
ወደ ግቢው ስንገባ ሰዓቱ ገና ከጠዋቱ 2፡15 አካባቢ ነው። ይህ ሰዓት ባለጉዳይም ሆነ ሠራተኛ የማይገባበት ሰዓት ነው። ገና ወደ መጀመሪያው ክፍል እንደገባን መገናኛ ወይም ሜክሲኮ ከሚገኝ አንድ የፎቅ በረንዳ ላይ ሆኖ አካባቢውን እንደመቃኘት ይቆጠራል። ይህ የሚሆነው ግን ከአንድ ዘመናዊ ቢሮ ውስጥ በሚታይ ስክሪን ነው። ሁሉም የአዲስ አበባ ወረዳዎች የሥራ እንቅስቃሴ በግድግዳው ስክሪን ላይ ይታያል። ይህን የሚያየው ግን ሥራቸውን እንዲቆጣጠር የተፈቀደለት የሥራ ኃላፊ ነው።
ለጉብኝት የተፈቀደልን ሰዎች ወደ ቀጣዩ ክፍል ገባን። በዕለቱ የተሠሩ ሥራዎችን በሁሉም ክፍለ ከተሞች በዝርዝር ከሚያሳይ ዲጂታል ስክሪን ጋር ተፋጠጥን። በዕለቱ የተደረገ የፍቺ ምዝገባ፣ በዕለቱ የተደረገ የዲጂታል መታወቂያ ምዝገባ፣ በዕለቱ የተደረገ ጠቅላላ የኩነት ምዝገባ የመሳሰሉት በዝርዝር ይታያሉ። ሰዓቱ ገና ከጠዋቱ 2፡30 ስላልሆነ እና መደበኛው የሥራ ሰዓት ስላልተጀመረ 0 የሚል ይበዛዋል። ያም ሆኖ ግን ልደታ ክፍለ ከተማ ገና መደበኛው የሥራ ሰዓት ሳይጀመር 9 የዕለቱ የኩነት ምዝገባዎችን አከናውኗል። ይህ ተቋም በየዕለቱ እና በየሰዓቱ በመላው አዲስ አበባ ውስጥ የተከናወኑ የነዋሪነት አገልግሎቶችን በዲጂታል መረጃ ያውቃል።
ይህ ዘመናዊ የነዋሪዎችን የነዋሪነት አገልግሎት የሚመዘግብ ተቋም የሲቪል ምዝገባ እና የነዋሪነት አገልግሎት ኤጄንሲ ይባላል። ኤጄንሲው ባሕላዊ ከሆነ የወረቀት ክምር ተላቆ ዲጂታል የሆኑ አገልግሎቶችን እየሰጠ ነው። ይህን አሠራር የአዲስ አበባ ከተማ ነዋሪዎች ያውቁት ዘንድ እንዲጎበኙት ይደረጋል። በእዚህ ዕለት በንግዱ ዘርፍ የተሠማሩ የኅብረተሰብ ክፍሎች አሠራሩን ጎብኝተው በሀገራቸው መዘመን እንዲኮሩ አድርጓቸዋል።
አቶ አንለይ መስፍን በንግድ ሥራ የተሠማሩ የአዲስ አበባ ነዋሪ ናቸው። አቶ አንለይ በተለይም ለኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት እንደገለጹት፤ የሲቪል ምዝገባ እና የነዋሪነት አገልግሎት ኤጄንሲን አሠራር ሲጎበኙ ኢትዮጵያ ውስጥ የሚሠራ ዘመናዊ አሠራር አልመሰላቸውም። እርሳቸው የሚያውቁት ረጅም ሰዓት የሚወስድ የወረቀት አሠራር ቀርቶ የዕለቱን ብቻ ሳይሆን በሰዓታት ውስጥ በአዲስ አበባ ውስጥ የሚከናወነውን ሁነት ማወቅ የሚያስችል አሠራር መኖሩ ዘመናዊነት ነው። በሠለጠኑት ሀገራት ብቻ እንደሚደረግ ይሰሙ የነበሩት አቶ አንለይ፤ በዕድሜያቸው እንዲህ ዓይነት ቀልጣፋ እና ዘመናዊ አሠራር በማየታቸው ደስተኛ መሆናቸውን ተናግረዋል።
‹‹የንግዱ ማህበረሰብ የሚከፍለው ግብር ምን አገልግሎት ላይ እንደሚውል የሚያረጋግጥ ነው›› ያሉት አቶ አንለይ፤ በዓይን የሚታዩት ዘመናዊ የከተማ ልማት ሥራዎች እና ዘመናዊ የዲጂታል አገልግሎቶች በመንግሥት እና በሕዝብ መካከል መተማመን የሚፈጥሩ ናቸው ብለዋል።
ሌላኛው የአዲስ አበባ ነዋሪ አቶ መልካሙ ደርጀው በተመሳሳይ በንግድ ሥራ ላይ የተሰማሩ ሲሆኑ፤ ያስተዋሉት የዲጂታል አገልግሎት እና የአዲስ አበባ ከተማ ዘመናዊ መንገዶች ከልብ ከሠሩ ሀገርን ማበልፀግ እንደሚቻል ማሳያ ነው ሲሉ ለኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት አስተያየታቸውን ሰጥተዋል።
እንደ አቶ መልካሙ አስተያየት፤ እንዲህ አይነት ዘመናዊ አሠራር መኖሩን ብዙ የአዲስ አበባም ሆነ የኢትዮጵያ ነዋሪ አያውቅም፤ አሠራሩ በእዚህ ዓይነት ዘመናዊ መንገድ ነው ብሎ የሚያስብ የለም። ተቋሙ አሠራሩን ለብዙዎች ተደራሽ አድርጎ አለማሳየቱን በትዝብት አንስተዋል። የነዋሪዎች የምዝገባ አያያዝ ዘመናዊነት ለሌሎች አሠራሮችም አርዓያ እንዲሆን አሳስበዋል።
እንደ አቶ መልካሙ አስተያየት፤ ከእዚህ በፊት በተደጋጋሚ ይሰማ የነበረው ቅሬታ አዲስ አበባ አለመልማቷን የሚገልጽ ነበር፤ የከተማዋ አለመልማትም ለንግዱ ማህበረሰብ ማነቆ ነበር። አዲስ አበባ በመንገዶቿ እና በአገልግሎቶቿ ዘመናዊ መሆኗ እንግዶችን እንደሚስብና ይህም ለነጋዴው ምቹ መሆኑን ተናግረዋል።
አሠራሮች ቀልጣፋ እና ዘመናዊ መሆናቸው የነጋዴውን ጊዜ የሚቆጥብ፣ የሚጓተቱበትን አሠራሮች የሚያፋጥን ከመሆኑም ባሻገር የአዲስ አበባ ዘመናዊ መሆን እንግዶችን በመሳብ የንግዱን ማህበረሰብ ያጠናክራል ብለዋል።
የሲቪል ምዝገባ እና የነዋሪነት አገልግሎት ኤጄንሲ ዋና ዳይሬክተር አቶ ዮናስ አለማየሁ እንደገለጹት፤ በኤጄንሲው መዋቅር ውስጥ ከዋና መሥሪያ ቤት እስከ ወረዳ ድረስ 362 አይ ሲ ቲ ላይ ስፔሻላይዝድ ያደረጉ ባለሙያዎች አሉ። እነዚህ ባለሙያዎች የሚሰጡ የነዋሪነት አገልግሎቶችን ያረጋግጣሉ።
በሁሉም ክፍለ ከተሞች ውስጥ ካሜራ የተገጠመ መሆኑን የተናገሩት ዋና ዳይሬክተሩ፤ ተገልጋይ ሲጉላላ እና አገልግሎት ሰጪው ባለሙያ በሰዓቱ በሥራ ገበታው ላይ የማይገኝ ከሆነ ርምጃ ይወሰዳል ብለዋል።
ከእዚህ በፊት በነበረው አሠራር አገልግሎቱን የሚሰጡ ባለሙያዎች ‹‹ገብቻለሁ›› ብለው በመዋሸት ተገልጋዩን ያጉላሉ ነበር። በተጀመረው ዘመናዊ የዲጂታል አሠራር ግን ማንም ማንንም ማጭበርበርና መዋሸት አይችልም ብለዋል።
‹‹በኪሳችን የቀበሌ መታወቂያ፣ ፋይዳ መታወቂያ፣ መንጃ ፈቃድ፣ የኤ ኢ ኤም ካርድ የመሳሰሉትን አጭቀን ነው የምንሄደው›› ያሉት አቶ ዮናስ፤ የመታወቂያ አገልግሎት በዘመናዊ መንገድ እየተሠራ መሆኑን ተናግረዋል። የሚዘጋጀው መታወቂያ መንጃ ፈቃድ እና የኤ ቲ ኤም አገልግሎትን ጨምሮ ሁሉንም ዓይነት አገልግሎቶች የያዘ ይሆናል ብለዋል። ይህም ከመጪው ሐምሌ ጀምሮ እንደሚጀመር ገልጸዋል።
የንግዱ ማህበረሰብ የጉለሌ የተቀናጀ የልማት ሥራዎች አካል የሆነውን የጉለሌ እንጀራ ፋብሪካ ጎብኝተዋል። ጉብኚዎቹ በእናቶች የሚዘጋጅ እንጀራ አስተማማኝ እና ንፁህ ከመሆኑም ባሻገር በዘመናዊ መንገድ የሚቦካና የሚጋገር መሆኑ ለሌሎችም ልምድ እንዲካፈልበት አሳስበዋል።
ለምግብነት የሚውሉ የዕፅዋት፣ አትክልትና ፍራፍሬ ዓይነቶች በብዛት የሚገኙበት የእንጀራ ፋብሪካው ግቢ ልምዱን ለሌሎችም እንዲያካፍል ጎብኚዎች አሳስበዋል። የላሞች ማደሪያ ግን ንጽህናው መስተካከል እንዳለበት ለዕለቱ አስጎብኚ አሳስበዋል።
የጉለሌ ክፍለ ከተማ የብልፅግና ፓርቲ አደረጃጀት ዘርፍ ኃላፊ አቶ ሽመልስ ጎዴቦ እንደገለጹት፤ 551 እናቶች በፋብሪካው ውስጥ እንጀራ እየጋገሩ ይገኛሉ። 450 ምጣዶች የተዘጋጁ ሲሆን፤ በሁለት ፈረቃ ይሠራሉ። በእዚህም በቀን እስከ 20 ሺህ እንጀራ ይዘጋጃል። የሚጋገረው እንጀራ በዩኒቨርሲቲዎች፣ በጤና ተቋማት እና በከተማዋ ውስጥ በሚገኙ በተለያዩ የመሸጫ ቦታዎች ይወሰዳል። በቀጣይም አቅሙን ከፍ አድርጎ ለብዙዎች ዕድል እንደሚፈጥር ተናግረዋል።
ዋለልኝ አየለ
አዲስ ዘመን ሰኞ ግንቦት 18 ቀን 2017 ዓ.ም