
በእያንዳንዱ ኢትዮጵያዊ ልቦና የክብር ሥፍራ አለው። የዜግነት ድርሻና እውነተኛ የወገን አለኝታነት ተመስክሮበታል። ዓለምን ባስገረመ መጋመድ የተወለደው ታሪክ ሁሌም በድምቀት ሲወሳ ይኖራል። ለዘመናት ዕምቅ ተፈጥሮን ከማዕድናት ለባዕዳን ሲያስረክብ ለኖረው ዓባይ ወንዝ ደግሞ የቁጭት ታሪክን ቀይሮ የድል ብስራትን አቀጣጥሏል። ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ።
ኢትዮጵያ ‹‹ድህነት›› መጠሪያ ስሟ እስኪመስል በርካታ የችግር ዘመናትን ቆጥራለች። ለዓመታት አይረሴ ረሀብና ድርቅ፣ ጦርነትና ስደት ተመላልሰውባታል። የርዳታ እጆቿን የዘረጋችባቸው ጊዜያት ለልጆቿ የክፉ ዘመን ትውስታዎች ናቸው። ይህ ሁሉ የሆነው ተፈጥሮ ስለነፈገቻት፣ ፈጣሪ ፊት ስላዞረባት አልነበረም።
ሁሌም በዚህች ድንቅ ምድር ክረምት ከበጋ የሚፈሱ ወንዞች ከእጇ ናቸው። ለምለም ምድሯ፣ አረንጓዴ ተላብሶ ዓመታትን ይሻገራል። ያልተነካው ድንግል መሬቷ አንጡራ ሀብት ታቅፎ ዘመናትን ቆጥሯል። ጥቅጥቅ ደኖቿ የበርካታ ብዝኃ ሕይወት መገኛ ናቸው። ንፁሕ አየሯ፣ ዝናብ ፀሐይዋ ለፍጥረታት ሕይወት አይጎረብጡም።
ታላላቅ ወንዞቿ ከራሷ አልፈው ለሌሎች ርካታ ተርፈዋል። ግዙፉ የዓባይ ወንዝ ገባሮቹን ይዞ ከባዕዳን ምድር ሲደርስ ደግሞ ለግብፅና ሱዳን የሀብት በረከት ነው። በውስጡ የሸከፈው ማዕድንና ለም አፈር ለዘመናት የሀብት ሲሳይ ሆኖ ሕይወት አለምልሟል። የሀብት ምንጭ ደርቦ በምቾት አኑሯል።
ይህ እውነት ለአሳሾቹ ምድር ትርጉሙ ይለያል። እስከዛሬ ከቤት ወጥቶ ጎረቤት በሚያድረው ወንዝ ብሶት የወለደው፣ ኅዘን የወረሰው እንጉርጉሮ ከመሆን ያለፈ ታሪክ አተልጻፈም። ዓባይ ዘመናትን በጉዞ ሲባጅ በሚያመላልሰው አንጡራ ሀብት የኢትዮጵያ ሕዝብ ‹‹የበይ ተመልካች›› ሆኖ ኖሯል። ይህ ሐቅም ጊዜው ሲደርስ እንደ ፍም የጋመ፣ እንደብረት የጋለ ቁጭትን ወልዶ ለታላቅ ለውጥ አነሳስቷል።
ታላቁ የዓባይ ወንዝ የዘመናት ጉዞው ይገታ ዘንድ ‹‹ይበቃል›› ያለው የኢትዮጵያ ሕዝብ የአንድነት ክንዱን አጋምዶ ትግል ከጀመረ አስራ አራት ዓመታት ተቆጥረዋል። ታላቁ የህዳሴ ግድብ ግንባታ ዕውን ይሆን ዘንድ ጥሪ ከቀረበበት ጊዜ አንስቶ መላው የኢትዮጵያ ሕዝብ ያለ ልዩነት መጋመዱ ውጤቱን ለፍሬ አድርሶታል።
መጋቢት 24 ቀን 2003 ዓ.ም የህዳሴው ግድብ የመሠረት ድንጋይ ከተጣለበት ቀን አንስቶ ሕዝቡ አቅሙን አልሸሸገም። ስሜቱን አልደበቀም። በዚህ ታሪክ ሕልም ዕውን ይሆን ዘንድ ዕውቀት፣ ጉልበትና ገንዘቡን አዋጥቶ ሀገሩን ዳግመኛ ወለደ። የእናቶች መቀነት ተፈታ፤ የወገን እጅ ተዘረጋ፣ ተማሪውና ወታደሩ፣ ነጋዴውና አርሶአደሩ፣ ምሑሩና ጡረተኛው ስለ ሀገር ሕልውና በእኩል መከረ።
ሀብታም ድሀ ሳይል ቋንቋው እኩል በሆነበት ንቅናቄ ሀገር በልጆቿ ታጀበች። ህዳሴውን ለመገደብ በነበረው ጉዞ የማንንም ይሁንታና እገዛ ሳትሻ መንገዷን መቀጠሏ በሌሎች ፊት በቅንነት አልታየም። ‹‹ጥቅማችን ይነካል፣ ልምዳችን ይጎድላል›› ያሉ ባዕዳን ጦር ሰበቁባት። በዓለም ማኅበረሰብ ዘንድ ተፅዕኖ ለማሳደር የተጋችው ሀገረ ግብፅ የዕንቅልፍ አልባ ጉዟዋ አልተገታም።
በምዕራባውያን ደጋፊዎቿ ፊት ሞገስ ለማግኘት የሮጠችው ሀገር ለጊዜውም ቢሆን የኢትዮጵያን ጉዞ ለመግታት ታገለች። የወቅቱን የአሜሪካ ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕን ጨምሮ ሌሎች አጋሮቿ ሀሳቧን ደግፈው ከጎኗ ቆሙ። ይህ እውነት ግን ለኢትዮጵያ ሕዝብ ተጨማሪ ብርታት ሆኖ ሞራሉን አነሳሳ። በውጭ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያንና ትውልደ-ኢትዮጵያውያን በዲያስፖራ ኅብረት ታቅፈው የህዳሴውን ጉዞ አጣደፉት።
ኢትዮጵያውያን ያለማንም ድጋፍና እገዛ የጀመሩት የህዳሴ ግድብ ‹‹የእኔ ብቻ ይሁን›› ዓላማን አልሰነቀም። የህዳሴው እውንነት ጠቀሜታው ለተፋሰስ ሀገራት ጭምር ነውና ዕድልን በእኩል ያጋራል። ይህን እውነት ለሚመለከታቸው ሀገራት ለማሳየት የተደረገው ዲፕሎማሲያዊ ጥረት ታላቅ ስኬትን አጎናጽፏል። ሁሉም በጊዜ ሂደት የአንድ ገበታ ተቋዳሽነትን ተገንዝበው አጋርነታቸውን አረጋግጠዋል።
ለህዳሴ ግድብ ግንባታ የኢትዮጵያ ሕዝብ በቦንድ ግዢና በበርካታ የገቢ ማስገኛዎች ያኖረው ቋት ታላቅ አቅም ሆኖ ግንባታውን አሳድጓል። አንዳች የባዕዳን የድጋፍ እጆች ያልነካው ግንባታ የተጓዘው በኢትዮጵያውያንና በትውልደ ኢትዮጵያውያን እገዛና ጥረት ብቻ ነው።
ኢትዮጵያ በታላቁ የህዳሴ ጉዞ የብርታት ማንነቷን አሳይታለች። አንድነት ኃይል መሆኑ በተመሰከረበት ታሪክም የኢትዮጵያውያን ድንቅ ዐሻራ በድምቀት ጎልቶ ታትሟል። በገቢ ማሰባሰብ፣ በዲፕሎማሲና ሕዝቡን በማስተባበር ተግባራት ሀገራችን ስሟን በስኬት መዝገብ አስፍራለች።
ይህች ሀገር በሌሎች ዘንድ ‹‹አይቻልም›› የተባለውን ታሪካዊ ትግል በድል አጠናቃ አሸናፊነትን አውጃለች። ይህ እውነታም በሕዝቦቿ የጋራ ቃልኪዳን ተመሥርቶ የታነጸ ነው። ትናንት በድህነት የታለፈው ፈታኝ ዘመን ነገ መጪው ትውልድ እንዳይወርሰው የሁሉም ጠንካራ አበርክቶ ታላቅ ለውጥ መዝግቧል። በዚህ ለውጥ መሐል የሚመጣው አዲስ ታሪክ ደግሞ የኢትዮጵያን ምሰሶ በጽናት ያቆማል።
በህዳሴው ግድብ የግንባታ ጉዞ በርካታ አሉታዊ ጉዳዮች ዕንቅፋት መሆናቸው አልቀረም። በዲፕሎማሲና በዓለም አቀፍ ግንኙነቶች ዙሪያ የነበሩ ትግሎች በርካታ ትግል ጠይቀዋል። የግብፅ መንግሥት ምልከታና እጀ ረጅምነትም ተፅዕኖው የዋዛ አልነበረም። ኢትዮጵያ በተባበሩት መንግሥታት ፊት ክስ ተመስርቶባት ከችሎት ፊት ቆማለች።
እንደ ወንጀል በተቆጠረባት የጥንካሬ ታሪክም የብዙኃን ልጆቿ ቁርጠኝነት በተግባር ተረጋግጧል። ይህ የብርታት ትስስር በጀመረችው ዓላማ ተጉዛ ጅምሯን እንድታጠናቀቅ ምክንያት ሆኗል። በሀገር ልጅ አቅም ተገንብቶ በታላቅነት የገዘፈው የህዳሴ ግድብ ስለነገ ታላቅ ራዕይ ሰንቋል።
ከኢትዮጵያ ባሻገር ለምስራቅ አፍሪካ በሚኖረው በረከትም ዕቅዱን አስቀድሞ አጠናቋል። በኤሌክትሪክ ኃይልና በዓሣ ሀብት ልማት፣ በቱሪስት መስኅብነትና በውጭ ምንዛሪ፣ በሥራ ዕድል ፈጠራና በዕውቀት ቴክኖሎጂ፣ በብዝኃ ሕይወት መገኛነትና የካርቦን ልቀትን በማስወገድ ረገድ ድርሻው ከፍተኛ ነው።
የህዳሴው ግድብ እውን መሆን ለታችኞቹ ተፋሰስ ሀገራት ግብፅና ሱዳን የሚያበረክተው ድርሻ ቀላል አይደለም። የደለል መጠንን በመቀነስ ከጎርፍ አደጋ ይታደጋቸዋል። ዓመቱን ሙሉ የተመጣጠነ የውሃ አቅርቦት እንዲያገኙና ራሳቸውን ከደለል ስጋት ለመከላከል የሚያወጡትን ከፍተኛ ወጪ እንዲቀንሱ ያስችላል።
ከቀጣናው ትሰስር አኳያም ታላቁ የህዳሴ ግድብ የሚኖረው ጠቀሜታ ከፍተኛ ነው። በሚያመነጨው ግዙፍ ኃይል ለጎረቤትና ለሌሎች ሀገራት ሽያጭ በመዋል ሀገራዊ ኢኮኖሚን ለመገንባት ያግዛል። የህዳሴው መኖር የወንዙን የጋራ ተጠቃሚነት መርሕ ዕውን ያደረገ አዲስ ምዕራፍ ይከፍታል። ኢትዮጵያ፣ ግብፅና ሱዳንም በታሪክ አጋጣሚ የዓባይ ውሃን በፍትሐዊነት ለመጠቀም በሚያስችል የትብብር መንገድ በእኩል እንዲጓዙ በር ይከፍታል።
እነሆ! ዛሬ የትናንቱ ክፉ ታሪክ ሊሻር፣ ነባሩ ስማችን ጨርሶ ሊፋቅ ጊዜው ደርሷል። የዘመናት ብሶት ለብሶ በእንጉርጎሮ የሚወቀሰው ዓባይ በታላቁ የህዳሴ ግድብ ስሙን ለውጦ ብሥራት አውጇል። በራስ አቅምና ብርታት፣ በሀገር ሀብትና ወጪ፣ በወገን ላብና ወዝ የተገነባው ታላቁ የህዳሴ ግድብ ዝምታውን አሸንፎ አንደበቱን ከፍቷል።
በዚህ ድምፀት መሐል ታላቅ እውነት አለ። ከማያቋርጠው ፍሰት የተቀዳው ታሪክ የሕዝቦች ስም አርፎበታል። ይህ ድል በፈተናዎች የፈዘዘ፣ በተፅዕኖ የደበዘዘ አይደለም። ታላቁ የህዳሴ ግድብ ብሥራት ዛሬ በወርቃማ ብዕር ደምቆ ተጽፏል። የህዳሴው መሠረት አጥንትና ደም ከኢትዮጵያውያን ማንነት የተሠራ ግማድ ነው። ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ።
ይህ አምድ በተለያዩ ፖለቲካዊ ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ጉዳዮች ዙሪያ ዜጎች ነፃ ሀሳባቸውን የሚሰጡበት ነው። በዓምዱ ላይ የሚወጡ ጽሁፎች የዝግጅት ክፍሉን አቋም አያመለክቱም።
መልካምሥራ አፈወርቅ
አዲስ ዘመን ረቡዕ ሐምሌ 2 ቀን 2017 ዓ.ም