
አዲስ አበባ፦ በዲጂታል ኢትዮጵያ 2030 ስትራቴጂክ እቅድ መሠረት ሁሉም የመንግሥት ተቋማት አገልግሎቶች በበይነ መረብ (ዲጂታል) አማካኝነት እንደሚሰጡ የኢኖቬሽን ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር አስታወቀ።
በሚኒስቴሩ የዲጂታል ኢኮኖሚ ልማት ዘርፍ መሪ ሥራ አስፈፃሚ አቶ ስዩም መንገሻ ለአዲስ ዘመን ጋዜጣ እንደገለጹት፤ በግብርና፣ በአምራች ኢንዱስትሪው (በማኑፋክቸሪንግ)፣ በቱሪዝም እና በአይ.ሲ.ቲ ዘርፍ የተከናወኑት የዲጂታል ኢትዮጵያ 2025 ሥራዎች አመርቂ ውጤት አስመዝግበዋል። ይህንን ለማስቀጠል ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ የዲጂታል ኢትዮጵያ 2030 ስትራቴጂክ እቅድን የማዘጋጀት ሥራ እየተሠራ ነው። በዚህም ሁሉም የመንግሥት ተቋማት አገልግሎቶች ዲጂታል ለማድረግ ታቅዷል። ይህም ባለጉዳይ የመንግሥት አገልግሎቶችን የትም ሆኖ ጉዳዩን ማስፈጸም እንዲችል ያደርገዋል ብለዋል።
በ2030 ስትራቴጂክ እቅዱ የቢሮክራሲ እና የመልካም አስተዳደር ችግሮች የሚፈቱበት ሥርዓት እንደሚዘጋጅ ጠቁመው፤ ለዚህም የፋይዳ መታወቂያ ምቹ መደላድልን እንደሚፈጥር ተናግረዋል። ዲጂታል ኢትዮጵያ 2030 ስትራቴጅክ እቅድ የመንግሥት ተቋማትን ብቻ ሳይሆን የግሉ ዘርፍንም ያማከለ መሆኑን አመልክተዋል።
የቴሌኮም መሠረተ ልማት የግሉን ዘርፍ ተጠቃሚነት ከማሳደጉም በላይ ለበርካታ የሥራ እድል የመፍጠር አቅም አለው ያሉት አቶ ስዩም፤ ዲጂታል ኢትዮጵያ 2030 የኤሌክትሮኒክ ንግድን መሠረት በማድረግ የሀገር ውስጥ ምርቶች ግብይትን ይበልጥ የማሳደግ ሥራ እንደሚሠራ ገልጸዋል።
የስትራቴጂክ እቅድ ተዘጋጅቶ ባይጠናቀቅም የወደፊት የዓለም ሁኔታ መሠረት ባደረገ መልኩ መልኩ እቅዱን የማዘጋጀት ሥራ እየተሠራ እንደሆነ የጠቆሙት አቶ ስዩም፤ በተለይ በዳታ እና በሰው ሠራሽ አስተውሎት ላይ ትኩረት እንደሚደረግ ተናግረዋል።
ኢትዮጵያ በ2030 በሰው ሠራሽ አስተውሎት ረገድ ለማሳካት ያሰበችውን ግብ እውን ለማድረግ ፖሊሲን የመፈተሽ እና የአቅም ውስንነትን የመሙላት ሥራ እንደሚሠራ ጠቁመው፤ በዚህም ኢትዮጵያ የራሷ የሆነ ሰው ሠራሽ አስተውሎት እንዲኖራት ለማድረግ ታስቧል ብለዋል።
ከዚህ ጋር በተያያዘ የሰው ሠራሽ አስተውሎት መዋቅር የማዘጋጀት ሥራ ይሠራል። ይህም ከዓለም ሀገራት ተወዳዳሪ ለመሆን እና ራስን ለወደፊት ፈተናዎች ለማዘጋጀት እንደሚረዳ የተናገሩት አቶ ስዩም፤ በ2030 ዲጂታል ስትራቴጂክ እቅዱም ኢትዮጵያ “የዳታ ባለቤትነትን” ማረጋገጥ እንድትችል ለማድረግ ታቅዷል ነው ያሉት።
ለዚህም አይ.ሲ.ቲ ፓርክ ላይ ትላልቅ ዳታ ማዕከሎች (ሴንተሮች) የመዘርጋት እንዲሁም የማይቆራረጥ ኤሌክትሪክ ሃይል እንዲኖር ምቹ መደላድል እየተፈጠረ መሆኑን የገለጹት አቶ ስዩም፤ በዲጂታል ኢትዮጵያ 2025 የተሠሩ የቴሌኮም መሠረተ ልማቶች ለ2030 እቅዱ ምቹ ሥነ ምህዳር መፍጠር መቻሉን ተናግረዋል።
በሳሙኤል ወንደሰን
አዲስ ዘመን ዓርብ ሰኔ 13 ቀን 2017 ዓ.ም