
-የከተማዋ የኮሪዶር ግንባታ አፈጻጸም 60 በመቶ ደርሷል
ሰመራ፦ የሰመራ-ሎጊያ ከተማን ጽዱና ውብ እንዲሁም የቱሪስት መዳረሻ ለማድረግ ከተማ እየተሠራ መሆኑን የከተማዋ ከንቲባ አስታወቁ።
ከንቲባው አቶ አብዱ ሙሳ ሁሴን በተለይ ለአዲስ ዘመን ጋዜጣ እንደገለፁት፤ ከተማ አስተዳደሩ ከተማዋን የማስዋቡ ሥራ እየተካሄደ ያለው ከክልሉ መንግሥት እና ከተማ ልማት እና ኮንስትራክሽን ቢሮ ጋር በመሆን ነው። እነዚህ የመሠረተ ልማት ሥራዎችም ሰመራ ሎጊያን የቱሪስት መዳረሻ እና ለነዋሪ ምቹና ማራኪ ፅዱ ከተማ እንደሚያደርጓት ታምኖባቸዋል።
በከተማዋ እየተካሄደ ያለው የሁለት ኪሎ ሜትር ኮሪዶር ልማት ሥራ ግንባታም 60 በመቶ ያህል መጠናቀቁን ከንቲባው አስታውቀዋል። በኮሪዶር ልማቱ ከተካተቱት መካከልም የእግረኞችና የቢስክሌት መንገድ፣ የአረንጓዴ ውበት ቦታዎች እና መናፈሻዎች ልማት እንደሚገኙበት ጠቅሰዋል።
የኮሪዶር ልማቱ የእግር ኳስ መጫወቻ ሜዳ፣ የልጆች መጫወቻ ቦታዎችንም እንዳካተተ ከንቲባው ጠቅሰው፣ በሰመራ ከተማ እየተሠራ ያለው የኮሪዶር ልማት የአፋርን ባህልና ታሪክ ባካተተ መልኩ ዲዛይን የተደረገ መሆኑን አብራርተዋል።
ከተማዋን ፅዱና ውብ ለማድረግ ከተገነቡ መሠረተ ልማቶች መካከል አገልግሎት የጀመሩ መናፈሻዎች እንዳሉም ጠቅሰው፣ መሠረተ ልማቶቹ በሙሉ አቅማቸው ወደ ሥራ ሲገቡ ከተማዋን ማራኪና አረንጓዴ እንደሚያደርጓት አመልክተዋል። አካባቢውን በረሃማነት ከሚያስከትለው ጫና ለመታደግ እያንዳንዱ አባወራ በየቤቱ 10 እና 20 ዛፎችን እንዲተክል አቅጣጫ ተቀምጦ ተግባራዊ እየተደረገ ነው ብለዋል።
የኮሪዶር ልማቱን በፍጥነት ለማጠናቀቅ የገቢ ማሰባሰብ ሥራዎች መጀመራቸውን ከንቲባው ጠቅሰው፣ በሀገር ውስጥና በውጭ የሚገኝ ሁሉም የክልሉ ተወላጅ በገቢ ማሰባሰቡ ላይ አንዲሳተፍም ጥሪ አቅርበዋል። በቴሌ ብር 519310 እንዲሁም በንግድ ባንክ 1000692046041 የክልሉ የኮሪዶር ልማት ገቢ ማሰባሰቢያ መሆኑንም ጠቁመዋል።
የክልሉ ፕሬዚዳንት ከፌዴራል መንግሥት የመንገዶች አስተዳደር ጋር በመነጋገርም ሶስት ነጥብ አራት ኪሎ ሜትር የመንገድ ሥራ መጀመሩንም ከንቲባው አስታውቀዋል። በቻይና ኩባንያ በመሠራት ላይ የሚገኘው መንገዱ ከአሊግደይ እስከ ጅቡቲ መውጫ በኩል ግንባታው ተጀምሮ እየተሠራ መሆኑንም ከንቲባው ገልፀዋል።
ይህ በእንዲህ እንዳለ የከተማዋ ማዘጋጃ ቤት የራሱን ቁመና እንዲይዝ እና ለማህበረሰቡ ቀልጣፋና ተገቢውን አገልግሎት እንዲሰጥ ከፍተኛ ጥረት እየተደረገ መሆኑን ከንቲባው አቶ አብዱ አስታውቀዋል። ከተማዋ ከማዘጋጃ ቤታዊ ለውጥ አኳያ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ የካዳስተር አገልግሎት መጀመሩንም ጠቁመዋል።
በሰመራ ሎጊያ ሆቴሎች እየተስፋፉ መሆናቸውንም ጠቅሰው፣ ይህም ቱሪስቶችን የማስተናገድ አቅም እየጎለበተ መሆኑን እንደሚያመለክት ተናግረዋል። በከተማዋ በሆቴል ቱሪዝም ኢንቨስትመንት መሠማራት የሚፈልጉ ባለሀብቶችን ለመቀበልም ከተማዋ ዝግጁ መሆኗንም ገልፀዋል። አፋር ሰላማዊ ክልል ነው ሲሉም ጠቅሰው፣ ማንኛውም ኢትዮጵያዊ በከተማዋ ኢንቨስት እንዲያደርግ ጥሪ አቅርበዋል።
‹‹አፋር የራሱ ባሕል እና እምነት አለው። ክልሉ ማንኛውም ኢትዮጵያዊ ብሔር ብሔረሰብ እኩል የሚኖርበት ነው›› ያሉት ከንቲባው፣ የትኛውም ባለሀብት ሀብቱን በአፋር ክልል ሥራ ላይ እንዲያውል ጥሪያቸውን አቅርበዋል።
በኃይሉ አበራ
አዲስ ዘመን ሰኞ ግንቦት 25 ቀን 2017 ዓ.ም