ቢል ጌትስ የኢትዮጵያ ታላቁን የክብር ኒሻን ተሸለሙ

በብሔራዊ ቤተመንግሥት ከትናት በስቲያ ምሽት በተካሄደ ሥነሥርዓት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) የኢትዮጵያን ታላቁን የክብር ኒሻን ለቢል ጌትስ ሸልመዋል። ሽልማቱ የቢል ጌትስ ፋውንዴሽን ባለፉት 25 ዓመታት በኢትዮጵያ ላበረከታቸው አሻጋሪ ሥራዎች እና ታላላቅ ዘመን ተሻጋሪ በጎ ተፅዕኖዎችን ያከበረ እንደሆነም ተገልጿል ።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በሽልማት ሥነሥርዓቱ ላይ ባስተላለፉት መልእክት ፣በእለቱ በአንድ ላይ የተሰበሰብነው ላለፉት 25 ዓመታት የሚሊዮኖችን ሕይወት ለቀየረው ቢል ጌት በፋውንዴሽን እና ለቢሊጌት ያለንን ልባዊ ምስጋና ለመግለጽ ነው ብለዋል፡፡

“የሠራኸው ሥራ የእውነተኛው ኑሮ መለኪያ ያለን ሳይሆን ለሌሎች የሰጠነው መሆኑን አሳይቶናል” ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ ፣ ቢል ጌትስ ፤በጥንካሬ እና በዓላማ የሚጓዝ ፤ የማወቅ ጉጉቱ በሳይንስ፣ በጤና እና በሠብዓዊነት ከፍታ ላይ ያደረሰው ሰው እንደሆነም አመልክተዋል ፡፡

ካለው ሀብት ወይም ዝና በላይ መልካምነቱ እና ተፅኖው የበለጠ ተደራሽ ሆኗል፡፡ ዛሬ በሕዝብ ዘንድ በበጎ አድራጊነት ከመታወቃቸው በፊት ዓለምን ቅርጽ ለማስያዝ የቻሉ ፤ በማይክሮ ሶፍት ድርጅት መሥራችነት የዲጅታሉ ዘርፍ የጀርባ አጥንት በመሆን ለዘመናዊነት መሠረት የጣሉ ፤ ለውጥ የሚወረስ ሳይሆን፤ የሚፈጠር መሆኑንም ያሳዩ እንደሆኑም ጠቁመዋል፡፡

በሲያትል ሆነ በሲዳማ ውስጥ እያንዳንዱ ሕይወት እኩል ዋጋ እንዳለው በማክበር እና በማመን ወደ ኢትዮጵያ በመምጣት ፤ ላለፈው ሩብ ክፍለ ዘመን ከነበሩ ለውጦች እና መሻሻሎች ጀርባ ትልቅ ኃይል መሆናቸውን ፤ በዚህም የመጀመሪያ ደረጃ የህክምና አገልግሎቶች ተጠናክሯል፣ በዝቅተኛ ደረጃ ያሉ አርሶ አደሮች ተደግፈዋል ፣ ሳይንሳዊ ፈጠራ እንዲስፋፋ እና በመረጃዎች የተደገፉ ውሳኔዎች ለመወሰን ረድቷል ብለዋል ፡፡

በቢል ጌትስ ፋውንዴሽን አማካኝነት በኢትዮጵያ በሀሉም ክልሎች የያንዳንዱ ግለሰብ ሕይወት ለመድረስ ተችሏል፡፡ በእለቱ የሁሉም ክልል ፕሬዚዳንቶች የመገኘታቸው ምክንያት ይህንን ለመመስከር እንደሆነ ጠቁመዋል፡፡ “ውድ ጓደኞቼ ትልቁ ነገር የተገኘው ስኬት ሳይሆን ከጀርባው ያለው መንፈስ ነው” ሲሉም ተናግረዋል፡፡

ጌት ፋውንዴሽን የኢትዮጵያን ሕዝብ እና መሪ ምኞት ያዳመጠ፣ የተረዳ እና ያከበረ ነው፡፡ ግንኙነቱም በጋራ መከባበር ላይ የተመሠረተ እና በጋራ ሥራ በተቋማት፣ በማህበረሰቡ እና በግለሰቦች መካከል መተማመንን የገነባ እንደሆነም አስታውቀዋል፡፡

በተለይ በሀገር ውስጥ አቅም ላይ ላሳዩት እምነት ፣ ለኢትዮጵያ፣ ለተቋሞቻችን እና ለሕዝባችን ፖለቲካዊ እና ኢኮኖሚያዊ ለውጦች ላሳዩት ጠንካራ ድጋፍ ከልብ እናመሰግናለን ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ ፤ፋውንዴሽኑ ለዓለም አቀፍ የጤና ቀውሶች እና ለተፈጥሮ ተግዳሮቶችን እንደራስ በማየት የማያወላውል አፋጣኝ ምላሽ ሲሰጥ መቆየቱንም አመልክተዋል ፡፡

ፋውንዴሽኑ ባደረጋቸው ስራዎች ለሀገራችን ህዝቡ ፍላጎት ምላሽ የመስጠት አቅም አጠናክሯል፡፡ ጤናማ፣ እኩልነት የሰፈነባት እና አካታች የሆነችውን የወደፊቷን ኢትዮጵያን ለማየት የምናገርደው ጉዞ ለብቻችን ሳይሆን፤ ግባችንን ከምናካፍላቸው እና በአቅማችን ከሚያምኑ ከእንዳንተ አይነት አጋሮቻችን ጋር ነው ብለዋል ፡፡

ቀጣዩ የወዳጅነት ምዕራፋችን የበለጠ አጓጊ፣ አካታች፣ በሀገር በቀል እውቀት እና አመራር የተመራ ሊሆን ይገባል። ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ ፤ የኢትዮጵያን ሕዝብና መንግሥት በመወከል ለጌት ፋውንዴሽን፣ ለአመራሩ ፣ ሠራተኞች እና በየትኛውም ቦታ ለ25 ዓመታት ለነበረው ጉዞ አስተዋጽኦ ላደረጉ በሙሉ ምስጋና አቅርበዋል ።

“ለዓለም ጥሩ ለማድረግ ከሀብትህ አብዛኛውን ለመመደብ የወሰንከው ውሳኔ ፣ አቅምህ እና ድምጽህ የሚደነቅ ብቻ ሳይሆን፤ ታሪካዊም ጭምር ነው። ትልቅ እንድናስብ፣ በጥልቅ ዓላማ እንድንሠራ እና በደግነት እንድንመራም ያስገድደናል። ሥራህ በርካታ ሕይወቶችን መንካቱን የሚቀጥል ነው። ለዚህም በእውነቱ እናመሰግናለን። የሠራኸው ሥራ የእውነተኛው ኑሮ መለኪያ ያለን ሳይሆን ለሌሎች የሰጠነው መሆኑን አሳይቶናል”ብለዋል ።

በዜጣው ሪፖርተር

አዲስ ዘመን ማክሰኞ ግንቦት 26 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You