የኢትዮጵያ ቆዳ ኢንዱስትሪ ትናንት እና ዛሬ

ኢትዮጵያ በቀንድ ከብት ሀብት በዓለም ከሚታወቁት አሥር ሀገሮች አንዱ ናት። እስከቅርብ ጊዜ በዓለም 6ኛ ወይም 7ኛ ደረጃ ስትገኝ በአፍሪካ በ1ኛ ደረጃ ላይ እንደነበረች ይታወቃል። ከቆዳና የቆዳ ውጤቶች ኢንዱስትሪ ምርምርና ልማት ማዕከል በተገኘው መረጃ መሠረት አሁን ያለው የእንስሳት ሀብት ብዛት ቀንድ ከብት 70 ሚሊዮን፣ በግ 42 ሚሊዮን እና ፍየል 53 ሚሊዮን ነው። ይህም በሀገሪቱ ዘመናዊ የቆዳ ኢንዱስትሪ እንዲስፋፋ ምክንያት ከሆኑት እድሎች አንዱ ነው።

በሀገራችን የቆዳና የቆዳ ኢንዱስትሪ በዘመናዊ መንገድ ማምረት ከተጀመረ አንድ ምዕተ ዓመት ያህል እንደሆነ ስለዘርፉ ከተዘጋጁ ሰነዶች .መረዳት ይቻላል። የመጀመሪያው ቆዳ ፋብሪካ አስኮ የአሁኑ አዲስ አበባ ቆዳ ፋብሪካ እ.ኤ.አ በ1928 ዓ.ም. የተቋቋመ ሲሆን እና ሁለተኛ ዳርማር ቆዳ ፋብሪካ የአሁኑ አዋሽ ቆዳ ፋብሪካ እ.ኤ.አ በ1933 ዓ.ም. የተቋቋመ መሆኑ ይነገራል። በፋብሪካዎቹ የሚመረተውን ቆዳ እሴት ጨምሮ ወደ ጫማና ሌሎች የቆዳ ውጤቶች ለመቀየርም በማሰብ በፋብሪካዎቹ ባለቤቶች ሁለት ጫማ ፋብሪካዎች ተቋቁሟል፡፡

የጫማ ፋብሪካዎቹም አስኮ ጫማ ፋብሪካ (የአሁኑ ጥቁር አባይ ጫማ ፋብሪካ) እና ዳርማር ጫማ ፋብሪካ (የአሁኑ አንበሳ ጫማ ፋብሪካ) በመባል ይታወቃሉ። ከጊዜ ወደ ጊዜ የዘርፉ ፋብካዎች እያደገ 34 ቆዳ ፋብሪካ የደረሰበት ጊዜ እንደነበር ይታወሳል። በአሁኑ ጊዜ ወደ 18 የቆዳ፣ 24 የጫማ እና 14 የቆዳ ዕቃዎች ፋብሪካ ሥራ ላይ እንደሚገኙ ከአምራት ኢንዱስትሪ ልማት ኢንስቲትዩት ከተገኘው መረጃ ለመረዳት ተችሏል፡፡

በሀገራችን እስከ ቅርብ ዓመታት ድረስ የውጭ ምንዛሪ በማስገኘት ረገድም ከቡና ቀጥሎ ቆዳና ሌጦ ሁለተኛ እንደነበር ይታወቃል። ኢንዱስትሪው የሀገሪቱን የኢኮኖሚ ዕድገት ከመደገፉም በተጨማሪ ለበርካታ ዜጎች የሥራ ዕድል በመፍጠር ለማኀበራዊ ዕድገትም ከፍተኛ አስተዋጽኦ እንደሚያበረክት ይታመናል። ከቅርብ ዓመታት ወዲህ ቆዳ ሀብት፣ ጤና እና ቅንጦት ነው (wealth, health & luxury) በሚልም ይገለፃል። ይህም ቆዳ ካለው ጥንካሬ፣ ምቾትና ውበት በሰው ልጅ ምን ያህል ተፈላጊ እንደሆነ መገመት ይቻላል፡፡

ሀገራችን በተፈጥሮ በተቸራት የእንስሳት ሀብትና መልከዓምድራዊ አቀማመጥ የቆዳ ኢንዱስትሪ መስፋፋት ያለው ኢኮኖሚያዊና ማኀበራዊ ጠቀሜታ የጎላ በመሆኑ በመንግሥት ልዩ ትኩረት ከተሰጣቸው ኢኮኖሚ ዘርፎች አንዱ ነው። በዚህም መሠረት ዘርፉን በዓለም ገበያ ተወዳዳሪ እንዲሆን ለማድረግ በሳይንስና ቴክኖሎጂ የሚደግፍ ተቋም መፍጠር አስፈላጊ ሆኖ በመገኘቱ በ1991 ዓ.ም. የቆዳና የቆዳ ውጤቶች ቴክኖሎች ኢንስቲትዩት እንዲቋቋም ተደርጓል፡፡

ኢንስቲትዩቱ ከተቋቋመበት ጊዜ ጀምሮ በመንግሥት ከሚመደበው በጀት በተጨማሪ መንግሥታዊ ካልሆኑ የልማት አጋር ድርጅቶች ጋር ግንኙነት በመፍጠር ዘርፉን ለመደገፍ የሚያስችል የተሟላ ተቋማዊ አደረጃጀት ከመፍጠር ጎን ለጎን የዘርፉን ችግር ለመፍታትና በዓለም ገበያ ተወዳዳሪ ለማድረግ እንዲቻል የተሟላ ዘመናዊ ሞዴል የቆዳ፣ የጫማ፣ የቆዳ ዕቃዎች ፋብሪካዎች እና የኬሚካል፣ ፊዚካል፣ ኢንቫይሮሜንታልና ኢንስትሩሜንታል ላቦራቶሪዎች እንዲደራጁ አደርጓል። የሰለጠነ የሰው ኃይል በማፍራት፣ በምርምር፣ በምርት ልማት፣ በቴክኖሎጂ ሽግግር እና የግብዓትና ምርት ትስስር በመፍጠርም በርካታ ተግባራትን አከናውኗል።

በመንግሥት በተሰጠው ልዩ ትኩረትም ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲና ከዘርፉ ምሁራንን ተመርው በሹመት ኢንስቲትዩቱን እንዲመሩ ተድርገዋል። ከተቋቋመበት ከ1991 ዓ.ም. ጀምሮ እስከ 2014 ዓ.ም ድረስ ኢንስቲትዩቱን የመሩት በቅድም ተከተል ዶ/ር ግዛቸው ዓለማየሁ፣ ዶ/ር ኢንጂነር በላይ ወልደየስ፣ አቶ ሰለሞን ጌቱ፣ አቶ ወንዱ ለገሠ፣ አቶ ቦጋለ ፈለቀ እና አቶ ዳኛቸው ሽፈራው ሲሆኑ በተለይም ኢንስቲትዩቱ በተሟላ ፋሲሊቲ እንዲደራጅና በአፍሪካ ደረጃ ታዋቂ የስልጠናና የምርምር ተቋም እንዲሆን የሁለቱ ዶክተሮችና የአቶ ወንዱ ለገሠ ሚና የጎላ ነበር።

ኢንስቲትዩቱ የተሟላ የኬሚካል፣ ፊዚካል፣ ኢንስትሩሜንታልና ኢንቫይሮሜንታል ላቦራቶሪ ያሉት ሲሆን ሁሉም በአንድ ቦታ ላይ መገኘታቸው በአፍሪካም ሆነ በአውሮፓ ከሚገኙ ተመሳሳይ ተቋማት የተለየ መሆኑን ከሰባት ዓመት በፊት ከእንግሊዝና ከጣሊያን የመጡ ጎብኚዎች ምስክርነት ሰጥተው ነበር። በርካታ የአፍሪካ ሀገሮች መሪዎች፣ ከፍተኛ የመንግሥት ባለሥልጣናት እና ባለሀብቶች ኢንስቲትዩቱን በተደጋጋሚ ጎብኝተዋል።

በዚህም መሠረት ከሱዳን፣ ከኬንያ፣ ከታንዛንያ፣ ከቦትስዋና፣ ከማዳጋስካር እና ከሌሎች የአፍሪካ ሀገሮች ባለሙያዎች ወደ ኢንስቲትዩቱ ተልከው በቆዳና በቆዳ ውጤቶች ሙያ እንዲሰለጥኑ ተደርጓል። ኢንስቲትዩቱ ለሀገሪቱ ቆዳ ኢንዱስትሪ የሰለጠነ የሰው ኃይል ከማፈራትና የቴክኖሎጂ ሽግግር ከማድረጉም በላይ ለሀገሪቱ የውጭ ምንዛሪ ገቢ በማስገኘትም አስተዋጽኦ እንደነበረው ያመለክታል። በተለያዩ ጊዜያት ከአውሮፓ፣ ከአሜሪካና ከኢስያ ሀገሮች የመጡ ልዑካን ቡድኖች በኢንስቲትዩቱ ባዩት ነገር መገረማቸውንና በሀገራቸው የሌለ ነገር እዚህ እንደሚገኝ በአድናቆት ሲገልጹ ነበር።

አሁን ግን ያ ሁሉም ክብርና ግርማ ሞገስ የለም። የተቋሙም አደረጃጀት ተቀይሯል። በመንግሥት ልዩ ትኩረትና መንግሥታዊ ባልሆኑ የልማት አጋሮች ትብብር ከፍተኛ ሀብት ፈስሶ የተደራጀ ተቋም የሚጠበቅበትን ያህል አገልግሎት እየሰጠ አይደለም። የአፍሪካ ቆዳ ኢንዱስትሪ ማዕከል ነው እስከመባል የደረሰ እና ከሀገር አልፎ ለአህጉር ቆዳ ኢንዱስትሪ የመሪነት ሚና ይጫወታል የተባለ ተቋም በዚህ ደረጃ ተጎሳቁሎ ሲታይ ያሳዝናል።

ሀገራችን ከቆዳ ኢንዱስትሪ ዘርፍ ያላትን የእንስሳት ሀብት የሚመጥን ጥቅም እንድታገኝ በኢንስቲትዩቱ የተጀመሩ በጣም በርካታ ጥናቶች፣ ምርምርና የምርት ልማት ሥራ ውጤቶች እንደነበሩ ይታወሳል። በኢትዮጵያ የእንስሳት ዝርያ ጭምር ተጠንቶ የትኛው ዝርያ የት አካባቢ እንደሚገኝና ለየትኛው የቆዳ ውጤቶች ምርት እንደሚያስፈልግ በምርምር የተለየውም በኢንስቲትዩቱ ነው። ይህ ብቻ አይደለም የጥሬ ቆዳና ሌጦ ብክነትን ለመቀነስና ለዜጎች በርካታ የሥራ ዕድል ለመፍጠር የሚያግዝ በየአካባቢው አነስተኛ የቆዳ ክላስተር እንዲቋቋም አዋጭነቱ ተጠንቶና ፕሮጀክት ተቀርጾ ለመንግሥት የቀረበውም በዚህ ኢንስቲትዩት ነው። ሀገራችን “የኢትዮጵያ ሃይላንድ ሺፕ ስኪን (ETHIOPIAN HIGH LAND SHEEP SKIN) ብራንድ እንዲኖራት የኢንስቲትዩቱ ሚና ከፍተኛ ነበር።

በየአካባቢው በቆዳና ሌጦ ንግድ ላይ የተሰማሩ ነጋዴዎች ቆዳና ሌጦ ለመሰብሰብ የሚያወጡት ወጪ እና ነጋዴው የሰበሰበውን ቆዳና ሌጦ ለማዕከላዊ ገበያ ለማቅረብ ሲጓዝ ለምግብና ለአልጋ የሚያወጣው ወጪ ከትራንስፖርት ወጪ ጋር ሲጨመር ቆዳና ሌጦን ለማዕከላዊ ገበያ አቅርቦ ሽጦ ከሚያገኘው ዋጋ ጋር የሚመጣጠን ባለመሆኑ ሥራውን ለማቆም ይገደዳል። በመሆኑም ቆዳና ሌጦን በባለቤትነት የሚሰበሰብ አካል ስለማይኖር በየአካባቢው እየተጣለ ይባክናል።

በዚህም ምክንያት ቆዳና ሌጦ ተመርቶ በመሸጥ ለሀገር የሚያስገኘው ኢኮኖሚያዊ ጥቅም ይቀራል። በየቦታው በሚጣል ቆዳና ሌጦ ሽታ የሕብረተሰቡ ጤና ይታወካል። በቆዳና ሌጦ ንግድ ላይ የተሰማሩ ሥራ ስለሚፈቱ የሥራ አጥ ቁጥር ይጨምራል። ነገር ግን በኢንስቲትዩቱ የተቀረፀው ፕሮጀክት ተግባራዊ ቢደረግ ከላይ የተጠቀሱት ችግሮችእንዲቀረፍ ከፍተኛ አስተዋጽኦ ያደርጋል።

ወጣቶች ተደራጅተው ወይም በግላቸው ቆዳና ሌጦን እየሰበሰቡ በአካባቢው ለሚገኘው የቆዳ ኢንዱስትሪ ክላስተር እንዲያቀርቡ በማድረግ የሥራ ዕድል መፍጠር ይቻላል። አለአግባብ የሚባክነው ጥሬ ቆዳና ሌጦን ወደ ምርት በመቀየር ለኢኮኖሚ እድገት አስተዋጽኦ እንዲያደርግ ማድረግ ይቻላል። ቆዳና ሌጦ በወቅቱ ተሰብስቦ ወደፋብሪካ ስለሚቀርብ ተጥሎ ለአካባቢ ብክለት ምክንያት ሊሆን አይችልም፡፡

የቆዳ ኢንዱስትሪ ዘርፍ አሁን ያለበት ደረጃ እንዲደርስ ካደረጉት ምክንያቶች አንዱ አዲሱ አደረጃጀት ነው ብዬ አስባለሁ። ምክንያቱም የሀገሪቱ የቆዳ ኢንዱስትሪ በከፍተኛ ሁኔታ ያሽቆለቆለው ይህ አደረጃጀት ከተፈጠረ በኋላ ነው። የኢንስቲትዩቱን አደረጃጀት ለመለወጥ የዘርፉን ታሪካዊ አመጣጥና የዕድገት ደረጃውን እንዲሁም የተቋሙ የሰው ኃይልና የንብረት አደረጃደት በጥልቀት መታየት ነበረበት።

ቀደም ሲል የነበረው የኢንስቲትዩቱ አደረጃጀት የሌሎች ሀገሮች ተሞክሮና የሀገሪቱን የቆዳ ኢንዱስትሪ ነባራዊ ሁኔታን በስፋት በማጥናት ነው። በመሆኑም ነው በአፍሪካ ብቻ ሳይሆን በዘርፉ ሳይንስና ቴክኖሎጂ የላቀ ደረጃ የደረሱ የእንግሊዝና የጣሊያን ባለሙያዎች ጭምር አድናቆት የቸሩት። አሁን ለሚታየው ችግር አንዱ ምክንያት የተቋሙ አደረጃጀት ጥናት ሲካሄድ ስለዘርፉ በቂ እውቀት ያላቸው ባለሙያዎች እንዲሳተፉ አለማድረግ ሊሆን ይችላል የሚል እምነት አለኝ፡፡

ይህን ዘርፍ ለማሳደግና ተወዳዳሪ ለማድረግ እንዲሁም ዘርፉን የሚደግፈውን ተቋም በተሟላ ቁሳዊና ሰብአዊ ሀብት ለማደራጀት እና አቅም ለመገንባት በመንግሥት በኩል ከፍተኛ ሥራ ተሠርቷል። የአፍሪካ አኅጉር ማዕከል ለማድረግ የሚያስችል ሥራም ተሠርቷል። የመላው አፍሪካ የቆዳ ንግድ ትርዒት በአዲስ አበባ እንዲዘጋጅም ማድረግም አንዱ ማሳያ ነው።

ይህ ንግድ ትርዒት በአዲስ አበባ እንዳይዘጋጅ ከግብጽ መንግሥት በተደጋጋሚ ጠንካራ ተቃውሞ ቢቀርብም በመንግሥት ልዩ ትኩረትና ብርቱ የዲፕሎማሲ ሥራ በየዓመቱ በአዲስ አበባ መዘጋጀቱ እንዲቀጥል ተደርጓል። ነገር ግን የ14ኛው የመላው አፍሪካ ቆዳ ትርዒት መቀዛቀዝ ድሮውንም የሆነ ቀዳዳ መከፈትን ሲጠብቅ ለነበረ ተቀናቃኝ ሀገር በትግሉ እንዲቀጥል መንገድ የሚከፍት ነው። ይህም የንግድ ትርዒቱ ባለቤት ለሆነው ለኢትዮጵያ ቆዳ ኢንዱስትሪዎች ማኀበርና ዘርፉን ለሚመራው በአምራች ኢንዱስትሪ ልማት ኢንስቲትዩት ለቆዳና ቆዳ ውጤቶች ኢንዱስትሪ ምርምርና ልማት ማዕከል ጠንካራ የማስጠንቀቂያ ደወል ነው። ይህን ንግድ ትርኢት ማዳከም ለተቀናቃኞች እጅ መስጠትና የሀገርን ጥቅም አሳልፎ መስጠት ስለሚሆን እነዚህን አካላት በኃላፊነት ሊያስጠይቅ የሚችል ነው።

በመጨረሻም የሀገሪቱ ቆዳ ኢንዱስትሪ ከነበረበት ከፍታ ወርዶ መሬት ላይ ሊከሰከስ እየተንደረደረ ነው። በዘርፉ መውደቅ ሊያስከትል የሚችለው ኢኮኖሚያዊና ማኀበራዊ ቀውስ ቀላል አይሆንም። የችግሩ ገፈት ቀማሽ የተወሰኑ አካላት ብቻ ሊሆኑ አይችሉም። ስለሆነም የሚመለከታቸው አካላትና መላው ሕብረተሰብ ዘርፉ ስለሚያንሰራራበት ሁኔታ ማሰብና የመፍትሔ አካል መሆን ይኖርባቸዋል። አሁን ካለበት ችግር ለማውጣት በተለይም የመንግሥት፣ የማኀበሩና የባለሀብቶች ትኩረትና ብርቱ ጥረት ወሳኝ ነው። በእኔ እምነት ዘርፉን ከውድቀት ለመታደግ እና ወደነበረበት ከፍታ ለመመለስ የሚከተሉት ሥራዎች በፍጥነት ቢሠሩ ይሻላል እላለሁ፡፡

  1. ከጠረፍና ራቅ ካሉ ቦታዎች ጥሬ ቆዳና ሌጦን ለማዕከላዊ ገበያ ለማቅረብ አሁን ባለው የማጓጓዣና የአበል ወጪ መጨመር ምክንያት አዋጭ አይደለም። ይህን ችግር ለመፍታት፣ በየአካባቢው እየተጣለ አካባቢው የሚበክለው ቆዳና ሌጦ ጥቅም ላይ ለማዋል፣ በየአካባቢው ለሚገኙ ሥራ አጥ ወጣቶች የሥራ ዕድል ለመፍጠር እና በየአካባቢው የሚገኙ የቆዳ ውጤቶች አምራቾች ለምርታቸው ግብዓት የሆነውን ቆዳ ከአጠገባቸው ሊያገኙ እንዲችሉ ቀደም ሲል በቆዳ ኢንዱስትሪ ልማት ኢንስቲትዩት ተጠንቶ የነበረው የቆዳ ኢንዱስትሪ ክላስተር በየአካባቢው የማደራጀት ጥናት በፍጥነት ተግባራዊ ማድረግ፣
  2. የጥሬ ቆዳና ሌጦ ብክነትን ለመቀነስ የቆዳና ሌጦ ነጋዴዎች ጋር የጋራ መድረክ በመፍጠር ችግሮችን በግልጽነት በመነጋገር መለየትና መፍታት፣ ነጋዴዎቹና የቆዳ ፋብሪካ ባለቤቶች ተቀራርበውና ተመካክረው ችግሮችን በጋራ የሚፈቱበትን ሁኔታ ማመቻቸትና መደገፍ፣ እንዲሁም ቀደም ሲል እንደነበረው የጥሬ ቆዳና ሌጦ ነጋዴዎች የኢትዮጵያ ቆዳ ኢንዱስትሪዎች ማኀበር አባል ሆኖ የመፍትሔ አካል እንዲሆን ማድረግ፣
  3. ዘርፉን የሚመራው የቆዳና ቆዳ ውጤቶች ኢንዱስትሪ ምርምርና ልማት ማዕከል አደረጃጀት በመንግሥት ልዩ ትኩረት ተሰጥቶ አሁን ያለው አደረጃጀት በባለሙያ ተጠንቶ ቀደም ሲል ወደነበረበት ቀጥታ ለኢንዱስትሪ ሚኒስቴር ተጠሪ የሆነ ተቋም (ኢንስቲትዩት፣ ኮሚሽን፣ ኤጀንሲ …) ሆኖ እንዲደራጅ ማድረግ፣
  4. የቆዳ ፋብሪካዎች እና የቆዳ ውጤቶች አምራቾች ተቀናጅተው በመሥራት ኢንዱስትሪዎቹንና ሀገሪቱን ተጠቃሚ ሊያደርግ የሚችል የአሠራር ማኑዋል/መመሪያ ማዘጋጀት፣ ከጥሬ ቆዳና ሌጦ ሰብሳቢዎች እስከ የምርቶች መዳረሻ ገበያ ድረስ ባሉት እርከኖች ያሉ ተዋናዮች በሙሉ ኃላፊነታቸውን በአግባቡ እንዲወጣ ግንዛቤ በመፍጠር የቅርብ ክትትልና ድጋፍ ማድረግ፣ በመንግሥት በኩል የሚደረጉ ድጋፎች የዘርፉን ነባራዊ ሁኔታ ያገናዘበ እንዲሆን ማድረግ፣
  5. በየዓመቱ የሚዘጋጀው የመላው አፍሪካ ቆዳ ንግድ ትርዒት ወደቀድሞ ውበቱና ድምቀቱ ተመልሶ በርካታ የሀገር ውስጥና የውጭ ሀገር ተሳታፊዎች እንዲታደሙ ለማድረግ እንዲችል የኢትዮጵያ ቆዳ ኢንዱስትሪዎች ማኀበርን የትርዒት ዝግጅትና የኮሙኒኬሽን (Event organization and Communica­tion) አቅም በመገንባት መደገፍና ማጠናከር፣ የንግድ ትርዒቱ ዝግጅትና የማስተዋወቅ ሥራ በመንግሥትና በማኀበሩ ዓመቱን ሙሉ እንዲሆን ማድረግ፣ የውጭ ሀገር ተሳታፊዎች ቁጥር ከፍ እንዲል በመንግሥት በኩል ከፍተኛ የዲፕሎማሲ ሥራ መሥራት፣
  6. የዘርፉ ችግር የሚፈታው በአንድ ወገን ጥረት ብቻ ስለማይሆን ቀደም ሲል ሲደረግ እንደነበረው በዓመታዊ ዕቅድ ላይ ባለሀብቶች ተወያይተው የዘርፉን ዕቅድ የጋራ እንዲያደርጉ ማድረግ፣ በየሦስት ወሩ ከፍተኛ የመንግሥት ኃላፊዎች፣ የኢንዱስትሪው ባለቤቶችና ስለዘርፉ በቂ እውቀት ያላቸው ታዋቂ ግለሰቦች ተገናኝተው በዕቅድ አፈፃፀም ላይ እየተወያዩ በአፈፃፀም ያጋጠሙ ችግሮችን በጋራ ለመፍታት የየራሳቸው ድርሻ ሊወስዱ የሚችሉበት የውይይት መድረክ ማዘጋጀት፣
  7. የዘርፉ ኢንዱስትሪዎች በውጭ ሀገርና በሀገር ውስጥ በሚዘጋጁ ኤግዚቢሽኖች፣ ባዛሮችና ሴሚናሮች እየተሳተፉ ልምድ እንዲቀስሙ፣ ገበያ እንዲያፈላልጉና ምርቶቻቸውን እንዲሸጡ በመንግሥትና በልማት አጋሮች በኩል ልዩ ድጋፍ ማድረግ፣ አፈፃፀሙን በትኩረት መከታተልና ድክመቶች ካሉ በፍጥነት እንዲታረሙ ማድረግ፣ … ወዘተ

ይህን አስተያየት ስጽፍ ማንንም ለመጉዳት ወይም ለመውቀስ ሳይሆን ለበርካታ ዓመታት በዘርፉ ውስጥ እንደመኖሬ በተለይ ዘርፉን የሚደግፈው ተቋም ከነበረበት ከፍታ ወርዶ አሁን ያለበት ደረጃ ላይ መሆኑና የዘርፉ መቀዛቀዝ ውስጤን ስለረበሸው ዘርፉን ወደነበረበት ደረጃ እንዲመለስ የበኩሌን አስተዋጽኦ ለማበርከት ከዚህ ልጀምር ብዬ ነው። ምናልባት ስጽፍ የተሳሳተ መልዕክት አስተላልፌ ከሆነም እንድታርሙኝ እየጠየቅሁ፣ ጽሁፌ ያስከፋችሁ አካላት ካላችሁም ትኩረቴ የቆዳ ኢንዱስትሪ ዘርፍንና የሀገር ጥቅምመሠረት ያደረገ መሆኑን እንድትረዱልኝ እፈልጋለሁ። በቀጣይ እንደሁኔታው ስለዘርፉ ያለኝንና የማውቀውን ለማካፈል እሞክራለሁ። አመሰግናለሁ።

ይህ አምድ በተለያዩ ፖለቲካዊ ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ጉዳዮች ዙሪያ ዜጎች ነፃ ሀሳባቸውን የሚሰጡበት ነው።በዓምዱ ላይ የሚወጡ ጽሁፎች የዝግጅት ክፍሉን አቋም አያመለክቱም።

በብርሀኑ ሰርጀቦ

አዲስ ዘመን ማክሰኞ ግንቦት 26 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You