
አዲስ አበባ ፦ የምስራቅ አፍሪካን ሰላምና ደህንነት ለማረጋገጥ ትብብርን ይበልጥ ማሳደግና ጠንካራ ተቋማትን መገንባት ወሳኝ መሆኑን ምክትል ጠቅላይ ሚንስትር ተመስገን ጥሩነህ ገለጹ።
ምክትል ጠቅላይ ሚንስትር ተመስገን ጥሩነህ የአፍሪካ ቀጣናዊ መረጃና ደህንነት ኮሚቴ የምስራቅ አፍሪካ ቀጣና ስብሰባ ትናንት በአዲስ አበባ ሲካሄድ ባደረጉት የመክፈቻ ንግግር፤ ኢትዮጵያ ለአብሮነትና ለአካባቢያዊ ሰላም ቁርጠኛ መሆኗን ገልጸው፤ የትኛውም ሀገር ጎረቤቶቹ በስጋት ውስጥ ሆነው ብቻውን ሊበለፅግ አይችልም የሚል ፅኑ አቋም እንዳላትም አንስተዋል።
ኢትዮጵያ ሉዓላዊነቷን ከማስጠበቅ ባለፈ በሌሎች ሀገራት ችግር ሲከሰት ሰላም በማስከበር እንዲሁም ለአፍሪካ ችግሮች አፍሪካ መር መፍትሔን በማራመድ መጓዟንም ጠቅሰዋል።
ምክትል ጠቅላይ ሚንስትሩ ኢትዮጵያ ለቀጣናው ዘላቂ ደህንነት በትብብር አበክራ እንደምትሠራም ተናግረዋል። አፍሪካ የተኩስ ድምፅ የማይሰማባትና ሰላማዊት አህጉር እንዲሁም ምስራቅ አፍሪካን የተረጋጋ ቀጣና የማድረግ ራዕይ ሊሳካ የሚችለው በትብብር፣ የጋራ ዓላማና በተግባር ቁርጠኝነት መሆኑን ገልጸዋል።
ቀጣናው አሁንም በፈተናዎች ውስጥ ነው ያሉት ምክትል ጠቅላይ ሚንስትሩ፥ ድንበር ተሻጋሪ ወንጀሎች፣ የሽብር ቡድን እንቅስቃሴዎች፣ ፅንፈኝነትና የተደራጁ የወንጀል ቡድኖች ትርምስ የሚፈጥሩበት መሆኑን ተናግረዋል።
ለቀጣናው ሰላም ትልቅ ስጋት ከሆኑት ጉዳዮች መካከል ዋነኛው አንዱ ሀገር በሌላው ሀገር ለሚንቀሳቀሱ የታጠቁ ቡድኖች በቀጥታና በተዘዋዋሪ ድጋፍ በማድረግ የሚፈጥራቸው የውክልና ግጭቶች ናቸው ብለዋል።
የውክልና ግጭቶች ዘርፈ ብዙ ጉዳት እንደሚያስከትሉ አይተናል ያሉት ምክትል ጠቅላይ ሚንስትሩ፥ ተቋማትን በመቦርቦር የዲፕሎማሲ ሥራዎችን ሲያውኩ፣ የሥርዓት አልበኝነት መገለጫ ሲያደርጉ መቆየታቸውን አንስተዋል።
የውክልና ግጭትና መሰል ችግሮችን በጊዜ መቀልበስ አስፈላጊ መሆኑን የገለጹት ምክትል ጠቅላይ ሚንስትሩ፥ ይህንንም በጋራ መከላከልና መቆጣጠር እንደሚገባ አንስተዋል።
ሀገራት በትብብር ኦፕሬሽን ሲፈጽሙና መረጃ ሲለዋወጡ የወንጀለኛ ቡድኖችን የትስስር መረብን በመበጣጠስ ማዳከምና የዜጎችን ሕይወት መታደግ እንደሚችሉ በተግባር መታየቱንም ጠቅሰዋል።
ሽብርተኝነትን በጋራ መዋጋት፣ የኮንትሮባንድ መስመሮችን መዝጋት፣ ወንጀልን የሚደግፉ የገንዘብ ምንጮችን ማድረቅ የግድ ነው ያሉት ምክትል ጠቅላይ ሚንስትሩ፥ በጋራ ስንቆም የበለጠ ስኬትን ማረጋገጥ እንችላለን ብለዋል።
የምስራቅ አፍሪካ ሀገራት ዘላቂ ሰላምና ደህንነትን ለማረጋገጥ ሦስት ተልዕኮዎች ላይ ትኩረት መስጠት እንደሚገባም አንስተዋል።
የመጀመሪያው ሀገራት የራሳቸውን የውስጥ ደህንነት በራስ አቅም መቆጣጠር እንጂ ከሌላ የውጭ አካል መጠበቅ እንደሌለባቸው ተናግረዋል። ሁለተኛው ጉዳይ ቀጣናዊ ትብብርን ማጠናከር መሆኑን ገልጸው፥ የመረጃና ደህንነት ተቋማት በየጊዜው መወያየት፣ መተባበር፣ መተማመንና የጋራ ርምጃ መውሰድ አለባቸው ነው ያሉት።
ሌላኛው ጠንካራ ተቋማትን መገንባት መሆኑን ጠቅሰው፥ ለዚህም የዘመኑን የደህንነት ስጋቶች በአግባቡ መቀልበስ የሚችሉ በዘመናዊ ቴክኖሎጂዎችና በብቁ ሙያተኞች የተደራጁ ማድረግ ወሳኝ መሆኑን አንስተዋል።
የአፍሪካ የመረጃና ደህንነት አገልግሎት ኮሚቴ የምስራቅ አፍሪካ ቀጣናዊ መድረክም ተግዳሮቶችን በመለየት በጋራ ለመፍታት ቁርጠኝነት የምንወስድበት ነው ብለዋል።
ኢትዮጵያ ከመቼውም ጊዜ በበለጠ ደህንነቱ የተጠበቀ፣ ጠንካራ እና ይበልጥ የተዋሃደ ቀጣና ለመፍጠር ዝግጁነቷን በማንሳት፥ ከቀጣናው ሀገራት ጋር ትብብሯን አጠናክራ እንደምትቀጥልም አረጋግጠዋል።
ኢትዮጵያ በመረጃና ደህንነት ዘርፍ ሽብርተኝነትንና የተደራጁ ድንበር ተሻጋሪ ወንጀሎችን በጋራ መከላከል የሚያስችል ተቋማዊ ሪፎርም ማድረጓን የገለጹት የብሔራዊ መረጃና ደህንነት አገልግሎት ዳይሬክተር ጀነራል አምባሳደር ሬድዋን ሁሴን፤ ሽብርተኝነት፣ ድንበር ተሻጋሪ ወንጀሎች፣ የሳይበር ጥቃት እና ግጭት የቀጣናው ስጋት ሆነው ቀጥለዋል። በቀጣናው የሚስተዋለውን የጸጥታና ደህንነት ስጋት በብቃት ለመመከት በሀገራት የጸጥታ ተቋማት መካከል የመረጃ ልውውጥ ወሳኝ መሆኑን ገልጸዋል።
ከዚህም ባለፈ በተቋማት መካከል ጠንካራ ትብብር በመፍጠር የቀጣናውን ሰላምና ጸጥታ ማረጋገጥ ይገባል ያሉት አምባሳደር ሬድዋን፤ የመረጃ ልውውጦችን በማሳደግ በምስራቅ አፍሪካ ሀገራት መካከል የጋራ ተልዕኮን በመፈጸም ፍላጎቶችን በአግባቡ ማሳካት እንደሚቻልም ጠቅሰዋል።
በኢትዮጵያ የብሔራዊ መረጃና ደህንነት አገልግሎት ለቀጣናው ሰላምና መረጋጋት የበኩሉን ሚና እየተወጣ መሆኑን ገልጸው፣ ሽብርተኝነትና ሌሎች ድንበር ተሻጋሪ ወንጀሎችን በጋራ መከላከል የሚያስችል ሪፎርም መደረጉንም ገልጸዋል።
ይህም የተቋሙን የፕሮፌሽናልና የቴክኒክ አቅም በዓለም አቀፍ ደረጃ ተወዳዳሪ ለማድረግና በእጅጉ ለማሻሻል አስችሏል ብለዋል፡፡
ከሁሉም በላይ ከበርካታ የደህንነትና የፀጥታ ተቋማት ጋር የተደረሱ የመግባቢያ ስምምነቶች በአቅም ግንባታና በመረጃ ልውውጥ ላይ ያለውን አቅም በእጅጉ ለማሳደግ ማስቻላቸውንም ተናግረዋል፡፡
የአፍሪካ ህብረት ኮሚሽን ሊቀ መንበር ተወካይና የሕብረቱ ኮሚሽን ጽህፈት ቤት ኃላፊ አምባሳደር መሀመድ አል አሚን ሱፍ ስብሰባው በቀጣናው ሰላምና መረጋጋት ላይ ለመምከር ወሳኝ ሰዓት መሆኑን ገልጸዋል።
የሳይበር ጥቃት፣ የፖለቲካ አለመረጋጋትና ሽብርተኝነትን የምሥራቅ አፍሪካ ቀጣና ሥጋት መሆናቸውን ገልጸው፤ በቀጣናው ሀገራት መካከል የተሳለጠ የመረጃ ልውውጥ ሊኖር እንደሚገባ ተናግረዋል።
በስብሰባው ኢትዮጵያን ጨምሮ የምስራቅ አፍሪካ 13 ሀገራት የመረጃና ደህንነት አገልግሎት ኃላፊዎች፣ ተቀማጭነታቸውን አዲስ አበባ ያደረጉ ዲፕሎማቶችና የዓለም አቀፍ ተቋማት ተወካዮች መሳተፋቸው ታውቋል።
በጋዜጣው ሪፖርተር
አዲስ ዘመን ረቡዕ ግንቦት 6 ቀን 2017 ዓ.ም