
የከተማ አስተዳደሩ የቀጣይ ዓመታት ትልቁ ትኩረት የመኖሪያ ቤቶች ግንባታ መሆኑ ተገለጸ
አዲስ አበባ፦ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የቀጣይ ዓመታት ትልቁ ትኩረት የመኖሪያ ቤቶች ግንባታ መሆኑን ከንቲባ አዳነች አቤቤ አስታወቁ ። ዘመናዊ የመኖሪያ መንደሮች ተገንብተው ለነዋሪዎች የሚተላለፉት ዘመናዊ አኗኗር እና ጤናማ ኑሮ ለማረጋገጥ መሆኑን አመለከቱ።
ከንቲባ አዳነች አቤቤ ትናንት በአዲስ ከተማ ክፍለ ከተማ በዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ ላይ ለሚገኙ ዜጎች በዘመናዊ መንገድ የተገነቡ የመኖሪያ ቤቶችን ባስረከቡበት ወቅት እንዳስታወቁት ፤ ከለውጡ ወዲህ በባለሀብቶችና በከተማ አስተዳደሩ በጀት እንዲሁም የግል አልሚዎችን በማሳተፍ ወደ 270 ሺህ ቤቶችን ለነዋሪዎች ማስተላለፍ ተችሏል።
ከዚህ ውስጥ 39 ሺህ ያህሉ የወዳደቁና የፈራረሱ ቤቶችን በማፍረስ የተገነቡ መሆኑን የገለጹት ከንቲባ አዳነች፤ ይህንንም ቀስ በቀስ ወደሌሎች የመዲናዋ የመኖሪያ አካባቢዎች የማስፋፋት ሥራ ይሠራል ብለዋል።
በእለቱ 54 ክፍሎች ያሉት ባለ 5 ወለል ህንፃ ለነዋሪዎቻችን መተላለፉን ፤ ግንባታው የተካሄደበት አካባቢም ድሮ ከነበረው በእጅጉ አምሮ፤ ሰፋፊ እና ምቹ መንገዶች ተካተውበት ፤ የህፃናት መጫወቻ እና የህፃናት ማቆያ ያሉት ፤ ህፃናት እንደፈለጉ የሚቦርቁበት ሆኖ መገንባቱን አስታውቀዋል።
አስተዳደሩ በሚቀጥሉት ዓመታት ትልቁ ትኩረት የሚሆነው የመኖሪያ ቤቶች ግንባታ መሆኑን አመልክተው ፤ በአሁኑ ወቅት በመዲናዋ በመቶ ሺዎች የሚቆጠር የቤቶች ግንባታ እየተካሄደ እንደሆነ ገልፀዋል። ካለው የቤት ፍላጎት አንፃር ግንባታው በቂ እንዳልሆነ፤ ከዛም በላይ መሥራት እንደሚያስፈልግ አመልክተዋል።
“ለዚህም የከተማችን ባለሀብቶችና ነዋሪዎች እንደየአቅማችሁ ተባበሩን እንተባበር አብረን እንሥራ፤ የተለወጡ ሀገራት የተለወጡት ፤ በርትተውና ተባብረው ስለሠሩ ነው” ያሉት ከንቲባዋ፤ ”ማደግ ከሕዝብ ጋር ነው፤ ተባብረን ብዙ ክፍተቶችን እንዝጋ፤ የዘመሙ ጎጆዎችን እናቃና ”ሲሉ ጥሪ አቅርበዋል ።
የዘመመ ጎጆ መጠገን ፤ የተሠራውንም ሥራ ማየት የማይችሉ ሰዎች መንግሥት የሚያከናውናቸውን ሰው ተኮር ሥራዎች በእውነተኛ አይን መመልከት እንደሚገባቸው አመልክተዋል። በአዲስ አበባ ያሉ ታሪካዊ ሥፍራዎችን በመጠበቅ ለትውልድ የማስተላለፍ ሥራ እየተሠራ እንደሆነ አስታውቀዋል።
በእለቱ ቤት ከተረከቡ የከተማዋ ነዋሪ መካከል አንዷ የሆኑት ወይዘሮ ጽጌ አያኖ ፤ ሲቃ በተሞላ ስሜት ፤ የቀድሞ መኖሪያ ቤታቸው በክረምት ወራት ጎርፍ የሚያስገባ ፤ የገባውን ውሃ በሰሃን ከሰፈር ሰዎች ጋር ተባብረው ወደ ውጭ ያስወጡ እንደነበር አስታውሰዋል ።
ይህንንም ለሰላሳ ዓመታት ሲያከናውኑ ለሳንባ በሽታ መዳረጋቸውን ፤ አሁን የተሰጣቸው ቤት የራሱ የሆነ መጸዳጃ ቤትና መኝታ ቤት ያለው መሆኑን አስታውቀዋል። ከእንግዲህ ክረምት መግባቱን ተከትሎ ያጋጥማቸው ከነበረው የጎርፍ አደጋ ስጋት ነጻ መውጣታቸውን ገልጸዋል “እኔን ከዛ መከራና ስቃይ የገላገለኝ ፈጣሪ ሌሎች ደሃ የከተማ ነዋሪዎችን በተመሳሳይ መንገድ ይገላግላቸው” ብለዋል።
በእለቱ የተጨማሪ ቤት ግንባታ የሚሆን አዲስ መሠረተ ድንጋይ ተጥሏል።
በሳሙኤል ወንደሰን
አዲስ ዘመን ሰኞ ግንቦት 11 ቀን 2017 ዓ.ም