የደንበኞችን አገልግሎት የሚያዘምኑ ሥራዎች

ከደንበኞች በየጊዜው በርካታ ጥያቄዎች ከሚነሱበት ተቋማት መካከል አንዱ የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት ነው። አገልግሎቱ በመላው ሀገሪቱ በሚሰጠው የኤሌክትሪክ አገልግሎት ዙሪያ ዘርፈ ብዙ ችግሮች እንዳሉም በተደጋጋሚ ይነሳል። ይሁን እንጂ በተያዘው በጀት ዓመት ጀምሮ እስካሁን ድረስ አገልግሎቱ የዳታ ማዕከል ከመገንባት ጀምሮ ዲጂታል የአሠራር ሥርዓቶች በመዘርጋት የደንበኞች አገልግሎት ጥራት ሊያመጡ የሚችሉ የሪፎርም ሥራዎች እየሠራ መሆኑን ይገልጻል፡፡

የአገልግሎቱ የደንበኞች ግንኙነት ማዕከል ኃላፊ ስምረት በለጠ እንደተናገሩት፤ በ2017 በጀት ዓመት የደንበኞች አገልግሎት አሰጣጥ ዘመናዊ በሆነ መልኩ ለማደራጀት ሪፎርም እየተሠራ ነው። በሪፎርሙ ጥራት ያለው አገልግሎት ለመስጠት የደንበኞች አገልግሎት ማዕከል በአዲስ መልኩ እንዲደራጅ ተደርጓል ይላሉ፡፡

በመላው ሀገሪቱ ያሉ ደንበኞች ሊያስተናግድ የሚያስችል የአሠራር ሥርዓት እየተዘረጋ ነው ያሉት ኃላፊዋ፣ የጥሪ መቀበል አቅም በሀገር አቀፍ ደረጃ ለማሳደግ ብዙ ሥራዎች እየተሠሩ መሆኑን ይገልጻሉ።

905 የጥሪ ማዕከል ቀደም ሲል ለአዲስ አበባ ከተማ ኤሌክትሪክ አገልግሎት ደንበኞች ብቻ የጥሪ አገልግሎት ይሰጥ እንደነበር አውስተው፤ አዲስ አበባ ብቻ ተወሰኖ የነበረው የደንበኞችን ጥሪ የመቀበል አቅም በማሳደግ ሀገር አቀፍ ለማድረግ የሚያስችል የአሠራር ሥርዓት /ሲስተም/ መዘርጋቱን ነው የገለጹት። በ2018 በጀት በመጀመሪያ ሩብ ዓመት ሙሉ ለሙሉ ሥራ ላይ ይውላል ሲሉ ተናግረዋል፡፡ ሪፎርሙ ብዙ ለውጥ የሚያመጡ የማስፋፊያ ሥራዎች እየተሠሩ ነው የሚሉት ኃላፊዋ፤ የደንበኞች አገልግሎት 24 ሰዓት እየተሰጠ መሆኑን አመልክተዋል።

እንዲሁም ደምበኞች በማህበራዊ ሚዲያዎች በመጠቀም የሚፈልጉት አገልግሎት ሆነ ጥያቄ የሚጠይቁበት አሠራር እንዳለ ጠቅሰው፤ ይህንንም በዘርፉ የሰለጠነ ሰው ኃይል እንዲስተናገዱ እየተደረገ መሆኑንም ጠቁመዋል።

የፕሮሰስና ኳሊቲ ማኔጅመንት ኃላፊ አቶ እሱባለው ጤናው በበኩላቸው አገልግሎቱ ከደንበኞች አገልግሎት፣ ከኤሌክትሪክ ኃይል መቆራረጥ፣ ከቆጣሪ እና ከሠራተኞች ሥነምግባር ጋር የተያያዙ በርካታ ችግሮች እንዳሉበት ገልጸዋል።

አንዳንዶቹ ነባር የሆኑ በጣም ጊዜ የወሰዱ የቆዩ ችግሮች መሆናቸው ጠቅሰው፤ አንዳንዶቹ ደግሞ አሁን ላይ እየመጡ ያሉ ችግሮች ሲሆኑ የሪፎርም ሥራዎቹ ችግሮች ለመፍታት ያግዛሉ ነው ያሉት፡፡

በየጊዜው እያደገ የመጣ የኃይል ፍላጎት መኖሩን ኃላፊው ጠቁመው፤ ፍላጎት እያደገ መምጣቱ በነበረበት ያለውን አገልግሎት ላይ ተጨማሪ ጫና ማሳደሩን ይጠቅሳሉ፡፡

በሌላ በኩል የኤሌክትሪክ መስመሮች ረጅም ዓመት ያስቆጠሩ በመሆናቸው በመሠረተ ልማቶች ላይ ብዙ ሥራዎች መሥራት እንዳለባቸው ጠቅሰው፤ ለዚህም ፍላጎቱን የሚመጥን ከዘመኑ ጋር አብሮ የሚሄድ ዝግጅት እንዲኖር እየተደረገ መሆኑ ያመላክታሉ።

አገልግሎቱ አምስት ነጥብ አንድ ሚሊዮን የሚደርሱ ደንበኞች አሉት ያሉት ኃላፊው፤ አገልግሎቶች ደበኛው በሚጠብቀው ልክ ስለማይሰጡ ዘርፈ ብዙ ችግሮች እንዳሉ ይጠቁማሉ።

ኃላፊው እንደሚሉት፤ አገልግሎቱ ያሉበትን ችግሮች ለመፍታት የተሠሩ የሪፎርም ሥራዎች መካከል መጀመሪያ ወቅቱ በሚፈልገው መጠን መሠረተ ልማቶቹን ማዘመን ነው። ሁለተኛው ደንበኞች አገልግሎት ቅሬታ መቀነስና ርካታ መጨመር ነው።

ሶስተኛው ፋይናንስ በማሳደግ ሲሆን አራተኛው የሰው ኃይል ከዘመኑ ቴክኖሎጂ ጋር አብሮ እንዲሄድ ማድረግን ይጠይቃል፡፡

አገልግሎቱ በእኤአ 2030 ሀገሪቱ የምትፈጥረውን ኢኮኖሚ መሸከም የሚችል ኤሌክትሪክ ተደራሽነት የመፍጠር ተልዕኮ አንግቦ እየሠራ ነው ያሉት አቶ እሱባለው፤ በሪፎርም አገልግሎትን በማዘመን ኤሌክትሪክ ያገኙትን አካባቢዎች ያልተቋራረጠና አስተማማኝ የኤሌክትሪክ አገልግሎትን እንዲያገኙ ለማድረግ እየሠራ ነው ብለዋል፡፡

በሀገሪቱ ካላት ሕዝብ የኤሌክትሪክ ተጠቃሚነት 63 በመቶ ያህል መሆኑን በቅርብ የተደረጉ ጥናቶች ያመላክታሉ ያሉት አቶ እሱባለው፤ 37 በመቶ የሚሆኑት ሕዝብ ኤሌክትሪክ የሚለው ሰምቶ ሆነ ተጠቅሞ የማያውቁ ናቸው ሲሉ አመልክተዋል፡፡

ወርቅነሽ ደምሰው

አዲስ ዘመን ቅዳሜ ሰኔ 14 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You