
ተስፋዬ በልጅጌ (ዶ/ር) በኢፌዴሪ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የመንግሥት ዋና ተጠሪ ሚኒስትር
አዲስ አበባ፡- የኢትዮጵያን የፖለቲካ ባህል ለመቀየር እየተሠራ እንደሚገኝ በኢፌዴሪ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የመንግሥት ዋና ተጠሪ ሚኒስትር ተስፋዬ በልጅጌ (ዶ/ር) ገለጹ፡፡
ዋና ተጠሪ ሚኒስትሩ ለኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት እንደተናገሩት፤ ባለፉት ሰባት ዓመታት ከፍተኛ ትኩረት ተሰጥቷቸው ከተከናወኑ ተግባራት ውስጥ አንዱ የፖለቲካ ባህሉን የመቀየር ጉዳይ ነው፡፡
ከግማሽ ክፍለ ዘመን ብዙም ባልዘለለው የኢትዮጵያ የፖለቲካ ታሪክ የፖለቲካ ፓርቲዎች የተንቀሳቀሱበት መንገድ የራሱ ድክመትና ጥንካሬ የነበረው ቢሆንም በብዙ መልኩ ጉድለቶች ያሉበት መሆኑን የጠቆሙት ሚኒስትሩ፤ መንግሥት የዴሞክራሲ ሥርዓት ከመገንባት አኳያ ከትናንት የተገኙ ወረቶችን ጠብቆ ይዞ መሄድና በሂደቱም የታዩ ጥፋቶችን ማረም የሚያስችል አቅጣጫ በመከተል እየተንቀሳቀሰ ነው ብለዋል፡፡
ከፖለቲካ ፓርቲዎች ጋር በተያያዘ በታሪካችን ውስጥ አንዱ የሚታየው ድክመት የጠላትና ወዳጅ ፖለቲካ መሆኑን ጠቁመው፣ የተለያየ የፖለቲካ አመለካከት መያዝ በጽንፈኝነት እና አክራሪነት ብሎም በጠላትነት ሲያስፈርጅ ቆይቷል:: ከሁሉም በላይ ደግሞ የፖለቲካ እሳቤን በኃይል በጠመንጃ ለማፈን ተሠርቷል:: ይህም ኢትዮጵያ የእርስ በእርስ ጦርነት እና ግጭት ውስጥ እንድትቆይ አድርጓል:: አወንታዊ የሰላም ባህል እየገነባን ባለመምጣታችን ሀገራችን የኋላ ቀርነትና የድህነት ተምሳሌት ሆና ቆይታለች ነው ያሉት::
የለውጡ መንግሥት ዴሞክራሲን በተመለከተ ያለው አቋም ግልጽ መሆኑን አመላክተው፣ በኢትዮጵያውያን ባህልና እሴት ላይ የተመሠረተ ተቋማዊ መሠረት ያለው ዴሞክራሲ መገንባት አለበት ተብሎ የዴሞክራሲ ተቋማት የሚባሉት ምክር ቤቶች፣ የፍትህ ተቋማት እንዲሁም የዴሞክራሲ ተቋማት የሚባሉት ሚዲያዎች፣ የሠብዓዊ መብት ኮሚሽን፣ እንባ ጠባቂ እና ሲቪክ ማህበራት አካባቢ ያሉ የዜጎችን ተሳትፎ የሚገድቡ የፖለቲካ ምህዳሩን የሚያጠቡ አሠራሮችና አዋጆች ተሻሽለዋል:: ሕጎች ተቀይረዋል፤ አመራሩ ተጠናክሯል:: የዴሞክራሲ ተቋማቱ ነጻ፣ ገለልተኛና ብቁ ሆነው እንዲገነቡ እየተደረገ ነው ብለዋል::
በአንድ በኩል የዴሞክራሲ ጥያቄን እውን ለማድረግ ኢትዮጵያዊ ባህል፣ እሴትና ታሪክ ላይ የተመሠረተ ሕዝባዊ የዴሞክራሲ ባህል ልምምድ እንዲኖር እየሠራን ነው:: በሌላ በኩል ደግሞ ነጻ፣ ገለልተኛና ብቁ የዴሞክራሲ ተቋማቶች ሆነው ሀገርን መሸከም የሚችሉ፣ በጥቂት ቡድኖች፣ ግለሰቦች ወይም ሥልጣን ላይ ባለ መንግሥት ፍላጎት ብቻ ሳይሆን ኢትዮጵያንና የመጪው ጊዜ ትውልድን ማዕከል ያደረጉ ተቋማት እንዲገነቡ እየተሠራ ይገኛል ብለዋል::
ከለውጡ ወዲህ መንግሥት ዴሞክራሲን በተመለከተ የተለያዩ ርምጃዎችን መውሰዱን አስታውሰው፣ ለውጡ እንደመጣ እስረኞችን መልቀቅ፣ የሚዲያ ምህዳሩን መክፈት፣ የተለያዩ የፖለቲካ ፓርቲዎች ከመንግሥት ጋር ተቀራርበው እንዲሠሩ ማድረግ እና ሌሎችም መሰል ርምጃዎች የተወሰዱት የፖለቲካ ምህዳሩን ለማስፋትና የዴሞክራሲ ጥያቄ ምለሽ እያገኘ እንዲሄድ መሠረት ለመጣል መሆኑን ገልጸዋል::
በተስፋ ፈሩ
አዲስ ዘመን ቅዳሜ ግንቦት 23 ቀን 2017 ዓ.ም