
አዲስ አበባ፡– የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ከጣሊያኗ አቻቸው ጂኦርጂያ ሜሎኒ ጋር የሁለቱን ሀገራት የሁለትዮሽ ትስስር ማጠናከር በሚቻልባቸው ጉዳዮች ዙሪያ መወያየታቸውን ገለጹ፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ (ዶ/ር) በማህበራዊ ትስስር ገጻቸው ላይ ትናንት ባስተላለፉት መልዕክት፤ ‹‹የጣሊያን ጠቅላይ ሚኒስትር ጂኦርጂያ ሜሎኒን በሮም ፓላዞ ቺጊ አግኝቼ ውይይት አካሂደናል። ውይይታችን በኢትዮጵያ እና ጣሊያን መካከል የሁለትዮሽ ትስስራችንን በማጠናከር ለአዲስ ኢንቨስትመንት እና የኢኮኖሚ ትብብር እድሎችን መፍጠር ላይ ያተኮረ ነበር›› ብለዋል።
የረጅም ዘመን ወዳጅነት ላይ በተመሠረተው የሁለቱ ሀገሮቻችንን ትብብር በተለያዩ መስኮች ይበልጥ ለማጠናከር የጋራ ፅኑ አቋማችንንም እንደገና አረጋግጠናል ሲሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ገልጸዋል።
የጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤት እንዳስታወቀው፤ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ወደ ኃላፊነት ከመጡበት ጊዜ ጀምሮ ከተለያዩ የጣሊያን መሪዎች ጋር የሁለትዮሽ ትብብሮችን ለማጠናከር ሠርተዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ በጥቅምት 2015 ዓ.ም ጠቅላይ ሚኒስትር ሜሎኒ ወደ ኃላፊነት በመጡ በአጭር ጊዜ በሮም በመገኘት በምሥራቅ አፍሪካ ቀጣናዊ የሰላምና ፀጥታ እንዲሁም በልማት ረገድ ጣሊያን ለኢትዮጵያ ልማት የምታደርገውን ድጋፍ አስመልክቶ ውይይት ተደርጎ ነበር።
ከእዚህ ውይይት በኋላ መሪዎቹ ጠንካራ የሥራ ግንኙነት የመሠረቱ ሲሆን፤ ጠቅላይ ሚኒስትር ጂኦርጂያ በ2016ዓ.ም ኢትዮጵያን ጎብኝተዋል። ቀጣይ ውይይቶችም በጣሊያን እንዲሁም ሌሎች ሀገራት ላይ በተከናወኑ የባለብዙ ወገን መድረኮች ላይ ተገኝተዋል።
ጣሊያን የኢትዮጵያ ልማት ቁልፍ አጋር ናት። በኢንዱስትሪ ብሎም በጤና፣ በግብርናና ባሕላዊ ቅርስ ጥበቃ የረጅም ዘመን ደጋፊም ናት። የጣሊያን ኩባንያዎች እና የጣሊያን የልማት ትብብር ተቋም ሥራዎችን በንቃት እየደገፉ ይገኛሉ። ሁለቱ መሪዎች በመጨረሻ ስብሰባቸው ለዘላቂ ልማት እና የተሻሻለ ኢንቨስትመንት ያላቸውን የጋራ ርዕይ አረጋግጠዋል።
በጋዜጣው ሪፖርተር
አዲስ ዘመን ረቡዕ ግንቦት 20 ቀን 2017 ዓ.ም