
የሁለቱ ሀገራትን የንግድ ትስስሮች የበለጠ ማሳደግ ከቅድሚያ የትኩረት ማዕከሎቻችን አንዱ ነው
አዲስ አበባ፡- በኢትዮጵያና በፈረንሳይ መካከል የንግድ ትስስሮቻችንን የበለጠ ማሳደግ ከቅድሚያ የትኩረት ማዕከሎቻችን አንዱ ነው ሲሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) ገለጹ፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) ከፕሬዚዳንት ኢማኑኤል ማክሮን ጋር የሁለቱን ሀገራት ግንኙነት ትብብራችንን በሚያጠናክሩ ጉዳዮች ላይ መወያየታቸውን ገልጸዋል፡፡ ለተደረገላቸው ደማቅ አቀባበልም ምስጋና አቅርበዋል፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትሩ በማኅበራዊ ትስስር ገጻቸው ባሰፈሩት መልዕክት፤ ከፕሬዚዳንት ኢማኑኤል ማክሮን ጋር ግንኙነታችንን እና ትብብራችንን በሚያጠናክሩ ሰፋ ያለ መጠነ ርዕይ ባላቸው ርዕሰ ጉዳዮች ላይ ተወያይተናል፡፡ ትብብራችን በብዙ ጠቃሚ ዘርፎች የቀጠለ ሲሆን፤ የንግድ ትስስሮቻችንን የበለጠ ማሳደግ ከቅድሚያ የትኩረት ማዕከሎቻችን አንዱ ነው ሲሉ ገልጸዋል።
ለተደረገልን ደማቅ አቀባበል እና በታኅሣሥ ወር በአዲስ አበባ ከነበረን ውይይት ቀጥለን ስላካሄድነው ፍሬያማ ውይይት ምስጋናዬን እገልጻለሁ ብለዋል።
የጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ እና የልዑክ ቡድናቸው በፕሬዚዳንት ኢማኑኤል ማክሮን በኤሊሴ ቤተመንግሥት አቀባበል እንደተደረገላቸው አስታውቋል፡፡
በሁለትዮሽ ውይይቱ ፕሬዚዳንት ማክሮን በታኅሣሥ 2017ዓ.ም ኢትዮጵያን ሲጎበኙ የተደረሱ ስምምነቶችን አፈጻጸም አብረው ገምግመዋል ያለው ጽሕፈት ቤቱ፤ ሁለቱ ሀገራት ለረጅም ዘመናት እንደ መከላከያ እና ጸጥታ፣ የባሕል ጥበቃ እና ትምህርት ባሉ ዘርፎች ጠንካራ ትስስር እና ትብብር የፈጠሩ መሆናቸው እንደተጠበቀ ሆኖ በፓሪስ የነበራቸው ውይይት በኢኮኖሚው መስክ የበለጠ ትብብር ለማድረግ እድሎችን የፈተሸ ነው ብሏል።
ፈረንሳይ የኢትዮጵያ እዳ ክለሳ ሂደት ቁልፍ ደጋፊ እንደሆነችም ተመላክቷል፡፡
ከ2010 ዓ.ም ጀምሮ ፈረንሳይ እና ኢትዮጵያ በሁለትዮሽ ግንኙነታቸው መጠናከር ላይ አበክረው መሥራታቸውን የጠቆመው የጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤት ማብራሪያ፤ በከፍተኛ የመሪዎች ጉብኝቶች፣ ስትራቴጂያዊ ስምምነቶች ብሎም በብዙ ዘርፎች በተጀመሩ የጋራ የሥራ ሂደቶች የታየ መሆኑንም ጠቁሟል፡፡
በጥቅምት 2011 ዓ.ም ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ወደ ፈረንሳይ ተጉዘው ለተጠናከረው የመከላከያ እና የባሕል ትብብር ስምምነት መሠረት የጣለ ውይይት አድርገው እንደነበር የታወሰ ሲሆን፤ በመጋቢት 2011 ዓ.ም የፈረንሳዩ ፕሬዚዳንት ኢማኑኤል ማክሮን በኢትዮጵያ የመጀመሪያ ይፋዊ ጉብኝታቸውን በማድረግ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ጋር በርካታ የትብብር ስምምነቶችን ፈርመዋል።
ከስምምነቶቹም የላሊበላ ውቅር አቢያተ ክርስቲያናት እና የብሔራዊ ቤተመንግሥት እድሳት መንገድ የከፈቱ ስምምነቶች ይጠቀሳሉ። በኢትዮጵያ ቆይታቸውም ፕሬዚዳንት ማክሮን ከጥገና ሥራው መጀመር አስቀድሞ ላሊበላን ጎብኝተው ነበር።
በየካቲት 2015 ዓ.ም ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ፈረንሳይን በድጋሚ የጎበኙ ሲሆን፤ የንግድ እና ኢንቨስትመንት ትስስሮች ላይ በማተኮር ውይይቶች ተካሂደዋል። በወቅቱም ኢትዮጵያ ያላትን የተረጋገጠ ዘላቂ የባሕር በር የማግኘት ፍላጎት ብሎም የቀጣና ሰላም አስፈላጊነት ላይ ውይይት ተካሂዷል።
በታኅሣሥ ወር 2017 ዓ.ም ፕሬዚዳንት ማክሮን ወደ ኢትዮጵያ በድጋሚ መጥተው ፈረንሳይ የኢትዮጵያን የኢኮኖሚ ሪፎርም እና የእዳ ክለሳ በተመለከተ ያላትን ድጋፍ በድጋሚ አረጋግጠው፤ በጉብኝቱ ፕሬዚዳንት ማክሮን የኢትዮጵያን የእዳ ክለሳ ሥራ በምሉእ መልክ ደግፈው የኢኮኖሚ መረጋጋት እና እድገት ለማምጣት ፈጣን መፍትሔ የመስጠትን አስፈላጊነት አፅንኦት ሰጥተው ነበር።
ባለፉት ሰባት ዓመታት በኢትዮጵያ እና በፈረንሳይ ያለው ግንኙነት የተለያዩ ዘርፎችን ያካተተ ጠንካራ ግንኙነት ተሸጋግሯል። ይህም በሁለቱ መሪዎች የነቃ ተሳትፎ የተጠናከረ መሆኑን ከጽሕፈት ቤቱ የተገኘው መረጃ ያመለክታል።
ኢትዮጵያና ፈረንሳይ ረጅም ዘመን ያስቆጠረ ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት ያላቸው ሀገራት ሲሆኑ፤ ግንኙነታቸው ከ17ኛው መቶ ክፍለ ዘመን በፊት እንደተጀመረ የታሪክ መዛግብት ያሳያሉ። የሀገራቱ ግንኙነት እየተጠናከረ ሲመጣ የወዳጅነትና የንግድ ስምምነት ወደ ማድረግ እንደተሸጋገሩና በተለይ ኢትዮጵያ የዓድዋ ድልን ከተቀዳጀች በኋላ እኤአ በየካቲት ወር 1897 ዓ.ም የኢትዮ-ጂቡቲ የድንበር ስምምነት በመፈራረም የዲፕሎማሲያዊ ትብብራቸውን መሠረት ጥለዋል።
እኤአ በ1904 ዓ.ም የኢትዮጵያና የፈረንሳይ የወዳጅነት ቢሮ በአዲስ አበባና በድሬዳዋ መከፈቱ ለግንኙነታቸው መጠናከር የበኩሉን ሚና ተጫውቷል። ግንኙነታቸው የበለጠ ተጠናክሮ እኤአ በ1907 ፈረንሳይ ከኢትዮጵያ ጋር ያላትን ግንኙነት የበለጠ ለማሳደግ ኤምባሲዋን በኢትዮጵያ ከፍታለች።
እ.ኤ.አ በ1943 የኢትዮጵያና የፈረንሳይ የባሕል ትብብር ማዕከል፣ በ1947 ሊሴ ገብረማርያም ትምህርት ቤትን፣ በ1955 የፈረንሳይ አርኪኦሎጂ ሚሽንን ወደ የፈረንሳይ ኢትዮጵያ የጥናት ማዕከል እንዲያድግ ማድረግና የሁለትዮሽ ግንኙነቱ በሁሉም መስክ እንዲጠናከር መደረጉን መረጃዎች ያሳያሉ፡፡
ፋንታነሽ ክንዴ
አዲስ ዘመን ቅዳሜ ግንቦት 16 ቀን 2017 ዓ.ም