
አሜሪካ እና ቻይና አንዳቸው በሌላኛቸው ምርቶች ላይ የጣሉትን ታሪፍ ለ90 ቀናት ለመቀነስ ከስምምነት ደረሱ። የአሜሪካ የገንዘብ ሚንስትር ስኮት ቤሴንት ለ90 ቀናት ሁለቱም ሀገራት የጣሉትን ታሪፍ በ115 በመቶ ዝቅ ለማድረግ መስማማታቸውን ተናግረዋል።
ሁለቱ ኃያላን ሀገራት እዚህ ስምምነት ላይ መድረሳቸው የተገለፀው በሳምንቱ መጨረሻ በስዊትዘርላንድ በዝግ ንግግር ሲያደርጉ ከቆዩ በኋላ ነው። ይህ ንግግር ዶናልድ ትራምፕ ወደ አሜሪካ በሚገቡ ምርቶች ላይ ከፍተኛ ታሪፍ ከጣሉ በኋላ ለመጀመርያ ጊዜ የተደረገ ውይይት ነው።
ፕሬዚዳንት ትራምፕ ከቻይና በሚገቡ ምርቶች ላይ 145 በመቶ ታሪፍ ሲጥሉ ቤጂንግ በምላሹ ከአሜሪካ በሚገቡ ምርቶች ላይ 125 በመቶ ታሪፍ ጥላለች። ይሁን አንጂ አሁን አሜሪካ በቻይና ምርቶች ላይ የጣለችው ታሪፍ ለ90 ቀናት ወደ 30 በመቶ ዝቅ ስታደርግ፣ ቻይና በአሜሪካ ምርቶች ላይ የጣለችው ታሪፍ ደግሞ እንዲሁ ለተመሳሳይ ቀናት ወደ 10 በመቶ ይቀንሳል።
አሜሪካ ሕገወጥ የሆነውን የፌንታኒል ኦፒየድ ዕጽ ለመቆጣጠር በሚል ያካተተቻቸው ርምጃዎች እንዳሉ መሆናቸው ተገልጿል። የአሜሪካ ባለሥልጣናት የቻይና መንግሥት ችግሩን ለመፍታት ባሳየው ፈቃደኝነት መደነቃቸውን ተናግረዋል። አሜሪካ እና ቻይና የገቡበት የንግድ ጦርነት በፋይናንስ ገበያው እና በዓለም ላይ ግሽበትን ያስከትላል የሚል ፍርሃት ቀስቅሶ ነበር።
ቤሰንት ውይይቱን ‹‹ገንቢ እና ውጤታማ›› ሲሉ የገለፁት ሲሆን የቻይናው ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ሂ ሊፌንግ በበኩላቸው ንግግሮቹ ‹‹በጥልቀት›› እና በመግባባት›› የተካሄዱ መሆናቸውን ገልፀዋል። በጄኔቫ ሲደረግ የቆየው የሁለት ቀናት ንግግር መጠናቀቁን ተከትሎ የአሜሪካ የንግድ ተወካይ ጃሚየሰን ግሪር ከቻይናውያን አጋሮቻችን ጋር የደረስንበት ስምምነት አሜሪካ ያለባትን አንድ ነጥብ ሁለት ትሪሊዮን ዶላር የንግድ ጉድለት ይቀንሳል ብለዋል።
ቤሴንት አሜሪካ እና ቻይና በመካከላቸው የተፈጠረውን የንግድ ጦርነት በማቀዛቀዝ ረገድ ወሳኝ የሆነ ርምጃ ላይ መድረሳቸውን ሲናገሩ፣ ምክትል ጠቅላይ ሚንስትር ሂ ደግሞ ‹‹ንግግሩ ለሁለቱ ሀገራት ትልቅ ጠቀሜታ አለው። ለዓለም አቀፉ ምጣኔ ሀብት መረጋጋት እና እድገትም ትልቅ አስተዋጽኦ ይኖረዋል›› ብለዋል።
ምክትል ጠቅላይ ሚንስትር ሂ ሁለቱ ተደራዳሪ ወገኖች በዋና ዋና ጉዳዮች ላይ መግባባት ላይ መድረሳቸውን እንዲሁም የምጣኔ ሀብት እና ንግድ ምክክር መንገዶችን የሚያሳልጥ ቡድን ለመመስረት መስማማታቸውን ተናግረዋል።
የዓለም ንግድ ድርጅት ዋና ዳይሬክተር ንጎዚ ኦኮንጆ ኢዌላ፣ ንግግሩን ወደ ትክክለኛው አቅጣጫ የሚደረግ ጉዞ ሲሉ አድንቀውታል።
ዳይሬክተሯ ባወጡት መግለጫ፣ ‹‹ሁለቱም ሀገራት ውጥረቶችን የሚቀንሱ፣ የሚታየውን ሁኔታ የሚያድሱ እና በባለብዙ ወገን የግብይት ሥርዓት ላይ ያላቸውን እምነት በማጠናከር ተግባራዊ መፍትሄዎችን በማዘጋጀት ግስጋሴያቸውን አጠናክረው እንዲቀጥሉ አሳስባለሁ›› ብለዋል።
ቅዳሜ ዕለት ውይይቱ በጄኔቫ እንደተጀመረ ፕሬዚዳንት ትራምፕ በሁለቱ ሀገራት ግንኙነት ላይ የተደረገውን ንግግር ግንኙነታቸውን ዳግም ማስጀመር ሲሉ አድንቀውታል። አርብ ዕለት ውይይቱ ከመጀመሩ በፊት የዋይት ሐውስ የፕሬስ ሴክሬታሪ ካሮሊን ሌቪት ዋሺንግተን ብቻዋን ታሪፍ እንደማትቀንስ ገልፀው፣ ቻይና የራሷን ድርሻ መወጣት አለባት ብለዋል።
ሁለቱም ወገኖች ከስብሰባው በፊት የተለያዩ ማስጠንቀቂያዎችን የሰጡ ሲሆን ቤጂንግ ‹‹ዩናይትድ ስቴትስ ታሪፎችን ማቃለል አለባት›› ስትል፣ ቤሰንት ግን ትኩረቱ ውጥረት ማርገብ ላይ እንደሆነና ይህ ትልቅ የንግድ ስምምነት እንዳልሆነ አፅንኦት ሰጥተው ተናግረው ነበር።
የቻይና መንግሥት ሚዲያ እንደዘገበው ቤጂንግ ከአሜሪካ ጋር ለመነጋገር የወሰነችው ዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ የሚጠብቀውን፣ የሀገሪቱን ጥቅም እና የአሜሪካን ነጋዴዎች ጥሪን ሙሉ በሙሉ በማጤን ነው።
በአሜሪካ እና በቻይና መካከል ያለው የንግድ ጦርነት የተካረረው ዶናልድ ትራምፕ ባለፈው ወር ከቻይና የሚገቡ ምርቶች ላይ ከፍተኛ የሆነ ታሪፍ መጣላቸውን ተከትሎ እንደሆነ ቢቢሲ በዘገባው አስታውሷል።
አዲስ ዘመን ማክሰኞ ግንቦት 5 ቀን 2017 ዓ.ም