የኢራን ባለሥልጣን አሜሪካንን አስጠነቀቁ

እስራኤል በኢራን ላይ በምትፈፅመው ጥቃት አሜሪካ እጇን የምታስገባ ከሆነ በአጠቃላይ በቀጣናው ገሃነም እንደሚፈጠር የኢራን ምክትል የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ተናገሩ። ”ይህ የአሜሪካ ጦርነት አይደለም” ያሉት ሳኢድ ኻቲብዛዴህ፣ የአሜሪካው ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ በዚህ ከተሳተፉ በማይመለከታቸው ጦርነት ውስጥ የገቡ ፕሬዚዳንት ሆነው ሁል ጊዜም ይታወሳሉ ብለዋል።

ምክትል የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ ጨምረውም የአሜሪካ ጣልቃ ገብነት ግጭቱን ወደ “አረንቋነት” እንደሚለውጠው፣ ቁጣው ተባብሶ እንደሚቀጥል እና የሚፈፀመውን ጭካኔ የተሞላበት ጥቃት ማብቂያ እንደሚያዘገየው ተናግረዋል። ምክትል የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ ይህን ያሉት በኢራን የሚሳኤል ጥቃት በደቡባዊ እስራኤል የሚገኘው ሶሮካ ሆስፒታል ከተመታ በኋላ ነው።

የኢራን የመንግሥት መገናኛ ብዙኃን ጥቃቱ ሆስፒታሉን ሳይሆን ከሆስፒታሉ አጠገብ የሚገኝ ወታደራዊ ሥፍራን ዒላማ እንዳደረገ ዘግበዋል። የእስራኤል የጤና ሚኒስቴር በሶሮካ ሆስፒታል ላይ በተፈፀመው ጥቃት 71 ሰዎች መጎዳታቸውን ገልጿል።

ይህ በእንዲህ እንዳለ የእስራኤል ጦር ናታንዝ ማዕከልን ጨምሮ የኢራን የኒውክሌር ሥፍራዎች ላይ ጥቃት መፈፀሙን አስታውቋል። ኢራን በእስራኤል ጥቃት ስለደረሰው ጉዳት እስካሁን የሰጠችው መረጃ የለም። አሁን ላይ ጥቃቱ የተፈፀመው ሐሙስ ዕለት ዋይት ሐውስ አሜሪካ በግጭቱ ውስጥ በቀጥታ ስለሚኖራት ተሳትፎ ትራምፕ በሚቀጥሉት ሁለት ሳምንታት ጊዜ ውስጥ ውሳኔ እንደሚሰጡ ካስታወቀ በኋላ ነው።

ኻቲብዛዴህ ሲናገሩ “በእርግጥ ዲፕሎማሲ የመጀመሪያው አማራጭ ነው፤ ነገር ግን ጥቃቱ የሚቀጥል ከሆነ ምንም ዓይነት ድርድር አንጀምርም” ብለዋል። ኢራን በእስራኤል ላይ የምትፈፅመውን ጥቃትም “በተባበሩት መንግሥታት ውል አንቀፅ 51 መሠረት ራስን መከላከል” እንደሆነ ምክትል የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ በተደጋጋሚ አስረድተዋል። እስራኤል ከሰባት ቀናት በፊት በኢራን የኒውክሌር ማዕከላት ላይ ጥቃት ስትፈፅም፣ ከፍተኛ የጦር አዛዦችን እና የኒውክሌር ተመራማሪዎችን ስትገድል በዲፕሎማሲያዊ ንግግር ውስጥ እንደነበሩም ተናግረዋል።

ምክትል የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ ግጭቱን “ምንም መነሻ የሌለው” እና “አላስፈላጊ” ብለውታል። ትራምፕ ኢራን የኒውክሌር ስምምነቱን ብትቀበል ኖሮ ግጭቱ ሊከሰት አይችልም ነበር ሲሉ በተደጋጋሚ በሰጡት አስተያየት ላይም ምክትል የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ ምላሽ ሲሰጡ፣ “እስራኤል ጥቃት ፈፅማ ሂደቱን እስከምታደናቅፈው ድረስ እየተነጋገሩ እንደነበር ገልጸዋል።

“በሙስካት ስድስተኛ ዙር የኒውክሌር ንግግር ለማድረግ እያቀድን ነበር። ለመስማማትም ጫፍ ላይ ደርሰን ነበር። ይህንን ከሌላ አካል ይልቅ ፕሬዚዳንት ትራምፕ ራሳቸው በደንብ ያውቃሉ” ብለዋል። ”ግራ አጋቢ” እና “እርስ በርስ የሚጋጭ” ያሉትን የትራምፕን የማህበራዊ ሚዲያ መልዕክቶች እና ቃለ ምልልሶችንም ምክትል ሚኒስትሩ ተችተዋል።

የአሜሪካ ልዩ መልዕከተኛ ስቲቭ ዊትኮፍ እና የኢራን የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አባስ አራቅቺ አርብ ዕለት ለግጭቱ ዲፕሎማሲያዊ አማራጭ ለመፈለግ በተደጋጋሚ በስልክ ተነጋግረው እንደነበር ሮይተርስ ዘግቧል። ለዜና ወኪሉ የተናገሩ ሦስት የዲፕሎማቲክ ምንጮች እንዳሉት አራቅቺ እስራኤል ጥቃቱን ካላቆመች ቴህራን ወደ ድርድር እንደማትመለስ ተናግረዋል።

እስራኤል ኢራን ለኃይል ማመንጫ ወይም ለኒውክሌር ቦምብ የሚያገለግለውን የበለጸገ ዩራኒየም ወደ ጦር መሳሪያነት ለመቀየር በቅርቡ እርምጃ ወስዳለች ስትል ከሳለች። ኢራን ግን የኒውክሌር መርሃ ግብሯ ሙሉ በሙሉ ሰላማዊ እንደሆነ በተደጋጋሚ ስትገልጽ ቆይታለች። ዓርብ ዕለት የተባበሩት መንግሥታት የኒውክሌር ተቆጣጣሪ የሆነው ዓለም አቀፉ የአቶሚክ ኢነርጂ ኤጀንሲ የኢራን ዩራኒየም 60 በመቶ ያህል እንደበለጸገ ገልጿል። ይህም ኒውክሌር ቦምብ ለመሥራት አሊያም 90 በመቶ ለመድረስ ጥቂት ቴክኒካዊ ርምጃዎች ናቸው የሚቀሩት ብሏል።

ምክትል የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ ግን “ ይህ ምንም ትርጉም የማይሰጥ ነገር ነው። በሐሰተኛ መረጃ እና ፍላጎት ላይ ተመስርቶ ጦርነት አይጀመርም” ብለዋል። “ኒውክሌር ቦምብ ብንፈልግ ኖሮ ከዚህ በፊት ሊኖረን ይችል ነበር” ሲሉም አክለዋል። ኢራን ሰላማዊ የሆኑ የኒውክሌር መርሃ ግብሯን ወደ የጦር መሣሪያ ለመቀየር የሚያስችል መርሃ ግብር አላወጣችም ሲሉም የቀረበውን ክስ አስተባብለዋል።

ዓለም አቀፉ አቶሚክ ኢነርጂ ኤጀንሲ ዋና ዳይሬክተር ራፋኤል ግሮሲም፣ምንም ዓይነት ሁኔታ ቢፈጠርም በሰዎች እና በአካባቢ ላይ ጉዳት ሊያስከትል ስለሚችል በኒውክሌር ማዕከላት ላይ በፍፁም ጥቃት መፈፀም እንደሌለበት አሳስበዋል ሲል ቢቢሲ ዘግቧል።

አዲስ ዘመን ቅዳሜ ሰኔ 14 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You