ሶሪያን በተስፋና በስጋት መካከል ያቆመው የትራምፕ ውሳኔ

የአሜሪካው ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ ሀገራቸው ቀደም ሲል በሶሪያ ላይ ጥላቸው የነበሩ ማዕቀቦችን እንደምታነሳ አስታውቀዋል፡፡ በመካከለኛው ምስራቅ ጉብኝት እያደረጉ ያሉት ፕሬዚዳንት ትራምፕ፣ በሳዑዲ አረቢያ ዋና ከተማ ሪያድ በተካሄደው የሳዑዲ-አሜሪካ ኢንቨስትመንት ጉባዔ ላይ ባደረጉት ንግግር፣ አሜሪካ በሶሪያ ላይ ጥላቸው የነበሩ ማዕቀቦችን እንደምታነሳ ይፋ አድርገዋል፡፡

ፕሬዚዳንቱ ‹‹ሶሪያ የተሻለችና ታላቅ ሀገር እንድትሆን እድል ለመስጠት ሲባል በሀገሪቱ ላይ የተጣሉት ማዕቀቦች እንዲነሱ ትእዛዝ አስተላልፋለሁ፡፡ ማዕቀቦች ዓላማቸውን አሳክተዋል፤ ከዚህ በኋላ አያስፈልጉም፡፡ አሁን ሶሪያ ወደ ፊት የምትጓዝበት ጊዜ ነው፡፡ ሶሪያን ወደ ሰላምና መረጋጋት እንደሚመልስ ተስፋን የሰነቀ አዲስ መንግሥት አለ›› በማለት ተናግረዋል፡፡ ፕሬዚዳንቱ በንግግራቸው ለሶሪያ መልካም እድል የተመኙ ሲሆን፣ ‹‹ሶሪያ ሆይ፣ አዲስና ልዩ የሆነ ነገር አሳዪን›› ብለዋል፡፡

ከሳዑዲ አረቢያ አልጋ ወራሽ መሀመድ ቢን ሰልማን እና ከቱርክ ፕሬዚዳንት ረሲፕ ጣይብ ኤርዶጋን ጋር ያደረጓቸው ውይይቶች ይህን ውሳኔ እንዲወስኑ እንዳደረጓቸውም ፕሬዚዳንቱ ተናግረዋል፡፡ የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ማርኮ ሩቢዮ በዚህ ሳምንት ከሶሪያው አቻቸው አሳድ አል-ሻይባኒ ጋር ቱርክ ውስጥ ተገናኝተው እንደሚወያዩም የጠቆሙት ፕሬዚዳንት ትራምፕ፣ አሜሪካ ከሶሪያ ጋር ያላትን ግንኙነት ማደስ እንደምትፈልግም አስታውቀዋል፡፡

የሶሪያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አሳድ አል-ሻይባኒ የአሜሪካን ውሳኔ በደስታ እንደሚቀበሉት ተናግረዋል። ‹‹ሶሪያውያን ከዓመታት አውዳሚ ጦርነት በኋላ ወደ መረጋጋት፣ ራስን መቻልና መልሶ ግንባታ እየተጓዝን ባለንበት ወቅት ላይ የተገኘ ወሳኝ ርምጃ ነው›› በማለት ለሶሪያ መንግሥት የዜና ማዕከል (Syrian Arab News Agency – SANA) ተናግረዋል፡፡ በሺዎች የሚቆጠሩ ሶሪያውያንም በብዙ የሀገሪቱ ከተሞች አደባባይ በመውጣት ደስታቸውን ገልፀዋል፡፡

የሶሪያ የሽግግር መንግሥት በጦርነት የወደመችውን ሀገር ለመገንባት የሀገሪቱን ፖለቲካዊና ምጣኔ ሀብታዊ ዲፕሎማሲ ማደስና ማጠንከር ይፈልጋል፡፡ ሀብታሞቹ የባህረ ሰላጤው ሀገራትና ዓለም አቀፍ የፋይናንስ ተቋማት በሀገሪቱ የመልሶ ግንባታ ተግባር ላይ ወሳኝ ሚና እንዲኖራቸው ይፈልጋል፡፡

የአሜሪካ ማዕቀቦች መነሳታቸውም የሶሪያ ምጣኔ ሀብት ከገባበት አዘቅት ወጥቶ እንዲያገግም በማድረግ ረገድ ቀላል የማይባል ድርሻ ይኖረዋል፡፡ የማዕቀቦቹ መነሳት በማዕቀቦቹ ምክንያት በሶሪያ ከርዳታና ከኢንቨስትመንት ታቅበው የቆዩት ሀብታሞቹ የባህረ ሰላጤው ሀገራት ለሶሪያ መልሶ ግንባታ በጎ አስተዋፅኦ በሚኖራቸው የኢንቨስትመንት ተግባራት ላይ እንዲሠማሩ ያስችላቸዋል፡፡ አሜሪካ በዓለም አቀፍ የፋይናንስ ሥርዓት ውስጥ ቁልፍ ሚና ያላት ሀገር በመሆኗ ማዕቀቦቿን ማንሳቷ ዓለም አቀፉ ኅብረተሰብ ከሶሪያ ጋር የንግድና ኢንቨስትመንት ሥራዎችን ለማከናወን ያስችለዋል ተብሏል፡፡

ሶሪያ ለ14 ዓመታት በዘለቀው የእርስ በእርስ ጦርነት አሰቃቂ ውድመትን አስተናግዳለች፡፡ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የልማት ፕሮግራም (UNDP) ይፋ ያደረገው ሪፖርት እንደሚያሳየው፣ ሶሪያ ከጦርነቱ በፊት ወደነበረችበት የምጣኔ ሀብት ሁኔታ ለመመለስ ከ50 ዓመታት በላይ ይፈጅባታል፡፡

የመልሶ ግንባታውን ሥራ ለማፋጠን ብዙ ኢንቨስትመንት ትፈልጋለች፡፡ ከአስር ሶሪያውያን መካከል ዘጠኙ በድህነት ውስጥ ይገኛሉ፡፡ የሀገሪቱ ጥቅል ሀገራዊ ምርት (GDP) ጦርነቱ ሲጀመር ከነበረው ዋጋ በእጥፍ አሽቆልቁሏል፡፡ የሀገሪቱ የሠብዓዊ ልማት አሃዝ እ.አ.አ በ1990 ከተመዘገበው ያነሰ ሆኗል፡፡ ሶሪያ በ14 ዓመቱ ጦርነት ያጣችው ጥቅል ሀገራዊ ምርት 800 ቢሊዮን ዶላር እንደሚሆን ገልጿል፡፡

ፕሬዚዳንቱ ቃላቸውን ጠብቀው ሁሉም ማዕቀቦች ከተነሱ፣ ውሳኔው አሜሪካ ባለፉት 53 ዓመታት በሶሪያ ላይ ስታራምደው የቆየችውን አካሄድ የሚለውጥ ይሆናል፡፡ ከአባትና ልጁ የቀድሞዎቹ የሶሪያ መሪዎች ሃፌዝ አል-አሳድ እና በሺር አል-አሳድ አስተዳደር ጋር ከፍተኛ ቅራኔ ውስጥ ገብታ የቆየችው አሜሪካ፣ በሶሪያ ላይ በርካታ ማዕቀቦችን ጥላ ቆይታለች፡፡ አብዛኞቹ ማዕቀቦች የበሺር አል-አሳድ መንግሥት በሰላማዊ ተቃዋሚዎች ላይ በሚፈፅመው የሠብዓዊ መብት ጥሰቶች ምክንያት የተጣሉ ነበሩ፡፡

የፕሬዚዳንት ትራምፕ ውሳኔ ላለፉት 14 ዓመታት በእርስ በእርስ ጦርነት ለደቀቀችው ሶሪያ መልካም ዜና እንደሆነ ተገልጿል፡፡ ይሁን እንጂ ውሳኔው በጥንቃቄ መታየት እንዳለበት የሚሞግቱ ተንታኞችም አሉ፡፡ የአልጀዚራ የፖለቲካ ተንታኝ ማርዋን ቢሻራ፣ ከትራምፕ ውሳኔ ጀርባ ምን ዓይነት የአሜሪካ ፍላጎት እንዳለ ማወቅ እንደሚያስፈልግ ይገልፃሉ፡፡ ‹‹ማዕቀብ የተነሳላት ደማስቆ በምላሹ ምን ይጠበቅባታል?›› ሲሉ ይጠይቃሉ፡፡

‹‹አሜሪካ ከአዲሱ የሶሪያ የሽግግር መንግሥት ጋር የዲፕሎማሲ ግንኙነት ለመፍጠር ከዚህ ቀደም ቅድመ ሁኔታዎችን አስቀምጣ ነበር፡፡ ከቅድመ ሁኔታዎቹ መካከል አንዱ ሶሪያ ‹የአብርሃም ስምምነት›ን እንድትቀበልና ከእስራኤል ጋር መልካም ግንኙነት እንድትመሰርት የሚጠይቅ ነው፡፡ ይህ ደግሞ የፍልስጤማውያንን ጥያቄና ጥቅም በመደፍጠጥ የሚከናወን ነው›› ይላሉ፡፡

በመካከለኛው ምስራቅ የዓለም አቀፍ ጉዳዮች ካውንስል ባልደረባ ኦማር ራህማን፣ የትራምፕን ርምጃ ከልክ በላይ ማጋነን ተገቢ ባይሆንም፣ ውሳኔው በጦርነት ለተጎዳችው ሶሪያ ጠቃሚ እንደሆነ እውቅና መስጠት እንደሚገባ ያስረዳሉ፡፡ እንደራህማን ገለፃ፣ ውሳኔው ሶሪያ መጠነኛ የምጣኔ ሀብት እድገት እንድታስመዘግብ ሊያግዛት ይችላል፡፡ ይሁን እንጂ ሀገሪቱ የገጠሟት ችግሮች ቁጥራቸውም ዓይነታቸውም ብዙ እንደሆነ ይገልፃሉ፡፡

ከዚህ በተጨማሪም አሜሪካ ፖሊሲዎቿን ለማስፈፀም ማዕቀብን እንደአማራጭ መጠቀሟን አስታውሰው፣ ትራምፕ ይህን ውሳኔ እንዲወስኑ ከሳዑዲ አረቢያ በተጨማሪ የተባበሩት አረብ ኤምሬቶችና ኳታር ግፊት ስለማድረጋቸው ያብራራሉ፡፡ ‹‹በእርግጥ ውሳኔው የኮንግረሱን ጨምሮ የሌላ አካልን ይሁንታ ስለማይፈልግ ይህን ማድረግ ለትራምፕ ከባድና አስቸጋሪ አይደለም›› ይላሉ፡፡

ይህ በእንዲህ እንዳለ ፕሬዚዳንት ትራምፕ ከሶሪያ የሽግግር መንግሥት ፕሬዚዳንት አህመድ አል-ሻራ ጋር በሪያድ ተገናኝተው ተነጋግረዋል፡፡ የአሜሪካና የሶሪያ መሪዎች ሲገናኙ ከ25 ዓመታት በኋላ ይህ የመጀመሪያው ነው፡፡ አሜሪካ አህመድ አል-ሻራን በአሸባሪነት ፈርጃቸው ነበር፤ ያሉበትን ለሚጠቁማትም የ10 ሚሊዮን ዶላር ጉርሻ አዘጋጅታ ነበር፡፡ አል-ሻራ ይመሩት የነበረው ‹‹ሃያት ታህሪር አል-ሻም›› (Hayat Tahrir al-Sham) የተሰኘው ታጣቂ ቡድንም በአሜሪካ ‹‹የውጭ አሸባሪ ድርጅት›› ተብሎ ተፈርጆ ነበር፡፡

ለ33 ደቂቃዎች በቆየው የሁለቱ መሪዎች ውይይት፣ ፕሬዚዳንት ትራምፕ አሜሪካ በሶሪያ ላይ ጥላቸው የነበሩትን ሁሉንም ማዕቀቦች እንደምታነሳና ከሶሪያ ጋር ያላትን ግንኙነት ማደስ እንደምትፈልግም ለአል-ሻራ ነግረዋቸዋል፡፡ የሶሪያ መንግሥት ደግሞ ‹‹የአብርሃም ስምምነት››ን በመቀበል ከእስራኤል ጋር ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት እንዲጀምር፣ አሸባሪ ፍልስጤማውያንን ከሀገሩ እንዲያስወጣ እና በሰሜን ምስራቅ ሶሪያ ለሚገኙ የእስላማዊ መንግሥት (ISIS) ማጎሪያ ማዕከላት ኃላፊነት እንዲወስድ ጠይቀዋል፡፡

የአልጀዚራው ዘጋቢ ኢምራን ካሃን ከደማስቆ ባሰራጨው ዘገባ፣ የትራምፕ ውሳኔ ለአሜሪካና ሶሪያ ግንኙነት አስደናቂ ርምጃ ቢሆንም፣ ‹‹የአብርሃም ስምምነት››ን ተቀብሎ ከእስራኤል ጋር ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት የመጀመር ጉዳይ ለሶሪያ መንግሥት እጅግ በጣም አስቸጋሪ እንደሚሆንበት ገልጿል፡፡

ትራምፕ በሶሪያ ላይ ተጥለው የነበሩ ማዕቀቦችን ለማንሳት ከመወሰናቸው ጋር ተያይዞ የምትነሳው ሌላዋ ባለጉዳይ እስራኤል ናት፡፡

የዋሺንግተኑ ትራምፕ የሁነኛ ወዳጃቸውን የቴል አቪቩን አለቃ ቤንጃሚን ኔታንያሁን ሳያማክሩ የሚወስኗቸው ውሳኔዎች እየበዙ ነው፡፡ ከየመን ሁቲ ታጣቂዎች ጋር የተኩስ ማቆም ስምምነት ላይ መድረሳቸው፣ በመካከለኛው ምስራቅ እያደረጉ ባለው የጉብኝት መርሃ ግብራቸው እስራኤልን አለማካተታቸው እንዲሁም እስራኤል ጥያቄና ቅሬታ ያሰማችበትን የሳዑዲ አረቢያን የሰላማዊ ኑክሌር ግንባታ ጉዳይ ችላ ማለታቸው በሁለቱ ጥብቅ ወዳጅ ሀገራት መሪዎች መካከል ነፋስ ገብቷል ተብሎ እንዲወራ ምክንያት ሆነዋል፡፡

አሁን ደግሞ እስራኤል ያለማንም ከልካይ ቦምብ የምታዘንብባትንና ‹‹አሸባሪ›› ብላ በፈረጀችው ቡድን የምትመራውን ሶሪያን የሚጠቅም ውሳኔ ይፋ ማድረጋቸው በዋሺንግተንና በቴል አቪቭ መካከል የተፈጠረውን ስንጥቅ ሊያሰፋው እንደሚችል እየተገለፀ ነው፡፡ በእርግጥ ፕሬዚዳንት ትራምፕ የሳዑዲ ቆይታቸውን አጠናቀው ወደ ኳታር ሲያቀኑ፣ እስራኤልን እንዳልዘነጉ ተናግረዋል፡፡ ‹‹እኔ ከእነዚህ ሀገራት ጋር እንዲህ ዓይነት ግንኙነት መመስረቴ ለእስራኤል ጥሩና ጠቃሚ ነው›› ብለዋል፡፡

ከሶሪያ የሽግግር መንግሥት ፕሬዚዳንት አህመድ አል-ሻራ ጋር በሪያድ ባደረጉት ውይይት፣ ሀገራቸው በሶሪያ ላይ ጥላቸው የነበሩትን ሁሉንም ማዕቀቦች እንደምታነሳ ከገለፁላቸው በኋላ፣ ሶሪያ ከእስራኤል ጋር ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት እንድትጀምር መጠየቃቸው ከግምት ውስጥ ሊገባ ይገባል፡፡

እስራኤል በሺር አል-አሳድ ለሩብ ክፍለ ዘመን ያህል የቆዩበትን ዙፋናቸውን ጥለው ከተሰደዱ ወዲህ ሶሪያ ውስጥ ተደጋጋሚ የአየር ጥቃቶችን ፈፅማለች፡፡ እስራኤል ለምትፈፅማቸው ጥቃቶች ከምትሰጣቸው ምክንያቶች መካከል አንዱ ሶሪያ ውስጥ በተለያዩ አካባቢዎች የነበረው የጦር መሣሪያ ለደህንነቷ ስጋት ይሆናሉ ባለቻቸው ታጣቂዎች እጅ እንዳይገባ የሚል ነው፡፡

ከሁለት ሳምንታት በፊት ደማስቆ ውስጥ በሶሪያ ፕሬዚዳንታዊ ቤተ መንግሥት አቅራቢያ የፈፀመችው ጥቃት ደግሞ የሶሪያ መንግሥት ኃይሎች በድሩዝ ማኅበረሰብ አባላት ላይ ለፈፀሙት ግድያ ምላሽ እንደሆነ ገልፃለች፡፡ የድሩዝ ማኅበረሰብ አባላት የሺአ እስልምና ተከታዮች ሲሆኑ በሶሪያ፣ በእስራኤልና በሊባኖስ ይኖራሉ፡፡ እስራኤል የማኅበረሰቡን አባላት እንደአጋሯ የምትቆጥራቸው ሲሆን፣ ብዙ ድሩዞች የእስራኤል ጦር አባላት ሆነው በማገልገል ላይ ይገኛሉ፡፡

በሌላ በኩል እስራኤል የበሺር አል-አሳድን መንግሥት የገለበጡትን ኃይሎች ያሰባሰበውን የሶሪያን የሽግግር መንግሥት በበጎ አትመለከተውም፡፡ ቀደም ሲል እስራኤል የአልሻራን መንግሥት ‹‹ከኢድሊብ ተነስቶ ደማስቆን በኃይል የተቆጣጠረው የሽብር ቡድን›› ብላ ሰይማው ነበር፡፡

እስራኤል አንድ ጊዜ ሶሪያ ውስጥ በተለያዩ አካባቢዎች የተከማቸው የጦር መሣሪያ ለደህንነቴ ስጋት በሆኑ ታጣቂዎች እጅ እንዳይገባ፣ ሌላ ጊዜ ደግሞ የሶሪያ መንግሥት አጋሮቼ የሆኑትን የድሩዝ ማኅበረሰብ አባላትን ከጥቃት ሊታደግ አልቻለም በሚሉ ሰበቦች ሶሪያ ውስጥ በተከታታይ የምትፈፅማቸው ጥቃቶች፣ አሜሪካ በሶሪያ ላይ ጥላቸው የነበሩትን ማዕቀቦች ለማንሳት የወሰደችውን ርምጃ እንዳያጠለሹት ጥንቃቄ ማድረግ እንደሚገባ የሚያስረዱ ተንታኞች አሉ፡፡

ማርዋን ቢሻራ እስራኤል በሶሪያ አለመረጋጋት ውስጥ ያላትን ሚና ችላ ማለት እንደማይገባ ይናገራሉ፡፡ ‹‹የሶሪያን ድንበር የደፈረችው፣ በሶሪያ ጉዳይ ጣልቃ የምትገባው እና ሶሪያን ለመከፋፈልና ለማዳከም የምትሞክረው እስራኤል ናት›› በማለት፡፡ አሜሪካ በሶሪያ ላይ ጥላቸው የነበሩትን ማዕቀቦችን ከማንሳቷ በተጨማሪ እስራኤልን ጣልቃ ገብነቷን እንድታቆም ጫና ማድረግ እንዳለባት ያሳስባሉ፡፡ የማዕቀቦቹ መነሳት ብቻ ትልቅ ለውጥ ሊፈጥር እንደማይችልም ይገልፃሉ፡፡

ፕሬዚዳንት ትራምፕ አሜሪካ በሶሪያ ላይ ጥላቸው የነበሩትን ማዕቀቦች እንደምታነሳ ይፋ ያደረጉት እቅድ ለሶሪያ ደስታን ብቻ ይዞ አልመጣም፡፡ ፕሬዚዳንቱ እቅዳቸው ገቢራዊ እንዲሆን ለሶሪያ ያቀረቧቸው ቅድመ ሁኔታዎች፣ በተለይም ‹‹የአብርሃም ስምምነት››ን ተቀብሎ ከእስራኤል ጋር ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት የመጀመር ጉዳይ፣ ለሶሪያ መንግሥት ‹‹ላም እሳት ወለደች፤ እንዳትልሰው ፈጃት፣ እንዳትተወውም ልጅ ሆነባት›› ዓይነት ኢትዮጵያዊ ብሂል እንደሚሆንበት አያጠራጥርም፡፡

አንተነህ ቸሬ

አዲስ ዘመን ዓርብ ግንቦት 8 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You