አሰልጣኝም ሰልጣኝም ከማይተዋወቁበት የስፖርታዊ የአካል እንቅስቃሴ ማዘውተሪያ ከሆነው መስቀል አደባባይ በማለዳ ተገኝቻለሁ፡፡ ያለ ፆታና ያለ ዕድሜ ገደብ ፍላጎት ያሰባሰባቸው ሰዎች በሕብረት ይሠራሉ፡፡ በማለዳው ውርጭ ከፊታቸው ነጭ ላብ ችፍ ብሎ በጉንጫቸው ኮለል ይላል፡፡
ከመካከላቸው አንድ ወጣት የውሃ ኮዳውን አንስቶ አንደቅድቆ ጠጥቶ የለበሰውን ቁምጣ እያሻሸ ወደ አንደኛው የአደባባዩ ጠርዝ አመራ፤ ብዙም ሳይርቅ እስከ ወገብ ድረስ በሚከልልና ለዚሁ ታስቦ በተዘጋጀ ቦታ ፍላጎቱን አሟልቶ ተመለሰ፡፡ ቀጥሎም በርካቶች ሲጠቀሙ ታዘብኩና ጉዳዩን ጉዳዬ አድርጌ አጣራሁ፡፡ ሌሎችም ተጨማሪ በጎ ሥራዎች በበጎ ፈቃደኛ ወጣቶች ሲከወኑ (ሜዳው ሲጸዳ) ተመለከትኩ፡፡
በበጎ ፈቃደኛ ወጣቶች ሥራ ሲገለገል ያገኘነው ወጣት አመሃ ሲሳይ እንደሚለው፤ ‹‹ማንኛውም ነገር በቦታውና በሰዓቱ ሲገኝ ፋይዳው ከፍተኛ ነው፡፡ የእነዚህን ቅን ወጣቶች ሥራ ማድነቅ ያሥፈልጋል፡፡ ሲያዩት ቀላል የሚመስል ግን መሰረታዊና አስፈላጊ ሥራ ነው፡፡ ለተመለከቱትና በሰፊው ላስተዋሉት ችግር መፍትሄ ሰጥተዋል፡፡ እንደምታየው የሚጠቀሙት ሰዎች ብዙ ናቸው፡፡ ይሄንም እያዩ በርካቶች አጥር ተደግፈው ሲሸኑ ትመለከታለህ፡፡
‹‹የእኛ ማህበረሰብ በማያሳፍረው ሲያፍር፤ በሚያሳፍረው ደግሞ ሲመፃደቅ ታየዋለህ፡፡ ብዙ ነገሮች ላይ መለወጥና መዘመን ያሥፈልገናል፡፡ ወጣቶችም ከፊት እየቀደምን በበጎ ፈቃድ ሠርተን ማሳየትና መተግበር አለብን፡፡ ወጣቱ በማንኛውም ነገር መቅደም አለበት፤ ከኋላ የሚጎተት ከሆነ የሀገር ለውጥም እንደዚያው አዝጋሚ የሚሆን ይመስለኛል፡፡ ከእነዚህ አዛኝ ወጣቶች ብዙ ተምሬያለሁ፡፡ አስተሳሰባችን በሕዝብ አገልጋይነት መቃኘት አለበት፤ በተለይም ወጣቱ ግዴታ አለበት ብዬ አምናለሁ›› ብሏል፡፡
የመስቀል አደባባይ ሰማያዊ ታክሲ ላዳ ማህበር ምክትል ሰብሳቢ ወጣት አቡ ወንድሙ እንደገለፀው፤ ‹‹የማህበሩ አባላት ወጣቶች ሲሆኑ በበጎ ፈቃደኝነት ብዙ ሥራዎች በመሥራት ላይ እንገኛለን፡፡ አነሰ በዛ ሳንል በማህበረሰቡ ዘንድ የምናስተውላቸውን ችግሮች ለመቅረፍ የሌላ አካል እገዛን ቆመን አንጠብቅም፡፡ ራሳችን፣ የአካባቢያችን ነዋሪ እና መስቀል አደባባይ ለሥራ የተገኘ ባለጉዳይ ለበሽታና ለሌሎች ተያያዥ ችግሮች እንዳይጋለጥ በአቅማችን ቆሻሻን ለማጽዳት እየሞከርን ነው፡፡
ይህን ማድረጋችን ደግሞ ለሰፈራችን ውበት፣ ለአካባቢያችን ተመራጭነት ብሎም ለሀገር የገጽታ ግንባታ ጠቃሚ ነው፡፡ የሚያኮራና የማያሳፍር ተግባር መፈፀም የሚያኮራ ከመሆኑም በላይ በራስ መተማመን ይፈጥራል፡፡ እኛም ያደረግነው ይሄን ነው፡፡›› ሲል ነግሮኛል፡፡
መስቀል አደባባይ በርካታ ትዕይንቶች የሚስተናገዱበት ቦታ ነው፡፡ የባስ መናኸሪያ፣ የስፖርታዊ እንቅስቃሴዎች መከወኛ፣ የወጣቶች ጊዜ ማሳለፊያ (መዝናኛ)፣ የውጭም ሆነ የሀገር ውስጥ በርካታ ዜጎች መተላለፊያ ነው፡፡ በመሆኑም ጽዳቱ ሊጠበቅ ይገባል፡፡
‹‹እኛ የሥራ ቦታችን እዚህ በመሆኑ ብዙ ነገር እንታዘባለን፡፡ ያንን መነሻ በማድረግ ለችግሮች መፍትሄ የሚሆኑ ተግባራትን ከገን ዘባችን እስከ ጉልበታችን ድረስ አስተዋጽኦ እያደረግን በፍላጎታችን እየሠራን ነው፡፡›› ብሎ አጫውቶኛል፡፡
የአካባቢው መቆሸሽ ለአይንም አስቀያሚ ነው። ለሥራም እንቅፋት መሆኑ አይቀርም፡፡ ስለዚህ ‹ከሌሎች አካላት መፍትሄ ለምን እንጠብቃለን› በሚል ተነጋግረን የማህበሩ አባላት በጉልበታችን መሥራት መጀመራቸውን ያስታውሳል፡፡ ጠቅላይ ሚንስትሩ ሀገራዊ የጽዳት ዘመቻ ከማወጃቸው ቀደም ብሎ ነው ሥራ እንደጀመሩ የሚናገረው። እስከአሁን ድረስ በየ15 ቀኑ በቋሚነት እያፀዱ መሆኑንም ይናገራል፡፡
ከዚህ በፊት መስቀል አደባባይ ዙሪያውን የወዳደቁ ቆሻሻዎች ተከማችተው ይታዩ ነበር። ከዚህ በተጨማሪ ማንኛውም አካል ያለከልካይ በየጥጋጥጉ የሚሸናበት ስለነበር መጥፎ ጠረን ነበረው፡፡ ቆመን እስከመጠበቅ ሞክረናል ነገር ግን ዘላቂ መፍትሄ ሆኖ አላገኘነውም፡፡ በሰውም ላይ አትፈርድበትም ምክንያቱም ከጤና ጋር በተያያዘ መቆጣጠር የሚቸገር ብዙ ሰው ትመለከታለህ፡፡
በየአካባቢው እንዳይሸና የሚያግዙ ሥራዎች ተሠርተዋል፡፡ በየማዕዘናቱ 8 ያህል ቦታ ተዘጋጅቶ ማህበረሰቡ እንዲጠቀም እያደረግን ነው፡፡ በሸራ በተከለለው የተፈቀደ ሽንት ማስወገጃ ውስጥ ሁለት ማጠራቀሚያዎች አገልግሎት እየሰጡ መሆናቸውን አጫውቶናል፡፡ ህፃናት፣ ህመም ያለባቸውና ሽማግሌዎች በነፃ ይጠቀማሉ፡፡ ሌሎች ሰዎች ግን ከተጠቀሙ በኋላ አንድ ብር እንዲከፍሉ በተዘጋጀው ሳጥን ውስጥ ያስገባሉ፡፡
ይሄ ሳንቲም ተሰብስቦ ደግሞ ለሌላ በጎ አላማ ይውላል፡፡ ለችግር ለተጋለጡ የመስቀል አደባባይ አካባቢ የጎዳና ህፃናት መሰረታዊ ፍላጎት ማሟያ ይሆናል፡፡ በጣም አነስተኛ ቢሆንም የገቢ ምንጭ እንደፈጠሩላቸው ገልጿል፡፡
የአውቶብስ መጫኛና ማውረጃ ከሆነ ወዲህ ደግሞ የመፀዳጃ ቤት ፈላጊውና የተጠቃሚው ቁጥር በእጅጉ እንደጨመረ የሚናገረው ወጣት አቡ ቢያንስ ከ12 በላይ መጠቀሚያ ያስፈልግ እንደነበረ አልደበቀም፡፡ የበጎ ፈቃድ አገልግሎቱ ዘላቂ ሆኖ እንዲቀጥል ማጠናከርና መልክ ማስያዝ አስፈላጊ መሆኑንም አስቀምጧል፡፡
የማህበሩ ሰብሳቢ ወጣት ስማቸው ግደይ እንደተናገረው፤ ‹‹ጽዳት ለራስ ነው፡፡ ወጣት ስትሆን ደግሞ ከራስህ አልፈህ ለማህበረሰቡ ማገልገል የሚያስችልህ ቅን ልቦና እና በጎ ፈቃድ ሊኖርህ ይገባል፡፡ ሰው ሜዳ ላይ ሲፀዳዳ ስታይ ያሳዝንሃል፤ በቅርበት የሚያገኘው የተዘጋጀ ቦታ ባለመኖሩ እንጂ ወዶና አላሳቅቅ ብሎት አይመስለኝም፤›› ብሏል፡፡
በሥራችን ምክንያት ከብዙ የውጭ ሰዎች ጋር የመገናኘት አጋጣሚው አለን፤ እነሱ ደግሞ እያንዳንዱን ነገር የሚመለከቱት በአስተውሎት ስለሆነ ሰው ሽንቱን በሜዳው ዳር ሲሸና ይጠይቁናል፡፡ በዚህ ተግባር እናፍራለን፡፡ የምንመልሰው እናጣለን፡፡
በነገራችን ላይ አንተም እኔም የሀገራችን ገፅታን በመገንባት ላይ ልንደራደር አይገባም። እኛ ከሥራችን ጎን ለጎን መረጃ የሚፈልጉ ቱሪስት ታክሲ ተጠቃሚዎች ይጠይቁናል፡፡ በዚህ ጊዜ ስለ አገራችን እና ስለ ወገኖቻችን ያላቸው አመለካከት አዎንታዊ እንዲሆን እንጥራለን፡፡ ይሄን የምናደርገው እንኳን በበጎ ፈቃድ ሳይሆን ኢትዮጵያዊነታችን አስገድዶን ነው፡፡ የሆነ አንዳች ስሜት ይወርሃል እኮ›› በማት ገልጿል፡፡
ወጣት ስማቸው አያይዞ እንዳለው፤ ‹‹ሜዳው የመነኸሪያ አገልግሎት መስጠት ከጀመረ ወዲህ በጣም ይቆሽሻል፡፡ ከሩቅ አገር የመጡ ተሳፋሪዎች መናፈስ ይፈልጋሉ፡፡ የሚያማቸውም በርካታ ናቸው፡፡ ሰው ሲቸገርና ሲጨነቅ ስታይ ትረበሻለህ፤ ሰላም ታጣለህ፡፡ በዚህ የተነሳ እኛ በበጎ ፈቃድ ተሰባስበን እያደረግን ያለነው ደረቅ ቆሻሻን ዘወትር መልቀምና ሜዳውን ማጽዳት ነው፡፡ ከዚህ ባለፈ ሽንት ማስወገጃ ጊዜያዊ ቦታ አዘጋጅተናል፤ ያውም የሚመቸው ለወንድ ነው፤ ስለዚህ ብዙ ሥራ ይቀራል ማለት ነው፡፡ አሁን ላይ መነኸሪያ እየሆነ ከመምጣቱም ጋር ተያይዞ መፀዳጃ ማዘጋጀት አስገዳጅ መሆን አለበት›› ሲል ሐሳቡን አጋርቶናል፡፡
በአገራችን ከጽዳትና ከንጽሕና አጠባበቅ ጋር በተያያዘ የማህበረሰቡን ባህል መቀየር የሚያስችሉ ሰፊ ሥራዎች መሠራት አለባቸው። ለዚህ ደግሞ ወጣቶች በበጎ ፈቃድ፣ በፍላጎታቸው እየተሰማሩ በመሥራት ማሳየት አለባቸው፡፡ በተግባር ማስተማርም እንዲሁ፡፡
ሁሉም ሰው ሀገሩን ከልብ መውደድ አለበት፤ ይህ የሚገልፀው ደግሞ በተግባር ሊሆን ይገባል። ቤቱን፣ ልብሱንና አካባቢውን ተቆጣጥሮ እንደሚያፀዳና ከቆሻሻ እንደሚጠብቅ ሁሉ የሕዝብ አገልግሎት በሚሰጡ ቦታዎች ጭምር ማድረግ አለበት፡፡ ይሄ አልተለመደም፡፡ ስለዚህ ወጣቶች በበጎ ፈቃድ እንደዚህ ሀገራዊ ችግሮች ላይ ዘምተው ካላሳዩ የአፈሙዝ ጦርነትማ አሁን የለም፡፡ በሀገር ደረጃ ጥሪ መተላለፉን በማስታወስ ነው፡፡
በአጠቃላይ ወጣቶቹ ክረምት ከበጋ በሚዘልቀው የበጎ ፈቃድ አገልግሎት ሥራቸው ከማህበረሰቡና ከሚመለከታቸው መንግሥታዊ ተቋማት የሚያገኙት ግብረ መልስ የሞራል አቅም እንደሆናቸው የገለፀው ወጣት ስማቸው ግደይ በጎ ተግባር ዋጋው የመንፈስ እርካታ ነው፡፡ ስለዚህ ለሕብረተሰቡ እስከ ጠቀመ ድረስ የበጎ ተግባር ትንሽ የለውም፡፡ ለሕብረተሰባችን ቅድሚያ ስንደርስና በበጎ ፈቃድ ስናገለግል ለልጆቻችንና ለሀገራችን መሰረት እያስቀመጥን እንደሆነ ልንረዳ ይገባል ሲል ወጣቶችን መክሯል፡፡
አዲስ ዘመን ሐምሌ 25/2011
ሙሐመድ ሁሴን