆኑንም ኮሚሽሩ ገልጸዋል።

በየክልሉ ካሉ ስካውቶች ጋር በሁለት ዓመት አንዴ ጃንቡሬ የሚባል በዓል የሚያከብሩበት እና ከሌሎች የዓለም ስካውቶች ማህበራትም ጋርም በተለያዩ ፕሮግራሞች በጋራ የሚሠሩ መሆኑን ጠቁመዋል።

መክሊት ወንድወሰን

አዲስ ዘመን ቅዳሜ ሰኔ 14 ቀን 2017 ዓ.ም

 

 

 

Recommended For You