የትግራይ ሕዝብ በተዛቡ ትርክቶች ሳይደናገር ስለ ኢትዮጵያ የጸና አቋሙን በተግባር እያሳየ ነው

አዲስ አበባ፡- የትግራይ ሕዝብ የኢትዮጵያ ጠል ፖለቲከኞች ለዘመናት ባራመዱት የመነጠል ትርክት ሳይደናገር ስለ ኢትዮጵያ የጸና አቋሙን በተግባር እያሳየ ነው ሲሉ የፕሪቶሪያ የሰላም ንግግር ዋና ተደራዳሪዎች የነበሩት እና የጠቅላይ ሚኒስትሩ የምሥራቅ አፍሪካ ጉዳዮች አማካሪ ሚኒስትር አቶ ጌታቸው ረዳና የብሔራዊ መረጃና ደህንነት አገልግሎት ዳይሬክተር ጀኔራል አምባሳደር ሬድዋን ሁሴን ገለጹ፡፡

የፕሪቶሪያ የሰላም ንግግር ዋና ተደራዳሪዎች የነበሩት እና የብሔራዊ መረጃና ደህንነት አገልግሎት ዳይሬክተር ጀኔራል አምባሳደር ሬድዋን ሁሴን እና የጠቅላይ ሚኒስትሩ የምሥራቅ አፍሪካ ጉዳዮች አማካሪ ሚኒስትር አቶ ጌታቸው ረዳ ከኢዜአ ጋር ቆይታ አድርገዋል። በቆይታቸውም የሰሜኑ ግጭት ከተከሰተ በኋላ ከፌዴራል መንግሥቱ ጋር የሰላም ንግግሮች እየተደረጉ ባሉበት ወቅት ስምምነት እንዳይደረስ እንዲሁም ግጭትና መከፋፈል እንዲቀጥል የሚፈልግ ጥቂት የቀድሞ ሕወሓት ቡድን ነበር ብለዋል።

አቶ ጌታቸው ረዳ፤ ይህ ቡድን የራሱን የሥልጣንና የሀብት ጥቅም ከማጋበስ ያለፈ አላማ እንደሌለው በመግለጽ፤ የትግራይን ሕዝብ እንደማይወክልም አንስተዋል። በግጭቱ ወቅት እኛ ኢትዮጵያ ትውደም እያልን እንኳ በትግራይ አብያተ ክርስቲያናት ጭምር ኢትዮጵያዊነት ይሰበክ ነበር ብለዋል።

የትግራይ ሕዝብ ኢትዮጵያዊነቱን አጽንቶ የኖረ ነው ያሉት አቶ ጌታቸው፤ ለዘመናት ኢትዮጵያ ጠል ኃይሎች ሲነዛ በኖረ የመነጠል ትርክት ሳይደናገር ስለ ኢትዮጵያ የጸና አቋሙን በተግባር ማሳየቱንም አንስተዋል።

በግጭቱ ወቅት ሕዝቡ ኢትዮጵያን እንዲጠላ ለማድረግ በተሰራጩ የተዛቡ ትርክቶች መጥፎ ስሜቶች መፈጠራቸውን ያነሱት አቶ ጌታቸው፤ ሕዝቡ ችግር ሲፈጠርም የሚመጣው ወደ አስመራ ሳይሆን ወደ አዲስ አበባ ነው ብለዋል።

አምባሳደር ሬድዋን ሁሴን በበኩላቸው፤ አንዳንድ አካላት የግልና የንዑስ ቡድን ኩርፊያቸውን የመነጠል ትርክትን በማቀንቀን ለማሳየት ይሞክራሉ ብለዋል።

ለግል ጥቅማቸው ሲሉ ግጭትን በማራዘም የፕሪቶሪያው የሰላም ስምምነት አፈጻጸም እንዲደናቀፍ ተደጋጋሚ ሙከራ እንደሚያደርጉ በማንሳት፤ ሆኖም ጸብም ካለ ከኢትዮጵያ ጋር ሳይሆን ከአስተዳደር ጋር መሆን ነበረበት ነው ያሉት።

የትግራይ ሕዝብ የመነጠል ትርክት በሚያቀነቅኑ አካላት ቅንጣት ታክል የመደናገር ስሜት እንደሌለው በማንሳት፤ በኢትዮጵያዊነት ማሕቀፍ ውስጥ ዘላቂ ሰላም የማረጋገጥና በጋራ የመልማት ፍላጎት ነው ያለው ብለዋል።

በግጭቱ የተፈጠሩ መጥፎ ስሜቶችን በማረቅ የጋራ እጣ ፈንታን በአንድነት ለማሳካትም የወል ትርክትን መገንባት እንደሚገባ ገልጸዋል።

ተደራዳሪዎቹ አክለውም፤ የፕሪቶሪያ የሰላም ስምምነት በመፈረሙና የሰው ሕይወት በመትረፉ የሚቆጫቸው አንዳንድ አካላት አሁንም ግጭት እንዲፈጠር ፍላጎት አላቸው ብለዋል።

“ለአብነት ላለፉት ሁለት ዓመታት ተፈናቃዮች ወደ ቀያቸው እንዲመለሱ የፌዴራል መንግሥቱ የጀመራቸውን ሂደቶች እያደናቀፉ በቁስላቸው እየነገዱባቸው መሆኑንም ተናግረዋል።”

የፌዴራል መንግሥቱ በክልሉ የፕሪቶሪያ የሰላም ስምምነትን በማስፈጸም ረገድ በርካታ ተግባራት ማከናወኑን ጠቅሰው፤ተፈናቃዮችን የመመለስ ሥራ ተጀምሮ ነበር። ሆኖም ተፈናቃዮች ወደቀያቸው እንዳይመለሱና በድንኳን እንዲሰቃዩ እያደረገ በቁስላቸው የሚነግደው ኃይል ሂደቱን እያደናቀፈ ነው ብለዋል።

ይህ ኃይል የተፈናቃዮች መመለስና የትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር ሥራውን በአግባቡ መሥራት ጥቅሙን ስለሚያስቀርበት አሁንም ችግር እየፈጠረ እንደሚገኝ ጠቅሰዋል።

በጋዜጣው ሪፖርተር

አዲስ ዘመን ሐሙስ ግንቦት 14 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You