
መስጠት ከበጎነት ይወለዳል፤ በጎነት ደግሞ ከቅን ልብና ልቡና ይፈልቃል። ቅን ልብና ልቡና በሃሳብ ጎልብቶ፣ በበጎነት ተግባር ግዘፍ ሲነሳ ደግሞ፤ የሚሊዮኖችን ጉድለት ይሞላል፤ የሚሊዮኖችን ድካም ይቀንሳል፤ የሚሊዮኖችን የጨለማ መንገድ አጥርቶ እንባቸውን ያብሳል፡፡
በዚህ መልኩ የሚገለጹ የዓለማችን ብርቅዬ ሰዎች እና ተቋማት መካከል ደግሞ አንዱ የዓለማችን ቱጃር የሆነው ቢልጌትስ እንደ ግለሰብ፤ ቢል እና ሚሊንዳ ጌትስ ፋውንዴሽን ደግሞ እንደ ድርጅት የአንድ ሳንቲም ሁለት ገጽታ ሆነው ሩብ ምዕተ ዓመታትን ዘልቀዋል፡፡
የማይክሮሶፍት መስራቹ ቢል ጌትስ እና ፋውንዴሽኑ፣ ከ25 ዓመት ለተሻገረው የበጎነት ተግባሩ ከ100 ቢሊዮን ዶላር በላይ ከሀብቱ ላይ ወጪ አድርጓል። በቅርቡ እንኳን የዓለማችን ስጋት ሆኖ የቆየውን ኮሮና ቫይረስ ለመከላከል እንዲውል 330 ሚሊዮን ዶላር መድበው ሠርተዋል። በምስራቅ አፍሪካ የአንበጣ መንጋ በተከሰተ ወቅትም፣ ከ10 ሚሊዮን ዶላር በላይ በመመደብ የአንበጣ መንጋውን የመከላከል ሥራ እንዲሠራ በማድረግ የግብርናው ዘርፍ አጋርነታቸውንም አረጋግጠዋል፡፡
በዚህ እና መሰል በጤናውም፣ በግብርናውም፣ በቴክኖሎጂና ሌሎች መሠረተ ልማት ተግባራት የበጎነት ሥራውም በመላው ዓለም ላይ ያሉ የሰው ልጆችን ያገዙበትን ተግባር መፈጸም ችሏል። ከእነዚህ የበጎነት ተግባሩ ተጋሪ ከሆኑ ሕዝቦች መካከል ደግሞ ኢትዮጵያውያንም ይገኙበታል፡፡
ቢል ጌትስ እና ፋውንዴሽኑ፣ በኢትዮጵያ ዘርፈ ብዙ ተግባራት ላይ ባደረገው እና እያደረገው ባለው የበጎነት ተግባር፤ ሚሊዮኖችን መድረስ ችሏል። የሚሊዮኖች ጉርስ፤ የሚሊዮኖች ጤና፤ የሚሊዮኖች የመሠረተ ልማት እና የቴክኖሎጂ አቅም መሆን ችሏል። ምክንያቱም፣ በእነዚህ ዓመታት በግብርና፣ በጤና፣ በመሠረተ ልማት፣ በሳይንስና ቴክኖሎጂ፤ አሁን ላይም ኢትዮጵያ ለጀመረችው የዲጂታላይዜሽን ጉዞ ላይ ዐሻራውን እያሳረፈ ይገኛል፡፡
በዚህ መልኩ ዘመኑን ለበጎነት ሰጥቶ፣ ሀብቱንም ለመልካምነት አበርክቶ የዘለቀው ቢል ጌት፤ በቀጣይ 20 ዓመታትም ሀብቱን ለዚሁ የበጎነት ተግባር እንዲውል ለሌሎች ሊሰጥ ማቀዱን በቅርቡ ይፋ አድርጓል። በዚህ መሠረትም በእነዚህ ዓመታት የሀብቱን 99 በመቶ የሚሆነውን፤ ወደ 200 ቢሊዮን ዶላር የሚገመት ገንዘብ በርዳታ ድርጅቱ (በቢል እና ጌትስ ፋውንዴሽን) በኩል ለመስጠት፤ እአአ በ2045 ሥራ እንደሚያቆም ነው የተገለጸው፡፡
ይሄ ተግባሩም፣ እርሱ ካለፈ በኋላ ሰዎች ስለ እርሱ ምንም ሊሉ ቢችልም፤ “ሀብቱን ይዞ ሞተ” ሊሉ እንደማይችሉ ግን የሚያረጋግጥ ነው። ከዚህም በላይ ይሄ ተግባሩ የብዙዎችን ጓዳ የመድረስ የበጎነት አብነት፣ ለብዙዎች አረዓያ የሚሆን ነው። ኢትዮጵያ እና ኢትዮጵያውያንም ትናንት፣ ዛሬ እና ነገ በዚሁ አግባብ የበጎነቱ ተቋዳሽ ሆነው የዘለቁ ናቸው፡፡
ኢትዮጵያም በችግሯ የደረሰላትን፤ በጉድለቷ ያገዛትን፤ የልጆቿን እንባ ያበሰላትን፤ ምግብም፣ ጤናም፣ ቴክኖሎጂም፣… በደጃቸው እንዲደርስ ያገዛቸውን የበጎነት ባለውለታ ዝም ብላ አላለፈችም። ቀደም ባሉት ጊዜያት በመሪዎች ደረጃ ምስጋና አቅርባለች። ለምሳሌ፣ ነሐሴ 2016 ዓ.ም ኢትዮጵያን በጎበኙበት ወቅት፣ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ቢል እና ሜሊንዳ ጌትስ ፋውንዴሽን በኢትዮጵያ በግብርና፣ በጤና እና የፋይናንስ ዘርፉን አካታች ለማድረግ በሚደረጉ ጥረቶች ለሚያደርግልን ያልተቋረጠ ድጋፍ ምስጋናቸውን አቅርበዋል፡፡
ከሰሞኑም፣ ኢትዮጵያ በበጎነት ያገለገላትን ቢል ጌት፣ በብሔራዊ ቤተ መንግሥት በተካሄደ ሥነ ሥርዓት ታላቁን የክብር ኒሻን ሰጥታ አክብራለች። ይሄንን አስመልክቶም ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ በማህበራዊ ትስስር ገጻቸው እንዳሰፈሩት፤ “ይኽ የከበረ ሽልማት የጌትስ ፋውንዴሽን ባለፉት 25 ዓመታት በኢትዮጵያ ላበረከታቸው አሻጋሪ ሥራዎች እና ታላላቅ ዘመን ተሻጋሪ በጎ ተፅዕኖዎችን ያከበረ ነው” ብለዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ አያይዘውም፣ ለቢል ጌትስ ፋውንዴሽን የ25 ዓመታት አሸጋጋሪ ሥራዎች ምስጋና ያቀረቡ ሲሆን፤ ቢል ጌትስ ከቴክኖሎጂ ፈር ቀዳጅነት ወደ በጎ አድራጊነት ያደረጉትን ጉዞ በማውሳትም ዝቅ ብሎ በማገልገል፣ በአክብሮት እና በእኩልነት እምነት ላይ ለተመሠረተው አገልግሎታቸው አድናቆታቸውን ገልጸዋል፡፡
ፋውንዴሽኑ በጤና፣ ግብርና፣ ዲጂታል መታወቂያ የሚያደርገው ጥረት ብሎም ጠንካራው በመከባበር ላይ የተመሠረተ ትብብር እንደመሆኑ፤ ኢትዮጵያም በታላቁ ሊሻን ይሄን ባለውለታዋን ማክበሯ ከፍታዋን የሚገልጽ ከመሆኑ ባሻገር፤ ሌሎች መሰል በጎዎች እንዲበራከቱ የሚያደርግ ነው፡፡
አዲስ ዘመን ማክሰኞ ግንቦት 26 ቀን 2017 ዓ.ም