እኔ በሰውነቴ ከማንም አልበልጥም፣ አላንስም! እርስዎስ?

በብዙዎቻችን ሰዎች ዘንድ ስለ አፈጣጠራችን ያለው የጋራ አቋም፤ ሰውን በፈጠረው አምላክ ፊት ሁላችንም እኩል እንደሆንን ማመናችን ነው። የሰው ልጆችን ከሌላው ፍጥረት የተለየን ከሚያደርጉን ጉዳዮች መካከል ፤ የግንዛቤ ባህሪያት እና የአካል ጥምረት ውጤት መሆናችን ነው። ይህም ማለት ባለ ትልቅ አእምሮ፣ ውስብስብ ቋንቋ መናገራችን ፣ የመማር እና የመረዳት ችሎታችን፣ ረቂቅ አስተሳሰብ እና ችግ ፈቺ የሆነ ማንነት ያለን በመሆናችን ነው ።

ስለ ሰው ልጅ እኩልነት በተለይ በዚህ በሠለጠነው ዘመን ሰፋ እና ጠለቅ ብሎ ሲገመገም የምንገነዘበው ዋናው ነገር፤ ሁላችንም በተፈጥሮ የየራሳችን ልዩነቶች ያለን (ማለትም በጾታ፣ ቀለም፣ ቁመት፣ ባህል፣ በባህሪያት፣ ልምዶች እና አመለካከቶች ወዘተ) ቢሆንም፤ በሰውነት ክብር እና በሞራል ዋጋ ግን ፍፁም እኩል ነን የሚለው እሳቤ ነው። ይህም መርህ ሁልጊዜ ግለሰቦች ተመሳሳይ መሠረታዊ መብቶችን የማግኘት እንዳለባቸው እና በአክብሮት እና ያለ አድልዎ ሊታዩ እንደሚገባ ያሳያል።

ፈጣሪ፤ አንዱን ሰው ከሌላው በላይ ወይም በታች አድርጎ አይፈጥርም!

ነገር ግን ይህ እውነት እንዳለ ሆኖ በሰው ልጆች ታሪክ፤ በቆዳ ቀለም ፣ በዘር፣ በቋንቋ እና በመሳሰሉት ልዩነቶች አንዱ ከአንዱ የተለየ ስሜት ሲሰማውና ሲያስተናግድ እንደነበር ታሪካዊ ክስተቶች አሳይተውን አልፈዋል፤ ቢሆንም ግን በየትኛውም አጋጣሚ ይህ እውነት እንደሆነ አረጋጠውልን አያውቁም። በየትኛውም ሚዛን አንዱ ሰው ከአንዱ በመሠረታዊ አፈጣጠሩ የሚበልጥበት ወይንም የሚያንስበት ሁኔታ የለም።

በሰው ልጆች መሃከል የዖታ፣ የቀለም፣ የቋንቋ ብዝሃነት አለ፤ የነበርም ፣ ወደፊትም የሚኖር ነገር ነው፤ ይህ ልዩነት በተፈጥሮ በሁሉም ብዝሐ ሕይወት ዘንድ አለ። ልዩነት ሰውን በፈጠረው አምላክ የተቸረ እንጂ እርግማን ወይም አሉታዊ ነገር አይደለም። የጥንካሬ ምንጭ እና ለአዎንታዊ ለውጦች ምክንያት የሚሆን ነው።

በሰዎች መሃከል በዚች ምድር ላይ በሕይወት ስንኖር ስለ ለተፈጥሮ እና ውበት፣ ስለ ፈጠራ እንዲሁም ለችግሮቻችን መፍትሄን መፈለግ ላይ የተለያየ ምልከታ እና ችሎታ ተጎናፅፈን ነው የተፈጠርነው። ብዝሃነት በበጎ ጎኑ ማሰብ ትሩፋቶቹን ለመጠቀም ያስችለናል። ብዝሃነትታችን በባህልና በወጎች፣ በክህሎቶች እና በእውቀት መሠረቶች የዳበረ ጠንካራ ማህበረሰብ ይፈጥርልናል፣ የመተሳሰብ እና የመቻቻል ልምድ ያጎናፅፈናል፣ የግንኙነት ችሎታዎች ለማዳበር ፣ ባህል ለማጎልበት እና ለማበልጸግ ይረዳናል፣ የማህበረሰባችንን ችግር የመፍታት አቅም ይፈጥርልናል፣ አዳዲስ ግንዛቤዎችን እና የአስተሳሰብ መንገዶችን ያላምደናል፤ በዚህም ጠንካራ ማህበረሰብ ይፈጥራል።

“ብዝሃነት እርግማን” የሚሆነው፣ ከብዝሃነት መልካም ተፈጥሯዊ ባህሪ ይልቅ በልዩ፣ ጤናማ ባልሆነና ጥቅምን መሠረት ባደረገ ማህበራዊ እና ፖለቲካዊ መነፅር ስንመለከተው ብቻ ነው።

የቆዳ ቀለም ፣ ዘር፣ ቋንቋ እና መሰል ነገሮች በአንድ ማህበረሰብ እና ሀገር፤ ተጽእኖ ፈጥረው ፣ አቅምን አግኝተው፤ በሰዎች ዘንድ ለጥላቻ፣ ቂም እና በቀል ከዚያም ሲያልፍ ለግጭትና ጥፋት ምክንያት እንዲሆኑ እድል መስጠት አይገባም!

እኔ በሰውነቴ ከየትኛውም ዘር፤ ከአማራ፣ ኦሮሞ፣ ትግሬ፣ ጉራጌ፣ ዶርዜ፤ ከይሁዲውም፣ ከግሪካዊውም፣ አሜሪካዊ፣ ቻይናዊው፣ ሞንጎሊያዊው፣ ወዘተ በየትኛውም የምድር ክፍል ከተፈጠረው ሰው አልበልጥም! አላንስምም! ሁሉንም በእኩል ዓይን ማየት ፍጥረታዊ ግዴታዬ ነው፤ በሌላውም ዘንድ በእኩልነት መታየት እፈልጋልሁ። እናንተስ?

ሰውን በእኩልነት ማየት መልካም ማህበራዊ ትስስር ያመጣል፣ የመተማመንን እና የትብብርን መንፈስ በመሃላችን ይጨምራል፣ የእኔነት እና የአብሮነት ስሜትን ያዳብራል ፤ በጋራ ወደ ጤናማ ፣ወደ ተባበረ እና የተቀናጀ የማህበረሰብ ደረጃ ላይ ያመጣናል፤ አላስፈላጊ አካባቢያዊ ውድመቶችን ያጠፋል፤ ግለሰባዊ ደህንነት እንዲሰማን ያደርጋል፣ ደስታችንን ይጨምራል፣ ጭንቀታችንን ስጋቶችን ይቀንሳል፣ ጠንካራ የሆነ ሁላችንንም የሚያጋራ ዓላማ እንዲፈጠር ምክንያት ይሆናል።

በተቃራኒው ሰውን በእኩልነት አለማየት ደካማ ማህበራዊ ትስስር እንዲኖር፣ በህብረተሰብ መሃል መከፋፈል እንዲፈጠር፤ አለመተማመን እና ፍትሃዊነት እንዳይኖረን ከማድረጉም በላይ አላስፈላጊ ወደ ሆነው ማህበረሰባዊ መራራቅ ያመራል። የልግስና እና የርህራሄ መንፈስ እየቀነሰ እንዲሄድ ያደርጋል፣ ስሜታዊነትን እና ጭፍን ጥላቻዎች ይወልዳል፣ አለፍ ሲልም ግጭት እና ውድመት ሊያደርስ ይችላል። ይህንንም በተለያዩ ዘመናት፥ በተለያዩ ሀገሮች ተከስቶ የሰዎችን ሕይወት ቀጥፎ፣ ንብረት አውድሞና ትልቅ ጠባሳ ትቶ እንዳለፈ ታሪክ ያስረዳናል።

በአንድ ሀገር በጋራ ሆኖ ፤ በትብብር እና በመረዳዳት ለመኖር፣ የጋራ ዓላማን ይዞ ለመጓዝ፣ ለማደግ፣ ዘለቄታዊ እና ዘመን ተሻጋሪ፣ ስም የሚያስጠሩ ታሪካዊ ሥራዎችን በጋራ ለማቆም እንደ አንድ ማህበረሰብ መከባበርን፣ መዋድድን፣ መቻቻልን ምርጫችን ማድረግ ብልህነት ነው።

በዚህ ጉዳይ “እኔ በሰውነቴ ከማንም አልበልጥም፣ አላንስም! እርስዎስ?” በሚለው አጽንዖት ያለበት ጥያቄ ውስጥ ለማስተላለፍ የፈልኩት ሃሳብ፤ “እኔ” (ማለትም ተናጋሪው ግለሰብ) በዚህ እሳቤ፤ ማንንም ሰው፤ በሰውነቴ የማልበልጥ እንደሆነና፤ ደግሞም ከማንም እንደማላንስ በመረዳት ነው።

ሰው የሆነ ሁሉ አንድ ጊዜ ቆም ብሎ፤ ለሌላው ሰው ያለውን ግምት እና ዋጋ እንዲያስብ ፤ ሌላውንም በዚህ ሚዛን እንዲመለከት እና ጤናማ ምልከታ በዙሪያው ባለው ማህበረሰብ ውስጥ እንዲፈጥር እጋብዛለሁ። ይህ የእኔ፣ የአንድ ሰው ሃሳብ ነው፤ እኔ ከአንተ /ካንቺ/ ከእርስዎ በፍጥረቴ አልበልጥም፤ አላንስምም!

እርስዎስ ምን ያስባሉ?

በቴዎድሮስ እንግዳ

አዲስ ዘመን ዓርብ ግንቦት 8 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You