
በሀገር ቤት የተሠሩ ትራክተሮች፣ ተሽከርካሪዎች፣ ዘመናዊ የተለያዩ የግብርና ማሽኖች፣ የግንባታ መሣሪያዎች እዚህም እዚያም ይታያሉ። ባለፈው ወር መጨረሻ ለሶስተኛ ጊዜ ለአምስት ቀናት በተካሄደው ኢትዮጵያ ታምርት ኤክስፖ ከ288 በላይ ኢንዱስትሪዎች፤ ከ120 ሺህ በላይ ጎብኚዎች ተሳትፈውበታል። በዚህ ኤክስፖም ከአራት ቢሊዮን ብር በላይ ግብይት ተከናውኖ እንደነበር የኢንዱስትሪ ሚኒስቴር መረጃ ያሳያል፡፡
ኤክስፖው ራሳቸውን ለማስተዋወቅ፤ የገበያ ትስስር ለመፍጠርና ተሞክሮ ለመለዋወጥ ማስቻሉን አምራቾች ነግረውናል፤ በሌላ በኩል ደግሞ ስለ ሀገራቸው አምራች ኢንዱስትሪ ዘርፍ አቅም እንዲገነዘቡ፤ ብሎም የነበራቸውን አስተሳሰብ የቀየረ ኤክስፖ መሆኑን የተለያዩ ጎብኚዎች ይገልጻሉ፡፡
የአሚዮ ኢንጂነሪንግ ኢንዱስትሪ ባለቤት አቶ ሙዘሚል ሞሀመድ እንደሚናገሩት፤ የኢትዮጵያ ታምርት ኤክስፖ በየዓመቱ እንዲዘጋጅ ያቀረበው ሰው እጅግ በጣም የሚደነቅ ነው። ብዙዎቹ ፋብሪካዎች ከዚህ በፊት እንደማይተዋወቁ የሚገልጹት አቶ ሙዘሚል፤ “ኤክስፖ ላይ ከጎኔ ምርቶቹን እያሳየ ያለው አምራች እንደው ለመሆኑ ሞልድ ትሠራላችሁ ሲል ተገርሞ ጠየቀኝ። ሌላው ደግሞ አንድ ባለፋብሪካ መጥቶ ከቻይና አምጥቶ የጣለው በርካታ ሞልድ እንዳለው ገልጾ፤ መጠገን የምንችል ከሆነ ጠይቆን እንዲያመጣ ነገርነው፡፡” ሲሉ ገጠመኛቸውን ያነሳሉ፡፡
ኤክስፖው በጣም እንድንተዋወቅ አድርጎናል። በዚህም አጋጣሚ ወደ ኢንዱስትሪው መጥተው ሞልድ ለማሠራት በርካታ ሰዎች ቃል የገቡ ሲሆን፤ ይህም ከሁለት ሚሊዮን ብር በላይ የሚገመት ገንዘብ ነው። ከዚህ ጋር ተያይዞ ኤክስፖው ትልቅ የሥራ እድል እንደፈጠረላቸው ይገልጻሉ።
የሚቻል ቢሆን ኤክስፖው በየስድስት ወር ቢካሄድ የበለጠ መልካም እንደሚሆን ጠቅሰው፤ አጠቃላይ ካለው ነገር አንጻር የሚቻል አለመሆኑንና ነገር ግን በየዓመቱ የሚዘጋጀው መቅረት እንደሌለበት ምክራቸውን ሰጥተዋል።
ከምርት ሂደት ጋር ተያይዞ የሚያጋጥሙ ችግሮች ምንድን ናቸው? የሚለውን ወደ ፋብሪካዎች በመሄድ መጠየቅ እና ማየት ቢቻል እንዲሁም የኢንዱስትሪዎች የገበያ ትስስር እንዲፈጠር የሚያስችሉ ሥራዎች በቀጣይ ቢሠሩ መልካም ነው ይላሉ፡፡
ከኩሪፍቱ የወረቀት ፋብሪካ የመጡት አቶ ሲሳይ ጌታቸው በበኩላቸው፤ ፋብሪካውን ከሚያጋጥሙ ተግዳሮቶች አንዱ የገበያ ትስስር አለመፈጠሩ እንደሆነ ጠቅሰው፤ እንደ ኢትዮጵያ ታምርት አይነት ኤክስፖዎች እነዚህን ችግሮች እየፈቱ ይገኛል ሲሉ ይገልጻሉ፡፡
እንደዚህ አይነት ኤክስፖዎች መዘጋጀታቸው በመጀመሪያው ከገበያተኛው ጋር፤ ማለትም ምርት ፈላጊ እና አቅራቢው እንዲገናኝ እና ትስስር እንዲፈጠር ያደርጋል። እንዲሁም ራሳችንን እንድናስተዋውቅ እድል የሚፈጥር ኤክስፖ ነው ሲሉ ይጠቅሳሉ፡፡
የመንግሥት አካላት ለጉብኝት በብዛት እንደሚመጡ የሚናገሩት አቶ ሲሳይ፤ በዚህም ቀጥታ የመገናኘት እድል ስለሚኖር በምርት ሂደት ፋብሪካዎች ያለባቸውን ተግዳሮት ለመግለጽና መፍትሄ ለማግኘት ይረዳል።እንዲሁም በአምራቹ ዘንድ ያለውን ሃሳብ ጠይቀው እንዲረዱ ያስችላል ሲሉም ያስረዳሉ፡፡
ኤክስፖውን መጥተው ሲጎበኙ ሶስተኛ ጊዜያቸው እንደሆነ የሚናገሩት፤ አቶ ጌቱ በቀለ በበኩላቸው፤ ከዓመት ዓመት የላቀ ውጤት እየታየ እና ኢንዱስትሪዎችም አዳዲስ ምርቶችን እያቀረቡ እንደሆነ መታዘባቸውን ይናገራሉ፡፡
ጎብኚው እንደሚሉት ከዚህ በፊት የውሃ ቧንቧ ቆጣሪ ከውጭ ሀገር ነው የሚገባው የሚል እሳቤ የነበራቸው ሲሆን፤ ኤክስፖው ላይ የውሃ ቆጣሪ ኢትዮጵያ ውስጥ ማምረት ከጀመረ ሰባት ዓመታትን ያስቆጠረ ድርጅት ለማስተዋል ችለዋል፡፡
የሀገር ውስጥ ምርት የመጠቀም ባህል በስፋት አለማደጉን በመግለጽ፤ ለአብነትም የውሃ ቆጣሪ የሚያቀርበው ድርጅት የሀገር ውስጥ ገበያ ችግር እንዳለበት እና በተቃራኒው ተጠቃሚዎች ከቱርክ ያስገባሉ ሲሉ መልዕክታቸውን አንጻባርቀዋል፡፡
የመንግሥት የልማት ድርጅቶች ገበያ ውስጥ ዘልቀው ለመግባት ራሳቸውን በስፋት የማስተዋወቅ ችግር እንዳለባቸው በመግለጽ፤ ለምሳሌ ኢትዮ- ኢንጂነሪግ በጣም የሚገራርሙ የተሸከርካሪ ፍሬን ሸራዎች ያመርታል፤ ማምረት ብቻ ሳይሆን ሞልዶች ይሠራል፤ ከውጭ የሚገቡትን ተኪ ምርቶች ያመርታል ሲሉ ይጠቁማሉ፡፡
አምርቶ ከውጭ በተሻለ ዋጋ ምርቶችን ቢያቀርብም ገዢ የለውም። ማህበረሰቡ የውጭ ምርት ነው ሲባል ጓጉቶ በከፍተኛ ገንዘብ ይገዛል፤ የሀገር ውስጥ ነው ሲባል ደግሞ ያጣጥላል። ስለዚህ ኢንዱስትሪ ሚንስቴር ኤክስፖ ከማዘጋጀት ጎን ለጎን ሕዝቡ ለሀገር ውስጥ ምርት ያለው አመለካከት እንዲስተካከል የሚያስችሉ ሥራዎችን ቢሠራ መልካም ነው ይላሉ፡፡
በተጨማሪም ኤክስፖውን ከትላልቅ ሰዎች ይልቅ፤ ተማሪዎች በተለይም የፈጠራ ሥራ ላይ የሚያተኩሩ መጥተው እንዲጎበኙ ማድረግ ተገቢ መሆኑን በመጠቆም፤ ኢንዱስትሪ ሚንስቴር እየሠራ ላለው ሥራ ምስጋናቸውን አቅርበዋል፡፡
ወይዘሮ ስንቅነሽ ተክሉ ኤክስፖውን የጎበኙት ለመጀመሪያ ጊዜ ነው።በኤክስፖው ተዟዙረው የተመለከቱት ነገር እጅግ በጣም አስደሳች እንደሆነ እና ከዚህ በፊት አይተው የማያውቋቸውን ምርቶች ብዙ ነገሮች ለመመልከት እንደቻሉ እንዲሁም፤ መደነቃቸውን ይገልጻሉ፡፡
“አንዳንድ ያየኋቸው ምርቶች ከዚህ በፊት ኢትዮጵያ ውስጥ የሚመረቱ እንኳን አይመስለኝም ነበር።ካየሁት ነገር አንጻር ለወደፊት እንደሀገር ያለን ተስፋ ትልቅ መሆኑን እና አሁንም ጥሩ ደረጃ ላይ እንደምንገኝ ተገንዝቢያለው፡፡” ይላሉ፡፡
በቀጣይ የኢንዱስትሪው ዘርፍ እንዲያድግ ሁሉም ባለበት የሙያ ዘርፍ ድጋፍ ቢያደርግ ምልካም ነው የሚሉት ወይዘሮ ስንቅነሽ፤ ኤክስፖው ለወደፊት የበለጠ ተጠናክሮ የማየት ምኞት እንዳላቸው ይገልጻሉ፡፡
ዓመለወርቅ ከበደ
አዲስ ዘመን ቅዳሜ ግንቦት 9 ቀን 2017 ዓ.ም