
አዲስ አበባ፦ በኦሮሚያ ክልል የግብርናውን ዘርፍ በቴክኖሎጂ በመደገፍ የአርሶ አደሩን ሕይወት ለማሻሻል እየተሠራ መሆኑን የክልሉ ግብርና ቢሮ አስታወቀ።
ኢትዮ ቴሌኮም እና የኦሮሚያ ግብርና ቢሮ የተቀናጀ የግብርና እሴት ሠንሠለት መረጃ መፍትሔ ለማቅረብ የሚያስችል ስምምነት በትናንትናው እለት ተፈራርመዋል።
የኦሮሚያ ግብርና ቢሮ ኃላፊ ጌቱ ገመቹ በወቅቱ እንደገለጹት፤ የኦሮሚያ ግብርና ቢሮ ምርታማነትን፣ ቅልጥፍናን፣ ጥራትን፣ ትርፋማነትን እና የገበያ ትስስርን በዘላቂነት ለማዘመን እየሠራ ነው። ለዚህም ቢሮው ከኢትዮ ቴሌኮም ጋር የተቀናጀ ግብርና እሴት ሠንሠለት ለማቅረብ የሚያስችል ስምምነት ተፈራርሟል።
ይህም ምርትን በማሻሻል፣ ሀብትን በብቃት ማስተዳደር፣ ተባዮችንና በሽታዎችን በመቆጣጠር፣ የገበያ ተደራሽነትን በመደገፍ፣ ዘላቂ ልማትን በማጎልበት እንዲሁም በመረጃ ላይ የተመሠረተ ፈጠራን በማምጣት የክልሉን የግብርና እሴት ሠንሠለት ወደ ላቀ ደረጃ ለማድረስ ያስችላል ብለዋል።
የክልሉ ግብርናን በቴክኖሎጂ በመደገፍ የአርሶ አደሩን ሕይወት ለማሻሻል እየተሠራ ነው ያሉት አቶ ጌቱ፤ ቢሮው የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ እና የኢኮኖሚ እድገትን ለማፋጠን በሚደረገው ጥረት ውስጥ ቁልፍ ሚና እየተጫወተ እንደሚገኝ ተናግረዋል።
በባህላዊ የግብርና አሠራር እየጨመረ የመጣውን የሕዝብ ቁጥር ለመመገብና በዓለም አቀፍ ገበያ ተወዳዳሪ ለመሆን የሚያስችል አይደለም ያሉት ኃላፊው፤ ይህም ለዘመናት ተግባራዊ ሲደረግ የቆየ በመሆኑ ምርታማነት፣ የሀብት አጠቃቀም እና የገበያ ሠንሠለቱ ላይ አሉታዊ ተፅዕኖ ሲያሳድር መቆየቱን ገልጸዋል።
አሁን ግን በግብርናው ዘርፍ የተሰማሩ ሴክተሮችን፣ የግብርና ግብዓት አቅራቢዎችን፣ ኢንተርፕራይዞችን፣ አከፋፋዮችን እና ቸርቻሪዎችን እንዲሁም የመንግሥትን እና የግሉን ዘርፍ ጥረቶች በማዋሓድ የተቀናጀ የግብርና እሴት ሠንሠለት መረጃ መፍትሔ ለማምጣት ትኩረት ተደርጓል ብለዋል።
ይህም በኦሮሚያ ግብርና በዲጂታል የተቀናጀ፣ ዘላቂ እና ቀልጣፋ የግብርና እሴት ሠንሠለት ለመፍጠር ከፍተኛ ፋይዳ እንደሚኖረው ተናግረዋል።
የኢትዮ ቴሌኮም ዋና ሥራ አስፈጻሚ ፍሬሕይወት ታምሩ በበኩላቸው፤ የሀገራችንን ኢኮኖሚያዊ እና ማኅበራዊ ሥነምሕዳርን የሚቀይሩ፣ ተቋማዊ አሠራርን የሚያዘምኑ እና የዜጎቻችንን የዕለት ተዕለት የአኗኗር ዘይቤን የሚያሻሽሉ ዘመኑ ያፈራቸውን ዘመናዊ ቴክኖሎጂዎችን እና ዲጂታል መፍትሔዎችን እያቀረበ ይገኛል ብለዋል።
በተለይም የዲጂታል መፍትሔዎችን ተደራሽነት በማስፋት የፋይናንስ አካታችነትን እና የሀገራችን ሁለንተናዊ እድገት ለማረጋገጥ የተለያዩ ፕሮጀክቶችን በማከናወን የዲጂታል ኢትዮጵያን ጉዞ በማፋጠን ረገድ ቁልፍ ሚና እየተጫወተ እንደሚገኝ ተናግረዋል።
ኢትዮ ቴሌኮም ለኦሮሚያ ግብርና ቢሮ የተቀናጀ የግብርና እሴት ሠንሠለት መረጃ መፍትሔ ለማቅረብ መስማማቱን አንስተው፤ ይህም በቴሌ ክላውድ ላይ እንደተመሠረተ እና የክልሉን የተቀናጀ የግብርና እሴት ሠንሠለትን በማዘመን ሁሉንም የግብርና አሠራር ሂደቶችን እንደሚሸፍን ገልጸዋል።
በዚህም ከግብዓት አቅርቦት ጀምሮ የምርት፣ የግብይትና ስርጭት ፍላጎት ትንተና እንዲሁም የዋጋ ክትትል ማድረግ እንደሚቻል ጠቁመው፤ ይህም የመረጃ አሰባሰብና አስተዳደርን በማሳለጥ ለክልሉ ግብርና እሴት ሠንሠለት ማዕከላዊ የመረጃ ማከማቻ እና ትንታኔ ማዕከል ሆኖ የሚያገለግል ይሆናል ብለዋል።
በሳሙኤል ወንደሰን
አዲስ ዘመን ማክሰኞ ሰኔ 10 ቀን 2017 ዓ.ም