
የአዲስ አበባ ብስክሌት ፌዴሬሽን ሲያካሂድ የቆየው ውድድር ተጠናቀቀ። የክለቦች፣ ታዳጊዎች፣ የግል ተወዳዳሪዎችና የጤና ቡድኖች ዓመታዊው የብስክሌት ቻምፒዮና ከመጋቢት 28 ጀምሮ በየሳምንቱ ሲካሄድ ቆይቶ ባለፈው እሁድ ፍፃሜውን ያገኘ ሲሆን በሁለቱም ፆታ በተለያየ ካታጎሪ በርካታ ብስክሌተኞች ተፎካካሪ ሆነዋል።
በታዳጊ ሴቶች ማውንቴን ብስክሌት ውድድር በድምር ውጤት ጽናት አብርሃም አሸናፊ በመሆን ስታጠናቅቅ፣ ቤተልሄም ተስፋዬ ሁለተኛ እና ሲፈን ፈይሳ ሦስተኛ ደረጃን በመያዝ የወርቅ፣ የብርና የነሐስ ሜዳሊያ ተሸላሚ ሆነዋል። በተመሳሳይ ውድድር በወንዶች ሚሊዮን በዛብህ አንደኛ ሆኖ ሲፈፅም፣ ቸርነት ቀኜ ሁለተኛ እና በእሱፈቃድ በላይ ሦስተኛ ደረጃን በመያዝ ውድድራቸውን አጠናቀዋል።
በአዋቂ ወንዶች ማውንቴን ዮናስ አበበ በቀዳሚነት በማጠናቀቅ የወርቅ ሜዳሊያና ዋንጫ ተሸላሚ ሲሆን፣ ሃይለኢየሱስ ደምስ እና ሲሳይ ፍቅሩ ሁለተኛ እና ሶስተኛ በመሆን አጠናቀዋል።
ብርቱ ፉክክር በታየበት የክለቦች የግል ክሮኖ ሜትር ፉክክር ዮሐንስ ታሪኩ ከሸገር ሲቲ በአንደኝነት ሲያጠናቅቅ፣ ሰለሞን ዓለሙ እና አእምሮ መንግሥቱ ከአዲስ አበባ ፖሊስ ሁለተኛ እና ሶስተኛ በመሆን ውድድራቸውን አጠናቀዋል። በክለቦች የቡድን ክሮኖ ሜትር ፉክክር ደግሞ አዲስ አበባ ፖሊስ፣ ኢትዮ ኤሌክትሪክ እና ሸገር ሲቲ ከአንደኛ እስከ ሶስተኛ ያለውን ደረጃ ይዘው ፈፅመዋል።
በሴቶች የኮርስ ብስክሌት ፉክክር ጺዮን ፍስሐ ውድድሯን በበላይነት ስታጠናቅቅ ትዕግስት ካሳሁን እና ማርታ ካሳሁን ሁለተኛ እና ሶስተኛ ሆነው አጠናቀዋል።
በወንዶች የዙር ውድድር በድምር ውጤት በግል አሸናፊ የሆነው አብስራ ፍፁም ሲሆን፣ ሸምሰዲን ሬድዋን ሁለተኛ ሆኗል። ሁለቱም ብስክሌት ጋላቢዎች የኢትዮ ኤሌክትሪክ ተወዳዳሪዎች ናቸው። ያሬድ ተካ ደግሞ ከአዲስ አበባ ፖሊስ ሦስተኛ በመውጣት ያጠናቀቀ ብስክሌተኛ ነው።
በክለቦች የዙር ውድድር ድምር ውጤት ኢትዮ ኤሌክትሪክ ውድድሩን በበላይነት ሲያጠናቅቅ፣ አዲስ አበባ ፖሊስ ሁለተኛ እና ኢትዮጵያ ስፖርት አካዳሚ ሦስተኛ በመሆን ውድድራቸውን አጠናቀዋል። በጤና ቡድኖች መካከል በተደረገው ፉክክር እሸቱ ማዴቦ አንደኛ ሆኖ ሲፈፅም፣ ቢኒያም መርዕድ ሁለተኛ እና አብርሃም ወልደጻድቅ ሦስተኛ ደረጃን በመያዝ ውድድራቸውን አጠናቀዋል።
የውድድሩ ዓላማ ከተማ አስተዳደሩን በመላው ሀገር አቀፍ ውድድሮች በብስክሌት ስፖርት የሚወክሉ ምርጥ ስፖርተኞችን ለመምረጥ እንሚረዳ ፌዴሬሽኑ ገልጿል። የአዲስ አበባ ብስክሌት ፌዴሬሽን የጽሕፈት ቤት ኃላፊ አቶ ሲሳይ ተረፈ እንደገለጹት፣ ውድድሩ የክለቦች አቋም የሚለካበት እና በያዝነው ግንቦት ወር መጨረሻ ለሚካሄደው የመላ ኢትዮጵያ ጨዋታዎች ከተማ አስተዳደሩን የሚወክሉ ምርጥ ስፖርተኞን ለመምረጥ ያስችላል።
በውድድሩ መዝጊያ መርሃግብር በተለያዩ ካታጎሪዎች አንደኛ ለወጡ ብስክሌተኞችና ክለቦች የዋንጫ እና የወርቅ ሜዳልያ እንዲሁም ሁለተኛ እና ሦስተኛ ሆነው ላጠናቀቁ የብር እና የነሐስ ሜዳልያ ሽልማት ከእለቱ የክብር እንግዶች ተበርክቷላቸዋል።
በጋዜጣው ሪፖርተር
አዲስ ዘመን ረቡዕ ግንቦት 6 ቀን 2017 ዓ.ም