ኢንቨስትመንትን ለማነቃቃት የሚከናወኑ ተግባራት ተጠናክረው ይቀጥሉ!

ኢትዮጵያ ለኢንቨስትመንት ምቹ የሆነች ሀገር ነች። ያላት ሰፊ መሬት፤ ከፍተኛ የውሃ ሀብት፣ ወጣትና
የተማረ የሰው ኃይል ብሎም ያላት የተሟላ መሠረተ ልማት ለኢንቨስትመንት ምቹ ያደርጋታል።
ብዙዎች እንደሚያረጋግጡት የኢትዮጵያ አፈር እና ተስማሚ የአየር ጸባይ የሰጡትን የሚያበቅል ነው።

በክረምትም ሆነ በበጋ የሚልማ ሰፊ መሬት ያላት እና በየትኛውም ሥነምህዳር ውስጥ መብቀል የሚችሉ
ተክሎችን ማበቀል የሚያስችል ሥነምህዳር ያላት ሀገር ነች። ከዚህም በተጨማሪ ያልታረሰ ሰፊ መሬት ያላት
እና በዝናብ እና በመስኖ ሊለማ የሚችል እምቅ ሀብት ያደላት ሀገር መሆኗ በግብርናው ዘርፍ ለሚሰማራ
ባለሀብት ሁሉ በርካታ አማራጮች የሚገኝባት ሀገር ነች፡፤በኢንዱስትሪውም መስክ ቢሆን 130 ሚሊዮን የሚጠጋው ሕዝብ ለባለሀብቶች ሰፊ ገበያ ነው።

ለባሕር ባላት ቅርበትም ባለሀብቶች በቀላሉ ምርቶቻችውን ወደተለያዩ ሀገራት የሚልኩበት አማራጭ ሰፊ ነው።
መንግሥት ኢንዱስትሪዎችን የሚደግፉ ‹‹ኢትዮጵያን ታምርት ›› የመሳሰሉ መነሳሳቶች ውስጥ መግባቱ
ባለሀብቶች በተነቃቃ የኢንዱስትሪ ምህዳር ውስጥ እንዲያመርቱ ምቹ ሁኔታዎችን ይፈጥርላቸዋል።
የሚገጥሟቸውንም ተግዳሮቶች በቀላሉ ለመፍታት ያስችላቸዋል።

ከዚህ በተጨማሪም ኢትዮጵያ ያላት ውብ እና ማራኪ የተፈጥሮ ሀብቶችም ቱሪዝምን በመሳሰሉ
የአገልግሎት ዘርፎች ቢሰማሩ በቀላሉ ውጤታማ የሚሆኑበት ነው። የሰው ልጅ መገኛ ፤ የተለያዩ የተፈጥሮ
እና ሰው ሠራሽ ሀብቶች መገኛ በሆነችው ኢትዮጵያ ኢንቨስት ማድረግ በቀላሉ ውጤታማ ያደርጋል።
ከዚህ በሻገርም ለባለሀብቶች የሚደረጉ ማበረታቻዎች እና እየተደረጉ ያሉ የሕግና ፖሊሲ ማሻሻያ
ርምጃዎች ለውጭ ቀጥታ ኢንቨስትመንት ምቹ ሁኔታ እየፈጠሩ ነው። ከዚህ ቀደም የነበሩ የተንዛዙ
አሠራሮችን በማስተካከል እና አንድ ማዕከል አገልግሎት መስፋፋትም ከጊዜ ወደ ጊዜ ባለሀብቱ ፊቱን ወደ
ኢትዮጵያ እንዲያዞር እያደረጉት ነው።

ካለፈው ሀምሌ ወር ጀምሮ መተግበር የጀመረው የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያም ለኢንቨስትመንት እድገቱ
የራሱን አወንታዊ አስተዋጽኦ እያበረከተ ይገኛል። ኢትዮጵያ የተገበረችው የተሟላ የማክሮ ኢኮኖሚ
ማሻሻያ፣ ተቋማዊ እና መዋቅራዊ ችግሮችን የሚፈቱ ሪፎርሞች ዘላቂ ሀገራዊ ዕድገትን የሚያመጡ ናቸው።
ኢንቨስትመንቱን እንዲያነቃቁ ታስበው የተወሰዱ የሕግና የፖሊሲ ማሻሻያዎች እንዲሁም የንግድና
ኢንቨስትመንት ምህዳሩን የመክፈት ርምጃዎችም ትልቅ ውጤት እያመጡ ነው። የኢትዮጵያ ካፒታል ገበያ
ወደ ሥራ መግባቱም ተወዳዳሪ እና በግሉ ዘርፍ የሚመራ ኢኮኖሚ ለመገንባት ጉልህ አስተዋጽኦ ከማድረጉም
በላይ ኢንቨስትመንት እንዲነቃቃ የማይተካ ሚና ይጫወታል።

በአጠቃላይ ኢንቨስትመንትን ለማነቃቃት የተወሰዱ አወንታዊ ርምጃዎች ከጊዜ ወደ ጊዜ በተለያዩ መስኮች
የሚሰማሩ ባለሀብቶችን ቁጥር እያሳደገው ይገኛል። ያለፉት ስምንት ወራት አፈጻጸምም የሚመለክተው
ይህንኑ ሀቅ ነው። ባለፉት ስምንት ወራት ወደ 2 ነጥብ አምስት ቢሊዮን ዶላር ኢንቨስትመንት ተስቧል፤
ወደ 363 ፈቃዶች ተሰጥተዋል።

የተሰጡ ፈቃዶች በየዘርፉ ሲታይ ደግሞ በግብርና 10 በማኑፋክቸሪንግ 207 በአገልግሎት ዘርፍ 146
ፈቃዶች ተሰጥተዋል። በባለቤትነት ሲታይ 143 የውጭ ፈቃድ ሲሆን ፣ ከውጭና ከሀገር ውስጥ በተፈጠሩ
ጥምረቶች ደግሞ ወደ 44 የሚደርሱ ፈቃድ ተሰጥቷል። ለሀገር ውስጥ ደግሞ ወደ 33 የሚሆኑ አዳዲስ
ፈቃዶች ወጥተዋል።

በአጠቃላይ ኢትዮጵያ እየተከተለች ያለችው የኢንቨስትመንት ማነቃቂያ ስትራቴጂ በርካታ የውጭ
እና የሀገር ውስጥ ባለሀብቶችን ወደ ኢንቨስትመንት እንድትስብ አስችሏታል። በቀጣም ዘርፉን የበለጠ
ሊያበረታቱ የሚያስችሉ ርምጃዎችን መውሰድ ያስፈልጋል።

ኢንቨስትመንቱ የበለጠ እንዲያብብ እና ለሀገራዊ ኢኮኖሚ ያለው ድርሻ የጎላ እንዲሆን ያልተነኩ
የኢንቨስትመንት እድሎችን እና የተዘረጉ ምቹ የአሠራር ሥርዓቶችን በአግባቡ ማስተዋወቅ ይገባል።
ፖሊሲዎቿም ለኢንቨስትመንት ምቹ መሆናቸው እና በመሠረተ ልማት የተሰሩ ተግባራትን እና
የተዘረጉ ቀልጣፋ አገልግሎቶችን በየአጋጣሚው የማስገንዘብ ሥራዎች በሰፊው ሊሠራ ይገባል። በዚህ
ረገድ ሰሞኑን የተጀመረው እና ከ 59 ሀገራት በላይ የተሳተፉበት ኢንቨስት ኢትዮጵያ 2025 ለዚህ ጥሩ ማሳያ
የሚሆን ነው።

አዲስ ዘመን ሐሙስ ግንቦት 7 ቀን 2017 ዓ.ም

 

 

Recommended For You