
አዲስ አበባ፡- ‹‹ከልባቸው ሰላምን የሚፈልጉ አመራሮች እንዳሉ ሁሉ በወርቅ ንግድ ላይ የተሠማሩ ዘራፊዎችም አሉ ሲሉ የቀድሞው የትግራይ ክልል ጊዜያዊ ፕሬዚዳንትና በአሁኑ ጊዜ በምስራቅ አፍሪካ ጉዳዮች የጠቅላይ ሚንስትሩ አማካሪ ሚንስትር አቶ ጌታቸው ረዳ ገለጹ።
አቶ ጌታቸው ሰሞኑን ከፋና ሚዲያ ኮርፖሬሽን ጋር በነበራቸው ቆይታ የትግራይ ክልል ወቅታዊ ሁኔታን አስመልክቶ እንደተናገሩት፤ አብዛኛው የሠራዊት አመራር በሰላም የትግራይ ህልውና እስከተረጋገጠ ድረስ ጥይት የመተኮስ ፍላጎት የለውም። በወንጀል ተነክረው ድንገት የሆነ ሰላም ከተፈጠረ ተጠያቂነት ውስጥ እንገባለን ብለው የሚያስቡ ሰዎች ግን ግርግር በፍፁም እንዲያልቅ አይፈልጉም ብለዋል።
የወርቅ ንግዳቸውንና ዘረፋቸውን ለማስቀጠል የሚፈልጉ ጥቂት አካላት በትግራይ ወጣት መሥዋዕትነት እንድናለን የሚል አስተሳሰብ ይዘው የሚፎክሩ መሆኑን አቶ ጌታቸው ገልጸው፤ ከመንግሥት ካዝና የወጣ በመቶ ሚሊዮን የሚቆጠር ገንዘብ የዘረፉ ሰዎች አሁን በትግራይ አንድነት ስም የትግራይን ወጣት ለማገዶነት እንዳርገዋለን በሚል የሚፎክሩ መሆናቸውን አስረድተዋል።
በአሁኑ ጊዜ የፌዴራል መንግሥት ድንገት ውጊያ ይገጥመናል በሚል ስጋት ውጊያው ትግራይ ውስጥ እንዲሆን የሚያስችል ስትራቴጂ መቀየሳቸውን አቶ ጌታቸው አመልክተው፤ በዚህም ፌዴራል መንግሥቱ ትግራይ ውስጥ ይዳከማል የሚል ስሌት መያዛቸውን ገልጸዋል።
አቶ ጌታቸው በኢትዮጵያና በኤርትራ መካከል ጦርነት መፈጠር እንደሌለበትና የትግራይ ክልልና ሕዝብም ድጋሚ የጦር አውድማ እንዳይሆን እስከ መጨረሻው ድረስ የሚታገሉ እንደሆነ አቋማቸውን ገልጸዋል፡፡
አብዛኛው የሠራዊት አመራር የትግራይ ሰላም እስከተረጋገጠ ድረስ ጥይት የመተኮስ ፍላጎት እንደሌለው የተናገሩት አቶ ጌታቸው፤ እነዚህም ከልባቸው ሰላምን የሚፈልጉ ሕዝባቸውን ማገልገል የሚፈልጉ እንደሆኑ አመልክተዋል። በአንጻሩ የሰላም እንቅፋት የሆኑት በወርቅ ንግድ ላይ የተሠማሩ ዘራፊዎች እንደሆኑ ስም በመጥቀስ ጭምር ገልጸዋቸዋል።
ዳግማዊት ግርማ
አዲስ ዘመን ረቡዕ ግንቦት 6 ቀን 2017 ዓ.ም