
በጤናው ዘርፍ የነበሩ ሀገራዊ ስብራቶችን ለማከም ከለውጡ ማግሥት ጀምሮ መንግሥት ሰፋፊ ሥራዎችን ሢሠራ ቆይቷል። ከችግሩ ስፋት አኳያ ገና ብዙ መሥራት የሚጠይቅ ቢሆንም በለውጥ ዓመታት ውስጥ የተከናወኑ ተግባራት እያስገኙ ያለው ውጤት ተስፋ ሰጭ ስለመሆናቸው የአደባባይ ሚስጥር ነው። የባላድርሻ አካላት ከፍ ባለ የኃላፊነት መንፈስ መንቀሳቀስ ከቻሉ የዘርፉን ስብራቶች ለመጠገን የተጀመሩ ሀገራዊ ጥረቶች ስኬታማ እንደሚሆኑ ይታመናል ።
የዘርፉን ስብራት ለመጠገን የሚደረጉ ጥረቶች በዋነኛነት ዘርፉን በቴክኖሎጂ ከማዘመን፤ የሰው ኃይል አቅም ከማሳደግ እና የጤና መሰረተ ልማቶችን ከማስፋፋት ጋር የተያያዙ ናቸው። በዚህም ባለፉት ስድስት ዓመታት ከፍተኛ ሀብት በመመደብ የጤና መሰረተ ልማቶችን የማስፋፋት ሥራዎች ተከናውነዋል። ከፍተኛ የውጪ ምንዛሬ በመመደብም ዘርፉን ዘመኑ ባፈራው ቴክኖሎጂ ለመደገፍ ረጅም ርቀት ተሄዷል። በዘርፉ የተሠማሩ ባለሙያዎችን አቅም ለማሳደግ የተደረጉ ጥረቶችም ሰፋፊ ናቸው።
እንደ ሀገር እየተከሰተ ያለውን የዋጋ ግሽበት ተከትሎ አጠቃላይ ሲቪል ሰርቪሱ እያጋጠመው ያለውን ችግር ለመፍታት በመንግሥት በኩል እየተደረጉ ያሉ ስትራቴጂክ የመፍትሄ አማራጮችም በዘርፉ የተሰማሩ ባለሙያዎችን ተጠቃሚ እያደረጉ ናቸው። በተለየ መልኩ የዘርፉ ባለሙያዎች ተጨማሪ የገቢ ምንጭ የሚፈጥሩባቸውን ስትራቴጂክ አማራጮች አቅም በፈቀደ መጠን ተግባራዊ መሆን ከጀመሩም ዓመታትን አስቆጥረዋል
በሚሠሩባቸው ተቋማት ከሥራ ሰዓት ውጪ፤ በመንግሥት የጤና መሰረተ ልማቶች ተጠቅመው አገልግሎት በመስጠት ተጨማሪ የኢኮኖሚ አቅም የሚፈጥሩበት ሁኔታ ተመቻችቶላቸው ተጠቃሚ እየሆኑ ነው። እንደ አንድ የሕዝብ አገልጋይ የሀገሪቱን ኢኮኖሚ ታሳቢ ባደረገ መንገድ ከፍያ እንደሚፈጸምላቸውም ግልጽ ነው ።
የጤናው ዘርፍ የራሱ የሆነ ባህሪ እንዳለው ቢታወቅም፤ ሀገራዊ የሆነው ሲቪል ሰርቪስ አካል ነው፤ የሚመራባቸው የራሱ የሆኑ ሙያዊ መርሆዎች ቢኖሩትም፤ እንደ ሲቪል ሰርቫንት ሀገሪቱ በደረሰችበት የኢኮኖሚ አቅም የሚሰላ ተከፋይነት ይጠብቀዋል። ይህ በየትኛውም መስክ ለሚሰማራ ሲቪል ሰርቫንት የሚሠራ መርኅ ነው።
ይህንን እውነታ ባልተገባ መንገድ ለመቀልበስ የሚደረጉ ሙከራዎች በዘርፉ የተጀመሩ የለውጥ ሥራዎችን ከማደብዘዝ ባለፈ ብዙም ትርጉም ያለው ለውጥ ሊያመጡ አይችሉም። ግርግር በመፍጠር የዘርፉን ጤናማ አካሄድ አደጋ ውስጥ ከመክተት ባለፈም ችግር ፈች ሊሆን አይችልም። ለጥፋት ኃይሎች መጠቀሚያ ከመሆን ባሻገር በራሱ መፍትሄም አይሆንም።
እንደ ማንኛውም የመብት ጥያቄ የዘርፉ ባለሙያዎች ጥያቄዎቻቸውን ለሚመለከተው አካል አቅርበው መነጋጋር እና መወያየት ይችላሉ። ይህ ዘመኑ የሚዋጅ ችግሮችን ለዘለቄታ የመፍታት የተሻለው አማራጭ ነው። መፍትሄ በማፈላለግ ሂደት ውስጥም ስኬታማ መሆን የሚቻለውም በዚህ መንገድ ብቻ ነው። ከዚህ ውጪ ፍላጎቶችን ባልተገባ መንገድ በሕዝብ እና በመንግሥት ላይ ለመጫን የሚደረጉ ጥረቶች አዋጭ አይሆኑም።
በተለይም እንደ ሀገር አሁን ካለንበት ሀገራዊ እውነታ አኳያ እንዲህ አይነቱ የተሳሳተ መንገድ፤ በሀገር እና በሕዝብ ጥቅሞች ላይ አድብተው ለጥፋት ለሚንቀሳቀሱ ኃይሎች መሣሪያ ከመሆን ያለፈ ፋይዳ አይኖረውም። ባለሙያዎች ለሙያቸው እና ለሚያገለግሉት የራሳቸው ሕዝብ ያላቸውን ተቆርቋሪነት በአደባባይ ከማደብዘዝ ባለፈም ሊያመጣ የሚችለው አዲስ ነገር አይኖርም።
በማናቸውም መመዘኛ አድመኝነት የዚህ ዘመን ችግር የመፍቻ አማራጭ አይደለም፤ አግባብ ባለው መንገድ ተጨባጭ እውነታዎችን ተረድቶ ችግሮችን በውይይት እና በድርድር መፍታት ከሁሉም የሚጠበቅ፤ ችግሮችን ለዘለቄታው መሻገር የሚያስችል ትክክለኛው አማራጭ ነው። ይህንን እውን ለማድረግ የጤና ባለሙያዎች ራሳቸውን በሁሉም መንገድ ማዘጋጀት ይጠበቅባቸዋል።
ከዚህ ውጪ አድማ በመምታት ዘርፉን ከዚያም በላይ ሀገርን ተጨማሪ ግርግር ውስጥ ለመክተት የሚደረግ የትኛውም ዓይነት ጥረት፤ የሕግ እና የሞራል ተጠያቂነት የሚያስከትል ይሆናል፤ መላው ሕዝባችን የተሻሉ ነገዎችን ተጨባጭ ለማድረግ ብዙ ዋጋ ከፍሎ በጀመረው የለውጥ ጉዞ ላይ ተግዳሮት ሆኖ መቆምም ጭምር ነው !
አዲስ ዘመን ማክሰኞ ግንቦት 5 ቀን 2017 ዓ.ም