ልዩ የምርመራ ዘዴ ዓለም አቀፍ የምርመራ መስፈርትን የተከተለ መሆኑ ተገለጸ

አዲስ አበባ፡- ልዩ የምርመራ ዘዴ ሕገ ወጥ የገንዘብ፣ የሰዎች፣ የአደንዛዥ እጽ እና የጦር መሣሪያ ዝውውርን በመቆጣጠር የሚደርሱ ዓለም አቀፍ ኢኮኖሚያዊና ሠብዓዊ ቀውሶችን ለመቆጣጠር ሀገራት የሚከተሉትን የምርመራ መስፈርት የተከተለ መሆኑ ተገለጸ።

በወንጀል ድርጊት የተገኘ ንብረት ወይም ገንዘብን ሕጋዊ አስመስሎ ማቅረብ እና ሽብርተኝነትን በገንዘብ መርዳትን ለመቆጣጠር የወጣውን ማሻሻያ አዋጅ አዋጅ 1387 /2017 አስመልክቶ በማህበራዊ ሚዲያ የሚሰራጩ የተዛቡ ትርጉሞችን ለማጥራት ፍትህ ሚኒስቴር እና የፋይናንስ ደህንነት አገልግሎት በትናንትናው እለት የጋራ መግለጫ ሰጥተዋል።

በወንጀል ድርጊት የተገኘን ንብረት ወይም ገንዘብ ሕጋዊ አስመስሎ ማቅረብ እና ሽብርተኝነትን በገንዘብ መርዳትን ለመቆጣጠርና ለመከላከል የወጣውን አዋጅ ቁጥር 780/2005ን ለማሻሻል የወጣው አዋጅ ቁጥር 1387/2017 ሰኔ 10 ቀን 2017 ዓ.ም በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት መጽደቁ ይታወቃል።

የፋይናንስ ደህንነት አገልግሎት ዋና ዳይሬክተር አቶ ሙሉቀን አማረ እንደተናገሩት ፤ ልዩ የምርመራ ዘዴ ከዚህ ቀደምም በአዋጅ ቁጥር 780/ 2005 መሠረት ለ12 ዓመታት ሲተገበር የቆየ ነው። ሀገራችን በወንጀል ድርጊት የተገኘን ገንዘብ ወይም ንብረት ሕጋዊ አስመስሎ ማቅረብና ሽብርተኝነትን በገንዘብ የመርዳት ወንጀልን ለመቆጣጠር በደንብ ቁጥር 171/2002 የፋይናንስ ደህንነት አገልግሎት እንዲቋቋም ተደርጎ በ2004 ዓ.ም ተቋሙ ወደ ሥራ ገብቷል። ተቋሙን ለማጠናከር በድጋሚ በደንብ ቁጥር 490 /2014 ማቋቋም ተችሏል።

ተቋሙ በፊትም ይሁን በድጋሚ ሲቋቋም ዋናው ተልእኮው ሀገራችን የዓለምአቀፍ የፋይናንስ ድርጊት ግብረ ሃይል ምክረ ሃሳቦችን መተግበር ከሚጠበቅባቸው ከ200 በላይ የዓለም ሀገራት አንዷ መሆኑን ታሳቢ በማድረግ መሆኑን ገልጸዋል። እነዚህ አባል ሀገራት ሽብርተኝነትን በገንዘብ መርዳትን ለመከላከል የሚያስችሉ 40 ምክረ ሃሳቦችን እንደሚተገብሩ ጠቅሰው፤ ምክረ ሃሳቦቹ እየተሻሻሉ መሄዳቸውን ተከትሎ አዲስ ሕግ ማውጣት አስፈልጓል ብለዋል።

እንደ አቶ ሙሉቀን ገለጻ፤ የወንጀል ባህሪዎች ተለዋዋጭ መሆናቸውን ተከትሎ ወንጀሉን ሊመጥን የሚችል የሕግ ማሕቀፍ አስፈልጓል። በወንጀል ድርጊት የተገኘ ንብረት ወይም ገንዘብን ሕጋዊ አስመስሎ ማቅረብ እና ሽብርተኝነትን በገንዘብ መርዳትን በተመለከተ አመንጪ ወንጀሎች የተባሉትን አዲሱ ሕግ በዝርዝር ያስቀመጠ ስለመሆኑም ጠቅሰዋል። በዚህም የዓለም ሕግ በሚፈቅደው መሠረት 21 ወንጀሎችን በዝርዝር ማስቀመጥ ተችሏል ነው ያሉት። ይህ አሠራር የተዘረፈና ያለአግባብ በወንጀል የተገኘውን ንብረት እስከማስመለስ የሚደርስ እንደሆነም ተናግረዋል።

የሕግ ማሕቀፉ ኢትዮጵያ ፈርማ ከተቀበለቻቸው ዓለም አቀፍ ሕጎች ጋር የተጣጣመ እንዲሆን የተሻሻለ መሆኑን አስረድተዋል።

ከዚሁ ጋር ተያይዞ ቀደም ሲል በሽፋን ስር የሚደረግ ምርመራን በተመለከተ ምርመራውን የሚያደርገው አካል፤ ከሕግ ነጻ የሚሆንበትና ተጠያቂ የማይሆንበት ሁኔታ እንደነበር ተናግረዋል። በአዋጅ ቁጥር 780/2005  አንቀጽ 26 በተቀመጠው መሠረት በሽፋን ስር የሚደረግ ምርመራን በተመለከተ መርማሪው አካል የሕግ ሽፋን ማግኘት አለበት ምክንያቱም መረጃን ለማግኘት ተመሳስሎ የሚገባ አካል ከመሆኑ አንጻር የበፊቱ ሕግ እንደወንጀል ፈጻሚም ያደርገውና ግን ደግሞ በወንጀል አይጠይቅም ይላል ሲሉ አስረድተዋል።

ሕጉ የግልጽነት ችግር ስለነበረው መርማሪው ወንጀል የሚፈጽመው መረጃ ለማምጣት በሽፋን ስር የሚያደርግ ምርመራ ለመፈጸም ከሚፈጽመው ወንጀል ተጠያቂ መሆን የለበትም የሚል ነው። በበፊቱ ሕግ ላይ ተጠያቂ አይሆንም የሚለው በጥቅል እንደነበር ዋና ዳይሬክተሩ ጠቅሰው፤ በዚህ ማሻሻያ ሕግ ላይ ግን ምንም እንኳን በሽፋን ስም የሚደረግ ምርመራ እያከናወነ ቢሆንም የሚፈጽማቸው ድርጊቶች ከግድያ መለስ የሆኑ መሆን እንዳለበት ያስቀምጣል ብለዋል።

በፍትህ ሚኒስቴር የሕግ ጥናት ማርቀቅ ፣ ማረምና ማጠቃለል ዳይሬክተር ጀነራል አቶ አዲስ ጌትነት በበኩላቸው እንደተናገሩት ፤ልዩ የምርመራ ዘዴ ሲባል ከመደበኛ ምርመራ የተለየና በፍርድ ቤት ክትትልና ትእዛዝ የሚከናወን ነው።

ወንጀሎች ድንበር ተሻጋሪና ዓለምአቀፍ እየሆኑ ነው ያሉት ዳይሬክተር ጀነራሉ፤ በወንጀል ድርጊት የተገኘ ንብረት ወይም ገንዘብን ሕጋዊ አስመስሎ ማቅረብ እና ሽብርተኝነትን በገንዘብ መርዳት ወንጀል ዓለም አቀፍ ባሕሪ ያለው እንደሆነ ገልጸዋል።

ድንበር ተሻጋሪና የተደራጀ ወንጀልን ከሀገራት ጋር ትብብር በመፍጠር ወንጀሉን ለመከላከል የሚደረጉ ጥረቶች እንዳሉ ጠቅሰዋል።

አዋጅ 1387 /2017 ከዓለም ስታንዳርድ እና መርህ ጋር የተጣጣመ ሆኖ በሽፋን ላይ የተመሠረተ ምርመራን ፍርድ ቤቱ አሳማኝ ሆኖ ሲያገኝ ሊፈቅድ ይችላል። ስለሆነም በሽፋን ስር በሚደረግ ምርመራ ተመሳስሎ መግባት ወይም ሰርጎ መግባት ስለሚኖር ተልእኮው የሀገርና የሕዝብን ጥቅም ማስከበር በመሆኑ መርማሪው ከወንጀለኞች ጋር ተመሳስሎ ወንጀል ሊፈጽም ይችላል። ስለሆነም መርማሪው በዘፈቀደ ሳይሆን በተቀመጠው አግባብ ከግድያ መለስ ተግባራትን ቢፈጽም ተጠያቂ እንደማያደርገው አስረድተዋል።

በኢያሱ መሰለ

አዲስ ዘመን ዓርብ ሰኔ 13 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You