
አሜሪካ የሰሜን አትላንቲክ የጦር ቃል ኪዳን ድርጅት (ኔቶ) አጋሮቿ የመከላከያ በጀታቸውንና ለድርጅቱ የሚያደርጉትን መዋጮ እንዲያሳድጉ በድጋሚ ጠይቃለች። የሀገሪቱ የመከላከያ ሚኒስትር ፔት ሄግሴት በብራሰልሱ የኔቶ አባል ሀገራት የመከላከያ ሚኒስትሮች ጉባዔ ላይ ባደረጉት ንግግር፣ አባል ሀገራት በዚህ ወር መገባደጃ ላይ ከሚካሄደው የድርጅቱ ዓመታዊ ጉባዔ በፊት የመከላከያ ወጪያቸውን እንዲጨምሩ ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ ያቀረቡትን ጥሪ እንዲተገብሩት ጠይቀዋል። አባል ሀገራት የበጀትና የመዋጮ ጭማሪውን በዚህ ወር እንደሚተገብሩትም ሄግሴት ያላቸውን ተስፋ ገልጸዋል። የአሜሪካው ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ የኔቶ አባላት ከጥቅል ሀገራዊ ምርታቸው ውስጥ አምስት በመቶ ያህሉን ለመከላከያ ዘርፋቸው እንዲመድቡ ጠይቀው ነበር።
ሄግሴት በንግግራቸው ‹‹እውነተኛ ጥምረት ከተፈለገ፣ ከሰንደቅ ዓላማ እና ከመደበኛ ኮንፈረንስ በላይ የሆነ አደረጃጀት ያስፈልጋል። ለውጊያ ዝግጁ የሆነ አቅምም ያስፈልጋል። እዚህ ያለነው ፕሬዚዳንት ትራምፕ የጀመሩትን የአምስት በመቶ በጀትና መዋጮ ሥራ ለመቀጠል ነው። እቅዱ በዚህ ወር መጨረሻ በሄግ በሚካሄደው የድርጀቱ ጉባዔ ላይ ሊተገበር ይገባል›› ብለዋል።
የኔቶ ዋና ጸሐፊ ማርክ ሩተ የድርጅቱ አባል ሀገራት ከጥቅል ሀገራዊ ምርታቸው ውስጥ ሦስት ነጥብ አምስት በመቶውን ለመከላከያ ኃይላቸው እንዲሁም ተጨማሪ አንድ ነጥብ አምስት በመቶ ደግሞ ከደህንነት ጋር ለተያያዙ ጉዳዮች እንዲመድቡ ጠይቀዋል። ‹‹ሰፋ አድርገንና በፍጥነት መጓዝ አለብን። በቀጣዩ የኔቶ ጉባዔ ላይ አዲስ የመከላከያ ኢንቨስትመንት እቅድ ይቀርባል›› ብለዋል።
የአልጀዚራው ዘጋቢ ሃሽም አሄልባራ ከብራሰልስ ባሰራጨው ዘገባው፤ ስፔን፣ ቤልጄምና ጀርመንን ጨምሮ የድርጀቱ አባል የሆኑ አንዳንድ የአውሮፓ ሀገራት የአምስት በመቶውን በጀት እቅድ ማሳካት እጅግ አስቸጋሪ እንደሆነ ያምናሉ። ‹‹ሀገራቱ እቅዱን ማሳካት አስቸጋሪ እንደሆነ ቢያምኑም አዳዲስ የጦር መሣሪያዎችንና ለመታጠቅ እና ሠራዊታቸውን ለድንገተኛ ጂኦፖለቲካዊ ለውጥ ዝግጁ ለማድረግ የሚያስችሉ ወታደራዊ ስትራቴጂዎችን በመቅረጽ ረገድ ግን ገፍተው እየሄዱ ይገኛሉ›› ብሏል። የሩሲያ-ዩክሬን ጦርነት ከተጀመረ ወዲህ የኔቶ አባላት የሆኑ የአውሮፓ ሀገራት የመከላከያ በጀታቸውን በፍጥነት እያሳደጉ ይገኛሉ። ሀገራቱ ሩሲያ ትልቋ የአውሮፓ የደህንነት ስጋት ናት ብለው እንደሚያምኑ አሄልባራ በዘገባው አመልክቷል።
ዋና ጸሐፊው ማርክ ሩተ የአምስት በመቶው የመከላከያ በጀት እቅድ እ.አ.አ. በ2032 ሙሉ በሙሉ እንዲሳካ ያቀረቡት ሃሳብ በአባል ሀገራቱ መካከል ክፍፍልን ፈጥሯል። አንዳንዶቹ አባል ሀገራት የተቀመጠው ጊዜ ረጅም እንደሆነ ሲገልጹ፣ ሌሎቹ ደግሞ አሁናዊ ነባራዊ ሁኔታዎችን ከግምት ውስጥ በማስገባት እቅዱን ለማሳካት የተቀመጠው ጊዜ አጭር እንደሆነ ይሞግታሉ።
የሊቱዌኒያ የመከላከያ ሚኒስትር ዶቪል ሳካሊን ለ2032 ተብሎ የተቀመጠው ጊዜ በጣም የዘገየ እንደሆነ ጠቁመው፣ እቅዱ እንዲሳካ የሚቀመጠው የጊዜ ገደብ ከ2030 ማለፍ እንደሌለበት ተናግረዋል። የስዊድን የመከላከያ ሚኒስትር ፓል ጆንሰን አባል ሀገራቱ የአምስት በመቶ እቅዱን እ.አ.አ በ2030 እንዲያሳኩ ፍላጎት እንዳላት ገልጸዋል። የጥምረቱ ባለስልጣናት በበኩላቸው አባል ሀገራቱ እቅዱን ለማሳካት ከጥቅል ሀገራዊ ምርታቸው ውስጥ ከሦስት ነጥብ አምስት እስከ ሦስት ነጥብ ሰባት በመቶውን ሊጠይቃቸው እንደሚችል አስረድተዋል።
የፕሬዚዳንት ትራምፕ በድጋሚ ወደ ዋይት ሃውስ መመለስ ለብዙ የኔቶ አባል ሀገራት መሪዎች ትልቅ ስጋት ፈጥሯል። ለባለብዙ ወገን ስምምነቶችና ዓለም አቀፍ ትብብሮች ብዙም ግድ የላቸውም ተብለው የሚወቀሱት ፕሬዚዳንት ትራምፕ፣ በሰሜን አትላንቲኩ ወታደራዊ ትብብር ላይ ተደጋጋሚ ወቀሳዎችን ያቀርባሉ። ፕሬዚዳንቱ የድርጅቱ አብዛኛው ሥራና ኃላፊነት በአሜሪካ ትከሻ ላይ የወደቀ ነው ብለው ያምናሉ። አባል ሀገራቱ የሚጠበቅባቸውን መዋጮ እያደረጉ እንዳልሆነና ለድርጅቱ የሚያደርጉትን መዋጮ እንዲያሳድጉም ደጋግመው ይናገራሉ። ‹‹አሜሪካ ከፍተኛ ገንዘብ እያወጣች አውሮፓን የምትጠብቀው በምን እዳዋ ነው?›› እያሉ ሲጠይቁ ቆይተዋል።
በዚህም የተነሳ ፕሬዚዳንቱ አሜሪካ አውሮፓን ላለፉት 75 ዓመታት ሲጠብቅ ከኖረው የትራንስአትላንቲክ የጦር ኅብረት ልትወጣ እንደምትችል ሲዝቱም ነበር። ታዲያ ይህን የአሜሪካ ዛቻ ችላ ማለት ያልፈለጉት የአውሮፓ ሀገራት የመከላከያ በጀታቸውን እንደሚያሳድጉ ገልፀዋል። ለአብነት ያህል ዩናይትድ ኪንግደም፣ ጀርመንና ፈረንሳይ ለመከላከያ ኃይላቸው የሚመድቡትን በጀት እንደሚጨምሩ አሳውቀዋል።
የፕሬዚዳንት ትራምፕ ርምጃዎች ያሰጓቸው አንዳንድ የአውሮፓ መሪዎች አውሮፓ ከአሜሪካ ጥገኝነት መላቀቅ እንዳለበት ደጋግመው እየተናገሩ ነው። ለአብነት ያህል በቅርቡ ጀርመንን የመምራት ኃላፊነት የተረከቡት መራሄ መንግሥት ፍሬድሪኽ ሜትስ አውሮፓ ከአሜሪካ ጥገኝነት መላቀቅ እንዳለበት በፅኑ የሚያምኑ ፖለቲከኛ ናቸው። ከአሜሪካ ጫና የተላቀቀ አውሮፓን መገንባት ከዋና ዋና እቅዶቻቸው መካከል አንዱ እንደሆነና ፕሬዚዳንት ትራምፕ በሚወስዷቸው ርምጃዎች በእጅጉ መበሳጨታቸውን የሚናገሩት ሜትስ፣ የአሜሪካ መንግሥት የአውሮፓ መፃኢ እድል ግድ እንደማይሰጠው በግልጽ ማሳየቱንና አውሮፓ በፍጥነት የራሱ የሆነ መከላከያ ሳያስፈልገው እንደማይቀር ተናግረዋል። ‹‹ከአሜሪካ በኩል ምን ዓይነት ውሳኔና ርምጃ እንደሚመጣ ብዥታ የለብኝም። ከአሜሪካም ከሩሲያም ከፍተኛ ጫና እየደረሰብን ነው›› በማለት አውሮፓ ለምጣኔ ሀብቱም ሆነ ለጸጥታው ተባብሮ ከመቆም ውጭ ሁነኛ አጋር አለኝ ብሎ መዘናጋት እንደማያስፈልገው አበክረው ሲናገሩ ይደመጣሉ።
በሌላ በኩል የአውሮፓ ኃያላን መንግሥታት ከአምስት እስከ 10 ዓመታት ውስጥ አሜሪካ በሰሜን አትላንቲክ የጦር ቃል ኪዳን ድርጅት (ኔቶ) ውስጥ ያላትን ሚና በአውሮፓ ኃይሎች ለመተካት የሚያስችል እቅድ ስለማዘጋጀታቸው ከሁለት ወራት በፊት ይፋ የሆነ አንድ መረጃ አመልክቷል። እቅዱ ለአውሮፓ ደህንነትና መከላከያ አህጉሩ ራሱ የበለጠውን ኃላፊነት እንዲወስድ የሚያደርግ ነው ተብሏል። ዩናይትድ ኪንግደም፣ ፈረንሳይ፣ ጀርመንና የኖርዲክ ሀገራት የጦር ኅብረቱን ቅርጽ የሚለውጠውን እቅድ ካዘጋጁት ሀገራት መካከል እንደሚጠቀሱ ‹‹ፋይናንሻል ታይምስ›› (The Financial Times) ጋዜጣ መዘገቡ ይታወሳል። ይህ እቅድ ስኬታማ ከሆነ በትራንስአትላንቲክ ትብብር እጣ ፈንታ ላይ ተጨባጭ ለውጥ የሚያስከትል ይሆናል ተብሏል።
አውሮፓና ካናዳ የኔቶን የጦር መሣሪያና የቁሳቁስ ክምችት በ30 በመቶ እንዲያሳድጉ የጥምረቱ አመራሮች ጥያቄ ማቅረባቸውም የሚታወስ ነው። የአውሮፓ መሪዎች ይህን እቅድ እንዲያዘጋጁ ካደረጓቸው ምክንያቶች መካከል የሩሲያ-ዩክሬን ጦርነት እና ዶናልድ ትራምፕ የአሜሪካ ፕሬዚዳንት ከሆኑ ወዲህ እየወሰዷቸው ያሉት ርምጃዎች በዋናነት ይጠቀሳሉ።
ቁጥራቸው ጥቂት የማይባሉ የአውሮፓ ፖለቲከኞች የሩሲያ ቀጣይ የወረራ ኢላማ አውሮፓ እንደሆነ ሲናገሩ ይደመጣሉ። ለዚህም አውሮፓ ከወዲሁ መዘጋጀት እንዳለበት ያሳስባሉ። አውሮፓ በአስተማማኝነት ራሱን መከላከልና ማስከበር የሚችለው በራሱ የመከላከያ ኃይል እንደሆነ የሚያምኑት እነዚህ የአውሮፓ ፖለቲከኞች፣ ከአሜሪካ ጥላ ነፃ የወጣ አውሮፓዊ የመከላከያ ኃይል እንደሚያስፈልግ ይገልፃሉ።
የዩክሬን ጦርነት አውሮፓን በብዙ መንገዶች አስጨንቋል። የሩሲያን ነዳጅና ሌሎች ምርቶችን በብዛት የሚገዙት የአውሮፓ ሀገራት ከደረሰባቸው የምጣኔ ሀብት ተፅዕኖ ባሻገር፣ ሀገራቱ የሩሲያ ወታደራዊ የጥቃት ሰለባ የመሆን ስጋትም አለባቸው። በርካታ የአውሮፓ ኅብረት አባል ሀገራት ለዩክሬን በሚያደርጉት የጦር መሣሪያና የገንዘብ ድጋፍ በእጅጉ የተበሳጨችው ሩሲያ፣ ለምትወስዳቸው የአፀፋ ርምጃዎች ኃላፊነቱን ሀገራቱ እንደሚወስዱ ትዝታለች። አውሮፓውያኑ የሩሲያ ርምጃዎች ወታደራዊ ጥቃቶችን ሊጨምር እንደሚችል ይገምታሉ።
የሩሲያን ዛቻ ለአውሮፓውያኑ የበለጠ አስፈሪ ያደረገው ደግሞ የዶናልድ ትራምፕ በፕሬዚዳንትነት ወደ ‹‹ዋይት ሃውስ›› መመለሳቸውና የሚወስዷቸው ርምጃዎች ናቸው። ‹‹ምርጫውን ካሸነፍኩ በአንድ ቀን አስቆመዋለሁ›› ያሉትን የሩሲያ-ዩክሬን ጦርነትን ለማስቆም የወሰዷቸው ርምጃዎች በአውሮፓ ፖለቲከኞች ዘንድ በበጎ አልታዩላቸውም። ፕሬዚዳንት ትራምፕ የዩክሬኑን ፕሬዚዳንት ቮሎድሚር ዘለንስኪን በተደጋጋሚ መውቀሳቸው፣ አሜሪካ ለዩክሬን ስትሰጠው የነበረውን ወታደራዊ ድጋፍ እና የስለላና ደህንነት መረጃዎችን ለዩክሬን ማጋራቷን ለጥቂት ቀናትም ቢሆን ማቋረጣቸው፣ ስለዩክሬን የኔቶ አባልነትና በሩሲያ ስለተያዙት ግዛቶቿ ጉዳይ የተናገሯቸው ንግግሮች እንዲሁም በመጀመሪያዎቹ የሩሲያ-አሜሪካ-ዩክሬን የድርድር መድረኮች ላይ የአውሮፓ ሀገራትን ለማሳተፍ አለመፈለጋቸው አውሮፓውያኑ ስለቀጣዩ የአህጉራቸው እጣ ፈንታ እንዲያስቡ ምክንያት ሳይሆናቸው አልቀረም።
አሜሪካ በሰሜን አትላንቲክ የጦር ቃል ከዳን ድርጅት ውስጥ ግዙፍ ሚና አላት። ከድርጅቱ ዓመታዊ ወጭ ውስጥ ከ16 በመቶ የሚበልጠውን የምትሸፍነው አሜሪካ ናት። በመላው አውሮፓ እስከ100ሺ የሚደርስ ጦርም አሰማርታለች። ይህ የሚያሳየው አሜሪካ በአውሮፓ ፀጥታና ደህንነት ውስጥ ከፍተኛ ድርሻ እንዳላት ነው። ከዚህ ወሳኝና ግዙፍ የአሜሪካ ሚና አንፃር ‹‹አባል ሀገራቱ የሚጠበቅባቸውን መዋጮ እያደረጉ ስላልሆነ ኃላፊነታቸውን ይወጡ፤ አለበለዚያ አሜሪካ ከጥምረቱ አባልነት ልትወጣ ትችላለች›› የሚለው የፕሬዚዳንት ትራምፕ ማሳሰቢያ ለድርጅቱ ህልውና በቀላሉ የሚታይና እንደዋዛ የሚታለፍ ማስጠንቀቂያ አይደለም።
አንተነህ ቸሬ
አዲስ ዘመን ማክሰኞ ሰኔ 3 ቀን 2017 ዓ.ም