በእናት ጥላ ስር

ትናንት…

ወይዘሮዋ ከዓመታት በፊት የነበራት መልካም ትዳር ለዛሬው ሕይወቷ አይረሴ ትዝታ ነው። የዛኔ ከውድ ባለቤቷ ጋር ብዙ ውጥኖች ነበሯት። ሦስት ልጆቻቸውን በወጉ ሊያሳድጉ፣ ጎጇቸውን በእኩል ሊመሩ፣ ሲያቅዱ ቆይተዋል። ሁለቱም ቤታቸውን በ‹‹አንተ ትብስ እኔ›› ይመራሉ። የጥንድነት ሕይወታቸው የጋራ ኑሯቸውን አጣምሮ፣ ትዳራቸውን አድምቆታል።

ወይዘሮ ትዕግስት ታርቆ ጥሩ ይሏት የቤት እመቤት ነች። ባለቤቷ በወዝ በላቡ ደክሞ የሚያመጣውን ገቢ በወጉ አብቃቅታ ልጆች ታሳድጋለች፣ ቤት ጓዳዋን ትመራለች። አባወራዋ ለፍቶ አዳሪ ጎልማሳ ነው። በበቂ ልምድ የዘለቀበት የጎሚስታ ሥራ መተዳደሪያው ከሆነ ዓመታት ተቆጥረዋል።

አንዳንዴ በሹፍርናው ሙያ ሥራ ባገኘ ጊዜ ራቅ ብሎ ይጓዛል። እንዲህ ማድረጉ ቤቱን ደጉሞ ልጆች ለማሳደግ ነው። ለእሱ ከትርፍ ጊዜው የሚገኘው ገቢ ለጎጆው ተጨማሪ እጅ ሆኖታል። ሁሌም ባለው ላይ ለማከል አቅሙ ነው። ቤቱን ደጉሞ የጎደለውን ይሞላበታል።

ባልና ሚስት ሁለት ወንዶችና አንዲት ሴት ልጅን አፍርተዋል። እንደ ወላጅ ስለ ልጆቻው ብሩህ ነገ ብዙ ያስባሉ። ዛሬን አልፈው ካሰቡት ለመድረስ የእናት አባታቸው ድጋፍ የግድ ይላል። ይህ ይሳካ ዘንድ ሁሌም የአቅማቸውን ይደክማሉ። ለሁሉም ከራሳቸው ቀንሰው እንደፍላጎታቸው ይሞላሉ። ለጥንዶቹ የመጀመሪያው ፍሬ ወንዱ ልጃቸው ነው። ከእሱ ቀጥሎ ቆንጅዬ ሴት ልጅ አግኝተዋል። የእሷ ተከታይ ሌላው ወንድ ልጅ ሦስተኛ ሆኖ ይቆጠራል።

ሁለተኛዋ ልጅ…

ቤተልሔም ለቤቱ ብቸኛዋ ሴት ልጅ ነች። ቆንጆና ዓይነግቡ ይሏት ቀልጣፋ። ቤቲ አጋጣሚ ሆኖ የተወለደችው በቤት ውስጥ ነበር። የዛኔ እናት ትዕግስት ድንገቴ ምጥ ባጣደፋት ግዜ ሆስፒታል ለማድረስ እንዳልተቻለ ታስታውሳለች። እናም ከቤት ልትወለድ ግድ ሆነ ። በወቅቱ ታዲያ ሕጻንዋን አንስቶ እትብቷን ለመቁረጥ የፈጠነ አልነበረም።

እናት ሁነኛ ሰው ደርሶ ጉዳዩ እስኪከወን ጥቂት ደቂቃዎች መቆጠራቸውን አትዘነጋም። በግዜው ግን ‹‹ምጡን እርሺው ልጁን አንሺው›› እንዲሉ ሆኖ እናትና ልጅ የገጠማቸው ችግር አልነበረም። ሁሉም በሠላም ተጠናቀቀ። እናት ልጇን በፍቅር አቅፋ ሳመች። የአራስነት ግዜ በወጉ አለፈ። ትንሽዋ ልጅ መሳቅ፣ መጫወት፣መቦረቅ ያዘች።

ሕጻንዋ ስድስተኛ ወሯን እንደያዘች ግን ያልታሰበው ሆነ። ወላጆቿና መላው ቤተሰብ በእሷ ዕድሜ ሊሆኑ የማይገባቸውን የጤና ማጣት ምልክቶች አስተዋሉ። የሚሹትን አካላዊ ለውጥ አለማየታቸው ደግሞ ይበልጥ ሥጋታቸውን ጨመረው። ቤቲ እንደሌሎች አይደለችም። በወጉ የመተንፈስ ችግር አለባት። አንገቷን ሰቅዞ የያዘውና በግልጽ የሚስተዋለው አካላዊ ተፅዕኖ ነፃ እንዳትሆን እያገዳት ነው። መላልሶ የያዛት ጉንፋንና ትኩሳት አቅሟን አዳክሞታል። ከተወለደች በኋላ ሐኪሞች ደጋግመው ቢያዩዋትም የጤና ችግር ስለመኖሩ አልገለጹም።

ጉዳዩ ያሳሰባቸው ወላጆች ወደ ጤና ጣቢያ በወሰዷት ግዜ ከፍተኛ ክትትል እንደሚያስፈልጋት ተነገራቸው። የተጻፈላቸውን የሕክምና ማስረጃ ይዘው በፍጥነት ወደ ጥቁር አንበሳ ሆስፒታል አመሩ። ሆስፒታሉ ተገቢውን ምርመራ እንዳጠናቀቀ በተለየ ችግር የ‹‹ልብ ክፍተት›› ስለመኖሩ አረጋገጠ። ወላጆች ይህን ካወቁ በኋላ ሕክምናውን በተለየ ትኩረት ገፉበት።

ስድስተኛ ወሯን ያጠናቀቀችው ሕጻን አሁንም ከነችግሯ ቀጠለች። ወር አልፎ ወር ሲተካ አካላዊ ለውጥ አልታየባትም። የአንደኛ ዓመት ልደቷን ሻማ ካበራች በኋላ ሁሉም ቤተሰብ ማደግ መለወጧን ናፈቀ። እሷ ግን እንደ እኩዮቿ አልሆነችም። እያደር መቀጨጭ፣ መክሳቷ ቀጠለ። አሁንምየ ወላጆቿ ጭንቀት በኀዘን፣ትካዜ ታጀበ።

ከቤቲ ቀጥሎ ሦስተኛው ልጅ ተወለደ። ታናሽዋ መሆኑ ነው። እሱ ዕድሜውን ይዞ ዕድገቱን ቀጥሏል ። እንደ ታላቅ እህቱ እየከሳ፣ እየቀጨጨ አይደለም። የእሷም ታላቅ ቢሆን ተለየ ችግር የለውም። ያለአንዳች እንከን ጤነኛ ሆኖ አድጓል። አሁንም እናት አባት መጨነቃቸው አልቀረም። ስለሴት ልጃቸው ጤንነት አጥብቀው አሰቡ፣ ተከዙ።

እናት ትዕግስት ከሕክምናው ባለፈ ለልጇ የቻለችውን ለማድረግ ሮጠች። ፀበል እያመላለሰች አስጠመቀቻት፣ የፍላጎቷን ለመሙላትም የአቅሟን ጣረች፣ ለፋች። ሁሉም እንደታሰበው አልሆነም። የቤቲ ጤና አልተመለሰም። አሁንም ወላጆች ዓይናቸው ከልጃቸው ላይ አልተነሳም። በየግዜው ሆስፒታል ከመመላለስ አልተቃቡም።

ተስፋ…

ውሎ አድሮ ቤቲ አካላዊ ለውጥ ታየባት። እንደ እድሜ እኩየቿ ከፍ ማለቷን ያዩ ቤተሰቦች ፈገግታቸው ተመለሰ። ይህን ተከትሎ የቀጠለው ሕክምና ግን ሌላ ችግር ስለመኖሩ አመላከተ። ከልቧ ችግር ጋር የሳንባዋ ግፊት አይሏል። እንዲህ መሆኑ የታሰበውን የልብ ቀዶ ሕክምና ለመከወን አያስችልም። በዓይኖቿ ላይ የተገኘው የሞራ ግርዶሽም እይታዋን ማዳከም ጀምሯል። ይህ እውነታ ችግሮች በነበሩበት እንዲቀጥሉ አስገደደ።

አሁን ልጆቹ እያደጉ ነው። ሁሉም ትምህርት ቤት ገብተው መማር ጀምረዋል። ባልና ሚስት እነሱን በወጉ ለማሳደግ ያጎደሉት የለም። እናት ከቤት፣ አባወራው ከውጭ እየሠሩ ለጎጇቸው ጽናት ይጥራሉ። ቤቲም በአካባቢያቸው ከሚገኝ ትምህርት ቤት ገብታለች። ለዘለቄታዊ መፍትሔ በውጭ አገር የተገኘላት ሕክምና በተስፋ እየተጠበቀ ነው። የውጭ ጉዞው ከተሳካ ጤናዋ ይመለሳል፣ ችግሮች ይቀላሉ።

የቀን ጎዶሎ…

የቤቱ አባወራ ዛሬም ርቆ ሊሄድ ተነስቷል። አንዳንዴ ከጎሚስታ ሙያው በተጓዳኝ የኮንትራት ሥራ ካገኘ መኪና ይዞ ይጓዛል። ለዚህ ደግሞ የዓመታት የሹፍርና ልምዱ አሳፍሮት አያውቅም። እንዳሻው አገር እያቋረጠ ይመልሰዋል። እንዲህ ማድረጉ ቤቱን ለመደጎም፣ ጎዶሎውን ለመሙላት ነው። አሁን ደግሞ የጉዞ መስመሩ በሰሜን አቅጣጫ ከወሎ ምድር አውሎታል።

አባወራው መሪውን ጨብጦ መኪናውን እያሽከረከረ ነው። ከቤቱ ሲመለስ ለሚስት ለልጆቹ ሊደርግ ያቀደውን ያስባል፣ የአሁኑን ከትናንቱ፣ የዛሬውን ከነገ እያዛመደ ብዙ ርቋል። ከፊት፣ ከኋላው ከግራ ከቀኙ ‹‹ሽው›› የሚሉ መኪኖች ያልፉታል። እሱም እንዲሁ ቀድሟቸው ይፈተለካል። ይህ እውነት የየዕለቱ የመንገድ ላይ ልማድ ነው።

ከደቂቃዎች በኋላ እሱን አልፈው የሄዱ ሾፌሮች የሆነውን አስተውለው ወደመኪናው ቀረቡ። እርዳታ ለማድረግ ዘግይተው ነበር። አባወራው ሾፌር ከነመኪናው ተገልብጦ ሕይወቱ አልፏል። ማግስቱን የባለቤቷ አስከሬን ተጭኖ የመጣላት ወይዘሮ የምትይዝ የምትጨብጠውን አጣች። በአንዴ ነገሮች ተለወጡ፣ ቀኑ ጨለመባት።

አሁን ድንገቴው የመኪና አደጋ እሷን ያለአጋር፣ ልጆቿን ያለአባት አስቀርቷል። ይህን እውነት አምኖ መቀበል ግድ ቢላትም ፈጥና በይሁንታ የምትስማማበት አልሆነም። ሦስት ልጆችን ለብቻዋ ማሳደግ ቀላል አልነበረም። እንዲያም ሆኖ አስከፊ የጨለማ ቀናትን ማለፍ፣ ፈታኙን የችግር ድልድይ መሻገር የግድ አላት። ልጆቿን እንደ እናትም፣ እንደአባትም ሆና ማሳደግ የእሷና የእሷ ግዴታ ብቻ ነው።

ከአምስት ዓመት በኋላ …

እነሆ! ይህ ታሪክ ካለፈ ዘንድሮ አምስት ዓመታት ተቆጠሩ። እነዚህ ያለፉ ጊዜያት ለወይዘሮዋ መልከ ብዙ ገጽታዎች ናቸው። ጎዶሎ ሞልታ የልጆቿን ፍላጎት ለማሳካት ራሷን እንደሻማ አቅልጣለች። ለምግብ እንጂ ለሥራ ያልደረሱ ልጆቿን በወጉ ለማሳደር እጅ እግሯን ለሥራ፣ አእምሮዋን ለበዛ ሀሳብ አጋልጣ ብዙ ለፍታለች።

ትዕግስት ባለቤቷን በድንገቴ ሞት ካጣች በኋላ ስለልጆቿ መኖር ያልሆነችው የለም። የባለቤቷ ሥራ ጊዜያዊ ነበር። ቀድሞ የቤት እመቤት ናትና ከእጇ ያኖረችው ሽራፊ ጥሪት በቤቷ የለም። የወሰደችው አማራጭ በጉልበቷ ሠርታ ልጆቿን ማኖርና ማስተማር ነው። ልብስ እያጠበች፣ በየቤቱ ሽሮ በርበሬ እያዘጋጀች ሕይወትን መግፋት፣ ኑሮን መቋቋም ግዴታዋ ሆነ።

ዛሬም ቢሆን ልጆቿ ደርሰው እናታቸውን ‹‹አለንልሽ፣ አይዞሽ›› የሚሏት አልሆኑም። አሁንም በእሷ ስር አድረው እጆቿን የሚሹ የነገን ተስፋ የሚጠብቁ ናቸው። ከምንም በላይ ግን የሴት ልጇ ጉዳይ ለእናት ትዕግስት አሳሳቢ ሆኗል። የጤናዋ ነገር ዛሬም መፍትሔ አልባ ነው።

ቤቲ አሁን የአስራ ሰባት ዓመት ወጣት ሆናለች። እንዲያም ሆኖ እንደ ዕድሜ እኩዮቿ ትሆን ዘንድ ዕድሉ የላትም። ዛሬም በልብ ሕመም እየተሰቃየች ነው። በዓይኗ ሞራ ምክንያት ርቃ መሄድ አይቻላትም። እናቷ ለእርሷ ልክ እንደምርኩዝ፣ ከዘራዋ ናት። ያለእሷ ድጋፍ የትም መሄድ መራመድን አትሞክርም።

እስካሁን የተሻለ ሕክምና ያለማግኘቷ የጤናዋን ጉዳይ አሳሳቢ አድርጎታል። በውጭ አገር ተይዞላት የነበረው የሕክምና ቀጠሮ ዛሬም ድረስ አልተሳካም። እንዲህ ሆኖ እናቷን ለኀዘን እሷን ለብስጭት ዳርጓታል። ወይዘሮዋ ሁሌም ባለቤቷን ባሰበች ቁጥር ብቸኝነት ይሰማታል። እሱ በሕይወት ቢኖርና ከጎኗ ቢቆም የዛሬው ሸክም የእሷ ብቻ አይሆንም። ይህን ስታስብ ውስጧ በኀዘን ይሰበራል።

ቤቲ የየዕለት እንቅስቃሴዋ በድካም የተሞላ ነው። ብዙ መራመድና ርቆ መሄድ ይከብዳታል። በየግዜው ነስር አያጣትም። የዓይኖቿ ሞራ መልበስ ደግሞ ችግሯን አብሶታል። ዘወትር ከጎኗ የማትርቀው እናት ሁሌም ድካሟን ታውቀዋለች። እንደ ልጅነቷ ግን ልታዝላት፣ ልታቅፋት አትችልም። ቀን ከሌት ሠርታ ከምታገኘው ገንዘብ የትምህርቷ ክፍያ እንዳይቋረጥ እንደጣረች ነው። ለዘንድሮ ግን ይህን መቀጠል የሚቻላት አይመስልም። የክፍያው መጨመር አቅሟን አንገዳግዶታል። የዓይኖቿ መታመምም እንዲሁ።

ለቤቲ ታላቅና ታናሽ የሆኑት ሁለት ወንድሞቿ እርስ በርስ ቅርበት አላቸው። ሁሌም አብረው ይጫወታሉ፣ ይውላሉ። ቤቲ የአካል እንጂ የአእምሮ ችግር የለባትም። በፍጹም ጤንነት የሚሆነውን ሁሉ ታውቃለች። አርቃ ታስባለች፣ ስለነገዋ ታልማለች። አእምሮዋ ሠላም በሆነ ጊዜ ደስተኛ ናት። ፊቷ በፈገግታ ይበራል።

አንዳንዴ ግን ወንድሞቿ እሷን የሚረዷት፣ የሚገነዘቧት ባልመሰላት ጊዜ ውስጧ በብስጭት ይሞላል። ሁኔታቸው በእጅጉ ያተክናታል። ስለምን የሚለው ጥያቄም በልቧ እየተመላለሰ ትፈተናለች፣ ትናደዳለች። ይህ ስሜት ሁሌም ወንድሞቼ እኔን አይረዱኝም ከሚል እውነት ላይ እንዳደረሳት እናቷ ትዕግስት በኀዘኔታ ትናገራለች።

ጥቂት ከቤቲ ጋር …

ቤተልሔም ሞሱን ያገኘኋት እንደሁልጊዜው ሁሉ ከእናቷ ጋር ሆና ነበር። ስሟን አስተዋውቃኝ ጨዋታ ከመጀመራችን የቀደመ ፍላጎቷን ለማወቅ አልቸገረኝም። የቤቲ የመጀመሪያ ቃል ‹‹ጤንነቴ እንዲስተካከልልኝ እፈልጋለሁ›› የሚል ነበር። በዚህ መነሻ የቀጠለው ቆይታ በተለየ ብሶት የተሞላ ነበር። ቤቲን አተኩሬ አስተዋልኳት። ለዓይን የሚቀል ስሜትን ታጋባለች። ቃሏ መልካም የሚባል ነው፣ ንግግሯ ፈጽሞ አይከብድም።

ግራ ቀኝ ሰቅዞ የያዛት የአንገቷ ላይ ችግር በግልጽ ይስተዋላል። ማጅራቷ ላይ የበቀለው ውብ ፀጉር ደግሞ ለዓይን በሚስብ መልኩ ዙሪያውን ተጎዝጉዟል። በሁኔታው እንደገረመኝ ፊቴን ወደ እሷ አዞርኩ። በዓይኖቿ ተቀብላኝ ንግግሯን ካቆመችበት ቀጠለች። አሁንም ሆድ እንደባሳት፣ እንደከፋት ነች። ቤቲ አፍታ ሳትቆይ ዓይኖቿ በዕንባ ተሞሉ። እይታዋ እናቷ ላይ ነበርና የምትለውን ልረዳው አልቸገረኝም። ‹‹እናቴ ስለኔ የሆነችልኝን ሩብ ታህል መሆን አልችልም። ድኜ፣ ሰው ሆኜ ውለታዋን መመለስ እፈልጋለሁ››

በዓይኖቿ ያቆቱት ትኩስ እንባዎች በፊቷ ተዘርግፈው በአንገቷ መውረድ ጀመሩ። በቻልኩት አቅም የእናት ደግነት ግዴታ ጭምር መሆኑን ዘርዝሬ ላሳምናት ሞከርኩ። እውነቱን ለመናገር ሁኔታዋ እኔን ጭምር እየረበሸኝ፣ ከልቤ እያዘንኩ ነው። እሷ በተለይ በዚህ ዓመት የመዳን ፍላጎቷ ጨምሯል። ይህ ባለመሳካቱ ግን ብስጭት፣ ንድድ እንደሚያደርጋት ስትነግረኝ በተለየ ስሜት ሆነ። የምትለውን ሁሉ በጥሞና አዳመጥኳት።

አሁን ይበልጥ ሆድ እየባሳትና ውስጧ በኀዘን እየነደደ ነው። በየዓመቱ ስለራሷ እንደምትሳልና ስለቷ ለምን እንደማይደርስ ራሷን መጠየቅ ያዘች። ወዲያው ደግሞ ብሶቷ አይሎ ተበሳጨች። ይህ ሁሉ ውስጧ ተከማችቶ የኖረ ኀዘን መሆኑ አልጠፋኝም።

ቤቲ ሕጻን ሳለችና በአሁን ዕድሜዋ ስሜቷ ይለያያል። የዛኔ ከእኩዮቿ ጋር ያለአንዳች ስጋት ትጫወት ነበር። አሁን ላይ ግን ሁሉም እንደራቋትና እንደማያወሯት ሆኖ ይሰማታል። ከወንድሞቿ ጋር ያላት ግንኙነትም ከዚህ አይለይም። መቼም ‹‹አይረዱኝም፣ አይሰሙኝም›› ስትል ታስባለች። ቤቲ ስለእነሱ ተስፋ ቆርጣለች። እንዲህ አይነቱ እውነት እያደር ፍራቻን ፈጥሮባታል። አንድ ቀን እናቷን ብታጣት የሚሆነውን ስታስብ ደግሞ ሞት ቀድሞ እንዲወስዳት አጥብቃ ትመኛለች።

ያልተመለሰው ጥያቄ

ብሶተኛዋ ልጅ ሁሌም በውስጧ አንድ ጥያቄ ይመላለሳል። ‹‹የእኔ የልብ ክፍተት ለምን አይገጥምም? ለምንስ ሕክምናውን አግኝቼ በቶሎ አልድንም? ራሷንም፣ ሐኪሞቿንም ደጋግም ትጠይቃለች። ይህ ጥያቄ በማንነቷ ዓለም መመላለስ የያዘው ወጣትነቷ በጀመረ ማግስት ነበር። አሁን ያለችበት ዕድሜ ብዙ እንድታስብ እንደእኩዮቿ አርቃ እንድታልም እያስገደዳት ነው።

ቤቲ ከትናንት ይልቅ ዛሬ ላይ የመኖር ፍላጎቷ ጨምሯል። ቢያንስ የዓይኗ ላይ ሞራ ቢነሳላት ተስፋዋ እንደሚለመልም ታውቃለች። አንዱ ሕመሟ ለሌላው አለመዳን ሰበብ ሆኖ ግን ዓመታትን ያለመፍትሔ አስቆጥሯታል። በአንድ ወቅት የደም ናሙናዋ ወደ እስራኤል ሀገር ተልኮ ውጤቱን በጉጉት ስትጠብቅ ነበር። ጥቂት ቆይቶ ግን ሁሉም እንዳልተሳካ ተነገራት።

ይህ አይነቱ አጋጣሚ ውስጧን ሰብሮ ተስፋዋን ያጨልመው ያዘ። ‹‹በቃ! አልድንም›› ይሉትን ስሜት እንዳትርቀው ምክንያት ሆነ። ቤቲ ከምንም በላይ የእናቷ ጉዳይ ውስጧን ያባባዋል። በምድር ላይ ያለቻት ብቸኛ ተስፋዋ ነችና ሕይወትን ያለእሷ ማሰቡ ይቸግራታል። ከፍቅሯ ብዛት በእጅጉ ትሳሳላታለች፣ ሁሌም ልፋት ድካሟ ዘልቆ ይሰማታል።

ቤቲ ባለባት ተደራራቢ የጤና ችግር ፍቅርና እንክብካቤ ያሻታል። በዚህ ክፍተት ግን እሷ በየቀኑ ሆድ እየባሳት ነው። ‹‹እናቴን በድንገት ባጣትስ ይሉት ስጋት ደግሞ ዕንቅልፍ ነስቷታል። ስለእናቷ ውለታ ብዙ ታስባለች። በሆነችላት ልክ ባይሆንም ነገን ልታሳርፋት፣ ልታስደስታት ትመኛለች። እናቷ ለእሷ ከቃል በላይ ነች። በትንፋሽዋ የምትፈውሳት መድኃኒቷ፣ ኖሯ የምታኖራት ጥላ ከለላዋ።

መልካምሥራ አፈወርቅ

አዲስ ዘመን ጥቅምት 2/2017 ዓ.ም

 

Recommended For You