
አዲስ አበባ፡- በሀገር አቀፍ ደረጃ በዓይነት አንድ ወይም የሕጻናት ስኳር ሕመም ከዓመት ዓመት ቁጥሩ ከፍ እያለ መጥቶ አሁን ላይ በእጥፍ መጨመሩን በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የጥቁር አንበሳ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል የሕጻናት የሆሮሞንና ስኳር ሐኪም ገለጹ። በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የጥቁር አንበሳ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል የሕጻናት የሆሮሞንና ስኳር ሐኪምና በኢትዮጵያ የስኳር ሕመምተኞች ማኅበር የቦርድ አባል ዶክተር ሰውአገኘሁ የሺዋስ ለአዲስ ዘመን ጋዜጣ እንደተናገሩት፤ የስኳር ሕመምም ሆነ ሌሎች በሽታዎች ላይ የሚደረጉ ጥናቶች በቂ መረጃ የሚሰጡ ባይሆንም እንደ የኢትዮጵያ ስኳር ሕመምተኞች መረጃ መሠረት በስኳር ሕመም ችግር ውስጥ የሚገኙ የሕጻናት ቁጥር ከዓመት ዓመት እየጨመረ መጥቷል። በአሁኑ ጊዜ የአይነት አንድ ስኳር ሕመም ወይም የሕጻናት ስኳር በሽታ የሚባለው ከሦስትና አራት ዓመት በፊት ከነበረው በእጥፍ ጨምሯል ብለዋል።
የስኳር ሕመምተኞች ማኅበር ውስጥ የሚሳተፉ ሰዎች ሕመሙ እንዳለባቸው የተረጋገጡ መሆናቸውን የጠቆሙት ሐኪሙ፤ የማኅበሩ አባላት ከአራት ዓመት በፊት በማኅበሩ ውስጥ ያሉ የአይነት አንድ የስኳር ሕመምተኞች ወይም የሕጻናት ስኳር ሕመም ተጠቂዎች ቁጥር ከስምንት እስከ ዘጠኝ ሺህ የሚደርስ ነበር። አሁን ላይ ችግሩ እየጨመረ በመምጣቱ የተነሳ ወደ ሕክምና ተቋም በመሄድ ተመርምሮ በሽታው ተለይቶለት አባል ያልሆነውን ሳይጨምር ወደ 16ሺህ ከፍ እንዳለ መረጃው እንደሚያሳይ አንስተዋል።
በሀገር አቀፍ ደረጃ የተጠናከረ መረጃ ባይኖርም በስኳር በሽታ የተያዙ ዜጎች ሁለት ሚሊዮን የሚደርሱ መሆናቸውን የሚገልጹት ዶክተር ሰውአገኝ፤ ከዚያ ውስጥ ከ100ሺህ ያላነሱ ሕጻናት በአይነት አንድ ስኳር በሽታ የሚያዙ መሆናቸውን የተለያዩ ጥናቶችን አብነት አድርገው ጠቁመዋል።
የሕመሙን መባባስ በመሠረታዊነት የሚጨምሩት ነገሮች መካከልም የሕክምና ባለሙያዎች እጥረት፤ የማኅበረሰቡ ግንዛቤ በበቂ ሁኔታ ያለመኖርና የግብዓት ተደራሽነት ጉዳይ እንደሆነ የሚናገሩት ዶክተር ሰውአገኝ፤ በሀገር ደረጃ ሕክምናውን በሚመለከት በበቂ ሁኔታ እየተሰጠ ነው ለማለት የማያስደፍሩ ሁኔታዎች መኖራቸውን ገልጸዋል።
ለአብነትም ከሕጻናት ሕክምና ጋር ተያይዞ በሀገር ደረጃ የሕጻናት ሆሮሞን ሕክምና የሚሰጡ ባለሙያዎች ቁጥር አራት ብቻ እንደሆኑ አመልክተው፤ ይህም ከ120 ሚሊዮን በላይ ለሆነ ሕዝብ ውስጥ ላሉ ሕጻናት ተደራሽ መሆን በፍጹም የማይቻል ነገር እንደሆነም አመላክተዋል።
አብዛኛው ማኅበረሰብ ሕጻናትን ስኳር በሽታ ይይዛቸዋል ብሎ አለማመንና እንደተያዙ ሲነገራቸውም ቶሎ አለመቀበል ከዚያም ወደ ሕክምና ተቋማት ያለመውሰድ ችግር የማኅበረሰብ ግንዛቤ ማነስ እንደሆነም አስረድተው፤ በዚህ ደግሞ በጥቁር አንበሳ ሆስፒታል ብቻ በተደረገ ጥናት 80 በመቶ የሚሆኑ ሕጻናት ወደ ሕክምና ተቋም የሚመጡት በሽታው የመጨረሻ ደረጃ ላይ ከደረሰ በኋላ መሆኑንም አብራርተዋል።
ጽጌረዳ ጫንያለው
አዲስ ዘመን ቅዳሜ ግንቦት 30 ቀን 2017 ዓ.ም