
አዲስአበባ፡– የጡረተኞች የሥራ አገልግሎት መረጃ በወቅቱ ተደራጅቶና ተጠናቅሮ እየደረሰው ባለመሆኑ የጡረታ አበል ለመክፈል መቸገሩን የግል ድርጅት ሠራተኞች ማህበራዊ ዋስትና አስተዳደር ገለፀ። 80 ከመቶ የሚጠጋ እድሜው ለጡረታ የደረሰ ሠራተኛ በጊዜውና በወቅቱ የሥራ አገልግሎት መረጃውን ለአስተዳደሩ እንደማያቀርብም ጠቁሟል።
በግል ድርጅት ሠራተኞች ማህበራዊ ዋስትና አስተዳደር የምዝገባ መዋጮ ገቢና አበል መወሰኛ ኮርፖሬት ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር አቶ ቅዱስ ሃጎስ በተለይም ለአዲስ ዘመን እንደገለፁት፤ የተቋሙ ዋነኛ ዓላማ ሠራተኞች የጡረታ መውጪያ ጊዜያቸው ሲደርስ ከደሞዝ ወደ ጡረታ ማሸጋገርና የገቢ ምንጫቸው እንዳይቋረጥ ማድረግ ነው። ይህንን ለማድረግ የሚያስችሉ ሥራዎች በተቋሙ በኩል እየተሠሩ ቢሆንም የግል ድርጅት ሠራተኛው የተሻለ ገቢ ለማግኘት በተለያዩ ተቋማት ውስጥ ሲዘዋወር የሥራ ማስረጃ ማህደሩን አብሮ እንዳላዘዋወረ ተናግረዋል።
ይህን ተከትሎም የግል ድርጅት ሠራተኛ እድሜው ለጡረታ መድረሱን የሚያውቀው ከተቋሙ በኩል ማስረጃ እንዲያቀርብ ሲጠየቅ መሆኑንም አቶ ቅዱስ ገልፀው፤ ሠራተኞች ከአንዱ ድርጅት ወደሌላኛው ድርጅት ሲዘዋወሩ ከለቀቁበት መሥሪያ ቤት የስንብት ደብዳቤ ይዘው እንደማይሄዱና ንብረት አስረክበው የቅጥር ደብዳቤ እንደማይወስዱ፤ የግል ማህደራቸውም እንደማይዞር ጠቁመዋል።
አስተዳደሩ ደግሞ አገልግሎት የሚያሰላው በቅጥርና ስንብት ደብዳቤ በመሆኑና ይህ ማስረጃ ተደራጅቶ በወቅቱ እየደረሰው ባለመሆኑ የጡረታ አበል ለመከፈል መቸገሩን አቶ ቅዱስ አመልክተዋል።
ሠራተኞች እድሜያቸው ለጡረታ እንደደረሰ ወዲያውኑ ጡረታ ማግኘት እንዳለባቸው የሚታወቅ ቢሆንም በግንዛቤ እጥረትና በቸልተኝነት ምክንያት አስፈላጊ የሆኑ የሥራ አገልግሎት መረጃዎችን በጊዜው ለአስተዳደሩ ባለማቅረባቸው የጡረታ አበል ክፍያቸው እየዘገየ መሆኑንም ተናግረዋል።
የግል ድርጅት ሠራተኞች ጡረታችን ብለው ማሰብና ማስረጃ ማደራጀት መጀመር ያለባቸው ከተቀጠሩበት ጊዜ አንስቶ ነው ያሉት አቶ ቅዱስ፤ የሠራተኞች መረጃዎች በበቂ ሁኔታ ካልተደራጁ ምናልባት ሞት እንኳን ቢያጋጥም የቤተሰብ ገቢ የሚቋረጥበት ሁኔታ እንደሚፈጠርም ጠቁመዋል። ውጫዊ በሆነ ምክንያት የጡረታ አበል በወቅቱ ባለመወሰኑ የአስተዳደሩ አገልግሎት አሰጣጥ ላይ ጥያቄ የሚያስነሳ መሆኑንም አቶ ቅዱስ ጠቅሰዋል።
ሁሉም የግል ድርጅት ሠራተኞች ጡረታ የሚወረስ ከመሆኑ አኳያ ለተተኪዎች በሚመች መልኩ ማስረጃዎችን አስቀድመው ማደረጀትና መሥሪያ ቤቶችን ሲቀይሩ የግል ማህደራቸውን አብረው ማዞር እንደሚጠበቅባቸው አሳስበዋል።
ቅጥር ሲፈፅሙም ወደ አስተዳደሩ ቀርበው መረጃቸውን ማያያዝ እንደሚኖርባቸው ጠቁመዋል። ይህም የጡረታ እድሚያቸው ሲደርስ ሳይቸገሩ የጡረታ አበል ክፍያቸውን ወዲያውኑ ማግኘት እንደሚያስችላቸው አቶ ቅዱስ ገልፀዋል።
ሰማንያ ከመቶ የሚጠጋ እድሜው ለጡረታ የደረሰ ሠራተኛ በጊዜውና በወቅቱ የሥራ አገልግሎት መረጃውን ለአስተዳደሩ እንደማያቀርብም ገልፀዋል።
በአስናቀ ፀጋዬ
አዲስ ዘመን ማክሰኞ ግንቦት 19 ቀን 2017 ዓ.ም