
አዲስ አበባ፡- 1 ሺህ 446ኛው የኢድ አል-አደሃ (አረፋ) በዓል በተለያዩ የሀገሪቱ ክልሎችና ከተሞች በድምቀት ተከብሯል። በዓሉ የመደጋገፍ፣ የአንድነትና የአብሮነት እሴቶች በጉልህ የተፀባረቁበት መሆኑን የእምነቱ ተከታዮች ተናግረዋል።
1446ኛው የኢድ አል-አድሃ ሰላት ስግደት በመዲናዋ ከተለያዩ አቅጣጫዎች የመጡ የእምነቱ ተከታዮች በተገኙበት በአዲስ አበባ ስታዲየም ተከናውኗል:: በሥነ ሥርዓቱ ላይ የኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክር ቤት ፕሬዚዳንት ሼህ ሐጂ ኢብራሂም ቱፋ ተገኝተዋል።
የአንዋር መስጂድ ዋና ኢማም ሐጂ ጠሃ ሀሩን የኢድ አል-አድሃ በዓል አስመልክቶ ባስተላለፉት መልዕክትም፤ አረፋ የመስዋዕትነት በዓል ነው። ሐጃጆች አረፋ ተራራ ላይ ቆመው በአንድነት፣ ዘር ቀለም ቋንቋ ሳይለያቸው ፈጣሪያቸውን አወድሰዋል፣ ጸሎት አድርገዋል ብለዋል። እኛም በሀገራችን አንዳንድ ቦታ የሚንፀባረቀውን ልዩነት ትተን ልክ እንደ አረፋ በጋራ በመቆም ሀገራችን ማስቀደም አለብን ሲሉ ተናግረዋል።
የሲዳማ ክልል እስልምና ጉዳዮች ከፍተኛ ምክር ቤት ፕሬዚዳንት ሼህ አብዱልሽኩር አብዱልቃድር 1 ሺህ 446ኛው የኢድ አል-አድሃ (አረፋ) በዓል በሀዋሳ ሲከበር፤ የአረፋ በዓል የአብሮነት በመሆኑ ሕዝበ ሙስሊሙ በዓሉን ከተቸገሩ ወገኖቹ ጋር ማክበር እንዳለበት አስገንዝበዋል። ካለው ላይ ለሌሎች ወገኖቹ በማካፈል በዓሉን ሁሉም ተደስቶ በአብሮነት እንዲያከብር ማድረግ አለብን ብለዋል።
የዕምነቱ ሥርዓት በሚያዘው መሠረት ሕዝበ ሙስሊሙ ለፈጣሪና ለመሪዎቹ ታማኝ መሆን እንዳለበትም ገልጸው፣ ያለሰላም ዕምነትን ማካሄድ ስለማይቻል ሰላምን አጠናክሮ ለማስቀጠል የበኩሉን መወጣት እንዳለበትም ገልጸዋል።
የኢድ አል-አድሃ (አረፋ) በዓል የደስታ በዓል በመሆኑ፣ የተቸገሩትን በማገዝ እና ያዘኑትን በማፅናናት ማሳለፍ እንደሚገባ የትግራይ ክልል እስልምና ጉዳዮች ፕሬዚዳንት ሼህ አደም አብዱልቃድር ገልጸዋል። የኢድ አል-አድሃ (አረፋ) በዓል በመቐለ ከተማ በተለያዩ ሃይማኖታዊ ሥነ-ሥርዓቶች ተከብሯል። በበዓሉ አከባበር የተገኙት ሼህ አደም፤ አረፋ ብቻችንን ተደስተን የምናሳልፈው በዓል ባለመሆኑ የመተጋገዝ ባህላችንን ማስቀጠል ይገባል ብለዋል።
የኢድ አል-አድሃ (አረፋ) በዓል በወላይታ ሶዶ ከተማ በአደባባይ ሶላት ሥነ-ሥርዓት ተከብሯል። የወላይታ አካባቢ ሸሪኣ ፍርድ ቤት ቃዲ ኡስታዝ ጃውሃር ሃሚድ፣ የሐጅ ሥነ-ሥርዓት የሚካሄደው በዚህ የኢድ ወቅት መሆኑ በዓሉን ለየት እንደሚያደርገው ገልጸዋል። ሕዝበ ሙስሊሙ የሚያከናውነው መልካም ተግባር በበዓልና በመደበኛ ጊዜያት ተጠናክሮ ሊቀጥል ይገባል ብለዋል።
የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል እስልምና ጉዳዮች ምክር ቤት ሥራ አመራር ኡስማን አኮ በበኩላቸው፤ የዘንድሮ የኢድ አል-አድሃ በዓል በዕለተ ዓርብ በጁማ ቀን መዋሉ ልዩ ትርጉም እንደሚሰጥ ተናግረዋል።
የኢድ አል-አደሃ (አረፋ) በዓልን በአካባቢያቸው የሚገኙ የተቸገሩ ወገኖችን በመርዳትና በመጠየቅ አብሮነትንና አንድነትን በሚያጠናክሩ ዕሴቶች ያከበሩ መሆኑን የእስልምና ዕምነት ተከታዮች ተናግረዋል።
በአዳማ፣ በደሴ፣ ጅማ፤ ድሬዳዋ፣ በቦንጋ፣ በጎንደር፣ በአሶሳ፣ በጋምቤላ፣ በጅንካ፣ በሠመራ፣ በሐረር፣ በባሕር ዳር፣ በጅግጅጋ ከተሞችና በሌሎች የሀገሪቱ አካባቢዎች 1446ኛው የኢድ አል-አድሃ (አረፋ) በዓል በተለያዩ ሃይማኖታዊ ሥነ ሥርዓቶች በድምቀት ተከብሯል። የዕምነቱ ተከታዮች ከማለዳው ጀምሮ በዓሉ በሚከበርበት ስፍራ በመገኘት የጋራ ሰላት ሰግደዋል።
ሳሙኤል ወንድወሰን
አዲስ ዘመን ቅዳሜ ግንቦት 30 ቀን 2017 ዓ.ም