የሰው ልጅ የሕይወት ውጣ ወረድ የተለያየ ነው። ሁሉም የሕይወት መስመሩ በሚወስደው ሃዲድ ይጓዛል።ይወድቃል ይነሳል።በዓለማችን ሆነ በሀገራችን በርካታ ሰዎች የዕለት ጉርሳቸውን ሸፍነው ከቻሉም ሌሎችን አግዘው ይኖራሉ። ይህ የሕይወት ኡደት ነው።በዚህ ኡደት መጓዝ ግን እንደየ ሰው ተፈጥሮና ትጋት ስኬታማነት ላይ ልዩነት አለ። እንዳንዱ የተሟላ አካል ይዞ መንገድ ላይ ለሥራ ሳይሆን ለልመና ይወጣል።ሌላው ደግሞ በተፈጥሮ ሆነ በሌላ ምክንያት ያጋጠመው አካል ጉዳት ሳይበግረው ከራሱ አልፎ ሌሎችንም ያግዛል፤ ይረዳል። የዛሬዋ የሲራራ አምድ እንግዳችንም አካል ጉዳተኝነቷ ያልበገራት፣ ትጉና ጠንካራ ሴት ናት። እታፈራሁ አየለ ትባላለች።
እታፈራሁ አየለ አካል ጉዳቷ እግሯ ላይ ቢሆንም ቤት መቀመጥ ወይም የሰው እጅ ማየትን አልፈቀደችም። ሕይወትን ለማሸነፍ ደፋ ቀና እያለች ራሷንና ቤተሰቧን በማገዝ ላይ የምትገኝ የጥንካሬ ተምሳሌት ናት። በሐኪም የታዘዙ የዐይን መነፅር ሥራዎች ላይ የተሰማራች ሲሆን፤ ከሃኪም የሚመጣን የህክምና ወረቀቶችን በማየት መነፅሮችን በማዘጋጀት ለደንበኞች ትሸጣለች።
የመነፅር ሥራዎችን የተማረችው የምስራች ዕደጥበብ ማሰልጠኛና ማቋቋሚያ ማዕከል በሚባል ግብረ ሰናይ ድርጅት ነው። ማዕከሉ ብዙ ጊዜ አካል ጉዳተኞችን በተለያየ ሁኔታ ወይም ትምህርትም ሳይሳካ ሲቀር ለአካል ጉዳተኞች ልዩ ልዩ ሥልጠናዎችን በመስጠት ራሳቸውን ለመቻል የሚያደርጉትን ጥረት የሚደግፍ ድርጅት ነው። እታፈራሁም ከዚህ ድርጅት ያገኘችውን ሙያ በመጠቀም የምትታትር ናት።
እታፈራሁ 12ኛ ክፍልን ብታጠናቅቅም ከፍተኛ ትምህርት የሚያስገባ ውጤት ባይመጣላትም ተስፋ አልቆረጠችም። ራሷን በሙያ አብቅታ የሰው እጅ ከማየት ለመላቀቅ ጥረቷን ጀመረች። በየምስራች ዕደጥበብ ማሰልጠኛና ማቋቋሚያ ማዕከልም ለሁለት ዓመት ሥልጠናዋን ወስዳለች።
«በወቅቱ 12ኛ ክፍል ጨርሼ ውጤት አልመጣልኝም ነበር። ምን ልሥራ እያልኩ በማስብበት ሁኔታ አንድ የጓደኛዬ ባለቤት ወደእዛ አካባቢ ሰው ለመጠየቅ ሲመጣ ‹ለምን ሥልጠና አትገቢም ጠይቂ እስቲ› አለኝ» ትላለች። እርሷም ይህ መረጃ በዋዛ ማሳለፍ አልፈለገችም። ወዲያውኑ ሄዳ ተመዘገበች። የመግቢያ ፈተና ተፈትና እንዳለፈች ተደውሎ ተነገራት። በመነፅር ክፍል ውስጥም ሥልጠና ጀመረች። ሁለት ዓመት የሚፈጅ ሥልጠና በትጋት ተከታትላ ራሷን የመቻል ጉዞ ጀመረች። ማዕከሉ ለሰልጣኞች የማቋቋሚያ ገንዘብ የሚሰጥ ቢሆንም፤ እሷ ግን በማዕከሉ ውስጥ የመስራት ዕድል አግኝታ ሕይወቷን መምራት ጀመረች።
በማዕከሉ በመነፅር ሽያጭ ክፍል እንግዶችን በማስተናገድ ለ17 ዓመታት ያህል ሠርታለች። ሁለት ዓመት ሥልጠና ወስዳ 17 ዓመት በሥራ ላይ በመቆየቷ ሥራውን እንድትለምደውና ከሥራው ጋር እንድትዋሃድ ጠቅሟታል።
«በማዕከሉ ውስጥ ከቆየሁ የራሴን ነገር አሰብኩኝ። ይህንን ሥራ ለምን ግን ራሴ አልሠራም ብዬ አሰበኩ። ለመሥራትም ወሰንኩኝ። አንዳንድ ነገሮች ተመቻቹልኝ። በተመቻቸልኝ መሠረት ሥራውን ጀመርኩ» ስትልም ወደዚህ የደረሰችበትን ምክንያት ታስረዳለች።
«በማዕከሉ በሠራተኝነት ስለተቀጠርኩ ከሥልጠና በኋላ የሚሰጠውን የመቋቋሚያ ገንዘብ አልወሰድኩም። ድርጅቱ ውስጥ እየሠራሁ በወር 10 ብር እያዋጣን የቤት ማኅበር መሥርተን ነበር። የሚገርመው ነገር 10 ብር ቤት አይሠራም። ግን ለኔ መሠረት ሆነችኝ» ስትል አሁን ለአለችበት ደረጃ መነሻ የሆናት አጋጣሚ ታስታውሳለች።
በሥልጠና ላይ እያሉ ጀምሮ በወር አስር ብር ይሰበስቡ ነበር። የዚህ አላማ ቤት ለመሥራት ነው። ምንም እንኳ አስር ብር ተቆጥቦ ቤት ለመስራት ከባድ ቢሆንም አቶ አማረ በሚባሉ የድርጅቱ መሥራች አማካኝነት እና በድርጅቱ ኃላፊዎች በሆኑ ፈረንጆች ድጋፍ ቤት ተሠራላቸው።
የእሱ ገንዘብ እንደ እርሾ ሆኖ ትልቁን ነገር በድርጅቱ በተለየ ሁኔታ ገንዘብ የሚገኘበትን በማመቻቸት ድጋፍ ተደርጎላቸዋል። ድጋፍ የተደረገላቸው 21 ሰዎች እንደነበሩም ታስታውሳለች። ከእነዚህ ውስጥ ግን አራት የሚሆኑት መቆጠብ ሲያቋርጡ፤ ለተቀሩት ቤት ተሠራላቸው። እታፈራሁም የዚሁ ተጠቃሚ ሆነች።
እታፈራሁ ያቺን ቤት ሸጠቻች። የዐይን መነፅር መሸጫውንም ከፈተች። ሥራዋን የምትሠራው ከቤተሰቦቿ ጋር ሆና ነው። ሙያውንም ለእህቷና ለልጇ አስተምራለች። በመሆኑም ከራሷ አልፋ ሙያውን ለሌሎች በማስተላለፍ አይበገሬነቷን አስመስክራለች። ሥራውን በዋናነት ራሷ ትሰራለች። እህቷና ልጇም አጠገቧ ሆነው ያግዟታል።
«ማኅበረሰቡ አካል ጉዳተኞችን የግድ መደገፍ አለበት» የምትለው እታፈራሁ፤ «እኛም የማኅበረሰቡ አባል ነን» ትላለች። ይህንን የዐይን መነፅር ሽያጭ ሥራ ቤተሰቦቼ ባያበረታቱኝ ድርጅቱ ባይደግፈኝ ለዚህ ሙያ መብቃት አልችልም ነበር። ሌሎች ሙያዎች አሉ። በሠለጠንኩበት ሙያ ግን እጅግ በጣም ጥሩ ሙያ ነው። እኛ ሀገር ውስጥ እጅግ ያልተሠራበት ሙያ ነው። ይሄን ሙያ ማግኘት ለእኔ በተለይ ጠቅሞኛል» በማለት ሙያው ራሷን ለመቻል እንደጠቀማት ትገልጻለች።
አሁን ላለችበት ደረጃ እንድትደርስ የማዕከሉ ሚና ከፍተኛ መሆኑን የምትገልጸው እታፈራሁ፣ በተለይ «በራስ መተማመን እንዲኖረን አድርጓል» ትላለች። «እኔ ብቻ አካል ጉዳተኛ የሆንኩ መስሎኝ የበታችነት ስሜት ይሰማኝ ነበር። ሥልጠና ቦታ ስመጣ ግን ብዙ ልጆችን አየሁ። ተፅዕኖ ያሳድርብኝ የነበረው ስሜት ለቀቀኝ» ስትል በራስ ለመተማመን መሠረቷ ማዕከሉ መሆኑን ታስረዳለች።
«አካል ጉዳተኝነት ማለት የሰው ጥገኛ መሆን ማለት አይደለም» የምትለው እታፈራሁ፣ መሥራት ይቻላል፣ ራሱን መቻል ሰው መሆን ይችላል። በትልቅ ደረጃ ላይ መድረስ ይችላል። ዋናው ነገር በጣም ደስተኛ መሆንና በራስ መተማመን ነው ትላለች።
«የሚገረመው ነገር አሁን መነፅሮች የሚገጥምልኝ ልጅም የምስራች ዕደጥበብ ማሰልጠኛና ማቋቋያ ማዕከል ሠልጣኝ ነበር። ማዕከሉ አቋቁሞ ራሱን እንዲችል አድርገውታል። ከእኔ ጋር ነው የሚሠራው» ትላለች። ከራሷ አልፋም ለሌሎች መትረፏ ያስደስታታል።
«ከተለያዩ ዐይን ሕክምና ቦታዎች መነጽር ታዞላቸው የዐይን መነፅር ፍለጋ ይመጣሉ። የመነፅሩን ዓይነት የሚገልፅ ትዕዛዝ አለ። በሐኪሙ ወረቀት ትዕዛዝ መሠረት ዐይተን የታዘዘው ምንድነው? የሚያስፈልገው ምንድነው? በሚል በጥንቃቄ ልክ እንደ መድኃኒት የሐኪም ወረቀት ታይቶ እንደሚገዛው ሁሉ አስፈላጊውን አሟልተን በጥንቃቄ እንሸጣለን። ለገበያ ብለን የማይሆን መነፅር አንሸጥም። የታዘዘውን ጠብቀን ከታዘዘላቸው ውጪ ሳናደርግ እንሠራላቸዋለን» በዚህም ከደንበኞች እምነት አግኝተንበታል ትላለች።
የዐይን መነፅር መሸጫውም ሆነ የመኖሪያ ቤቴ መነሻ የምስራች ዕደጥበብ ማሰልጠኛና ማቋቋሚያ መሆኑን የምትገልጸው እታፈራው፤ ቤቷን ከሸጠች በኋላ እንደገና ጥገኛ ሆኜ መሆን ስላልፈለገች ቤት ገዛች። በተረፈውም ሥራ ጀመረችበት።
ሥራውን ስትጀምር የሚያስፈልጓት ዕቃዎች የሚገኙበትን ቦታ ፈልጋ ገዛች። ብዙ ሌንሶች የምትገዛው ከምስራች ዕደጥበብ ማሰልጠኛና ማቋቋሚያ ማዕከል ነው። ምክንያቱም የሌንስ ፋብሪካ አላቸው።ሌሎች የሌንስ ፋብሪካዎች አሉ። ከዚያ ታስመጣለች። የታዘዘውን የሀኪሞች ወረቀት አይታ ለደንበኞቿ ትሸጣለች።
እታፈራሁ ከራሷና ከቤተሰቧ አልፋ አንድ መስማት የተሳነው ባለሙያ አብሯት ይሠራል። እሱም ከምስራች ዕደጥበብ ማሰልጠኛና ማቋቋሚያ ማዕከል ሠልጥኖ የወጣ ነው። በታዘዘው መሠረት ሌንሶችን ታመቻችለትና ይሠራል።
የመጀመሪያ ሥራዋን የጀመረችው ምስጋና የመነፅር ሥራ በሚል ሲሆን እሱ ጥሩና ውጤታማ ሲሆን አጠገቡ ምስክር የመነፅር ሥራ ለእህቷ ከፈተች። እህቷ ለአምስት ዓመት አብራት ሠርታለች። ቀጥሎ ምስክር የመነፅር ሥራ ሲከፈት አስተካክላ ሰጠቻት። በጥረቷ ከራሷ አልፏ ለእህቷ ተርፏለች። ቢያንስ ወደ 80ሺ ብር አውጥታ መነፅሮቹን ሁሉንም ነገር አመቻችታ ሰጥታታለች። አካል ጉዳተኝነቷ ያልበገራት – እታፈራሁ።
እታፈራሁ በ10 ብር ቁጠባ የጀመረው ራስን የማሸነፍ ጉዞ የራሷን ሕይወት ከማሸነፍ አልፋ ለእህቷ 80 ሺህ ብር የሚያወጣ የመነጽር መሸጫ ሱቅ ገዝታ፣ መኖሪያ ቤቷን ደግሞ 550 ሺ ብር በሚያወጣ ገንብታ የአይበገሬነቷን ጉዞ በስኬት ተያይዛዋለች።
አዲስ ዘመን ሐምሌ 27/2011
ኃይለማርያም ወንድሙ