“ስሎቬኒያ በንብ ማነብ ያላትን ልምድ ለኢትዮጵያ ለማካፈል ዝግጁ ናት” – ፕሬዚዳንት ናታሻ ፒርስ (ዶ/ር)

አዲስ አበባ፦ ስሎቬኒያ በሰው ሠራሽ አስተውሎትና በንብ ማነብ ያላትን ልምድ ለኢትዮጵያ ለማካፈል ዝግጁ ናት ሲሉ የስሎቬኒያ ሪፐብሊክ ፕሬዚዳንት ናታሻ ፒርስ (ዶ/ር) ገለጹ።

ፕሬዚዳንት ናታሻ ፒርስ (ዶ/ር) በአዲስ አበባ ጀሞ አካባቢ ያለውን ብዙ የጎዳና ሕፃናትን እየታደገ ያለውን የቦስኮ ሕፃናት ማዕከልን ትናንት የጎበኙ ሲሆን በእለቱ ከአዲስ አበባ ከንቲባ አዳነች አቤቤ ጋር “ዘመናዊ የከተማ ንብ ማነብ ሠርቶ ማሳያ ፕሮግራም”ን በአዲስ አበባ አዲሱ ዙ ፓርክ አስጀምረዋል።

የስሎቬኒያ ሪፐብሊክ ፕሬዚዳንት ናታሻ ፒርስ (ዶ/ር) በጉብኝታቸው ወቅት እንደተናገሩት፤ ኢትዮጵያና ስሎቬኒያ የፖለቲካ ምክክር እያደረጉ ነው። ስሎቬኒያ የፀጥታው ምክር ቤት ተለዋጭ አባል ብትሆንም በምክር ቤቱ አፍሪካ ቋሚ አባል እንድትሆን ስሎቬኒያ አስፈላጊው ድጋፍ ታደርጋለች። ለዚህም ከአፍሪካ ኅብረት አመራሮች ጋር ውይይት ተደርጓል ብለዋል።

የኢትዮጵያና የስሎቬኒያን ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት ለማሳደግ ሁለቱ ሀገራት በንብ ማነብ ሥራ ላይ ጅምር ሥራዎችን እያከናወኑ መሆኑን ጠቁመው፤ ስሎቬኒያ ከንብ ማነብ ባለፈ በሰው ሠራሽ አስተውሎት የተሻለ አቅም አላት። በተለይ የውሃ አካላትን በሳተላይት የመጠበቅ ልዩ አቅም ስሎቫሊያ እንዳላት ተናግረዋል።

ይህንን ልምድ ለሕንድ መንግሥት ተሞክሮ ማካፈላቸውን የገለጹት ፕሬዚዳንት ናታሻ ፒርስ (ዶ/ር)፤ የኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድም (ዶ/ር) ይህ ሥራ በኢትዮጵያ እንዲስፋፋ እንደሚፈልጉ ገልጸውልኛል ሲሉም ተናግረዋል።

ሶሎቬኒያ በቆዳ ስፋቷ እንዲሁም በሕዝብ ቁጥሯ ትንሽ ሀገር ነች። በዲፕሎማሲ ሥራዋም በዓለም ላይ ሰላም እንዲሰፍን እየሠራች የምትገኝ ሀገር መሆኗን ተናግረዋል።

ከዚህም ባለፈ በአዲስ አበባ ከንብ ማነብ ሠርቶ ማሳያ ባለፈ ሌሎች ፕሮጀክቶችንም እንደምትጀምር ገልጸው፤ ከንቲባ አዳነች አቤቤ የከተማ ንብ ማነብ ሥራን በስሎቬኒያ ተገኝተው እንዲመለከቱም ጋብዘዋል።

የአዲስ አበባ ከንቲባ አዳነች አቤቤ በበኩላቸው፤ ኢትዮጵያ በአየር ንብረት ለውጥን ለመከላከል በአረንጓዴ ዐሻራ ሰፊ ሥራ እየሠራች መሆኑን ገልጸው፤ በዚህም ለብዝኃ ሕይወት ጥበቃ እያደረገች እንደምትገኝ አመልክተዋል።

በከተማ ግብርናም ንብ ማነብ ላይ ትኩረት መደረጉን ጠቁመው፤ በዚህ ረገድም አዲስ አበባ ከስሎቬኒያ ለመማር ዝግጁ ነች ብለዋል። በተለይ አዲስ አበባ ከስሎቬኒያ ከተሞች ጋር የእህትማማችነት ስምምነት መፈራረም እንደምትፈልግ ጠቁመው፤ ዘመናዊ የከተማ ንብ ማነብ ሥራ ከማር ምርት ባለፈ ለሥርዓተ ትምህርት እና በሁለቱ ሀገራት መካከል ያለውን ግንኙነት ለማጠናከር የሚያግዝ እንደሆነ ተናግረዋል።

በውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የአውሮፓ እና የአሜሪካ ጉዳዮች ዳይሬክተር ጄኔራል አምባሳደር አብርሃም መንግሥቱ በበኩላቸው የሁለቱን ሀገራት ግንኙነት አስመልክቶ በሰጡት ማብራሪያ፤ ስሎቬኒያ የቀድሞ ዩጎዝላቪያ ሀገር አካል መሆኗን ገልጸው፤ በራሳቸው ሀገር ከሆኑ በኋላ ኢኮኖሚያቸው በከፍተኛ ሁኔታ ያደገ መሆኑን ገልጸዋል።

ስሎቬኒያ በአዲስ አበባ በቅርብ ጊዜ ኤምባሲዋን መክፈቷን አውስተው፤ በተለምዶ በሀገራችን የንብ ማነብ ሥራ በገጠር የሚከናወን ሲሆን አሁን ከስሎቬኒያ ጋር በከተማ ደረጃ ንብ ማነብ የሚቻልበትን ዘዴ ተሞክሮ መውሰድ እንደሚቻል ተናግረዋል።

ከዚህም ባለፈ በሰው ሠራሽ አስተውሎት፣ በፀጥታው ምክር ቤት ከኢትዮጵያ ጋር ያላቸውን ትብብር የሚጠናከርበት ሁኔታዎች ላይ ጅምር ሥራዎች እየተከናወኑ መሆኑን ጠቁመው፤ እነዚህን ጉዳዮች ወደፊት ይበልጥ ለማሳደግ ምቹ መደላድል እየተፈጠረ መሆኑን ገልጸዋል።

ሳሙኤል ወንደሰን

 

አዲስ ዘመን ዓርብ ግንቦት 29 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You