
አዲስ አበባ፡- የኢትዮጵያ ጂኦፓርኮች ለማህበረሰብ ጥቅም እና ለሥራ ፈጠራ እንዲውሉ ከዩኔስኮ ጋር እየተሠራ መሆኑን የቱሪዝም ሚኒስቴር አስታወቀ። በዓለም አቀፍ ደረጃ 229 ገደማ ጂኦፓርኮች መመዝገባቸውን አመለከተ፡፡
የቱሪዝም ሚንስትር ሰላማዊት ካሳ ፤ ሚንስቴሩ ከዩኔስኮ ጋር በመሆን ባዘጋጀው ቀጣናዊ መድረክ ላይ እንዳመለከቱት ፤ የኢትዮጵያ ጂኦፓርኮች ለማህበረሰብ ጥቅም እና ለሥራ ፈጠራ እንዲውሉ ከዩኔስኮ ጋር እየተሠራ ነው።
ኢትዮጵያ በቱሪዝም ዘርፍ ትልቅ አቅም እንዳላት ያመለከቱት ሚንስትሯ፤ ኢትዮጵያ ጂኦፓርኮቿን በማስመዝገብ እና ተፈጥሯዊ ይዘታቸውን ለመጠበቅ እያደረገች ያለው ጥረት ለሌሎች ሀገራትም ምሳሌ ነው ብለዋል።
ጂኦፓርኮች የምድርን ተፈጥራዊ ታሪክ የሚነግሩን እና የሰው ልጆችን ተፈጥሯዊ አኗኗር እና ጥንታዊነት እንዲሁም ባህል አስተሳስሮ የያዘ የሳይንስ እና የምርምር ዘርፍ ነው ያሉት ሚንስትሯ፤ ዩኔስኮ በዓለም አቀፍ ደረጃ አሁን ላይ በትኩረት እየሠራባቸው ከሚገኙት ዘርፎች መካከል ዋነኛው እንደሆነ አስታውቀዋል፡፡
በቅርቡ ይፋ የሚሆነው የኢትዮጵያ የተሻሻለው የቱሪዝም ፖሊሲም የጂኦ ፓርኮችን ለመጠበቅና ለማቋቋም እንዲሁም የጂኦ ቱሪዝም ሀብቶችን ለመንከባከብ አይነተኛ አስተዋጽኦ እንደሚኖረውም አመልክተዋል።
በምስራቅ አፍሪካ የተለያዩ የጂኦሎጂ ቅርሶች አሉ፣ ነገር ግን በአህጉሪቱ ያለው የጂኦ-ቱሪዝም ልማት ዝቅተኛ ነው፤ ይህንን ወደ ተሻለ ደረጃ ለመቀየርና ቱሪዝምን ለቀጣናው ዘላቂ ልማት ለማዋል መሥራት ይጠበቅብናል ብለዋል።
በዘርፉ ላይ ላለፉት አስር ዓመታት ዩኔስኮ ሲሠራ መቆየቱን የጠቀሱት ሚንስትሯ፤ የዓለም ጂኦፓርኮች የመጠበቅ እና ልዩ ተፈጥሯዊ ይዘት ያላቸውን ቦታዎች የመንከባከብ እንዲሁም በፓርኮቹ ዙሪያ ግንዛቤ ማስጨበጫ ሥራዎች ተሠርተዋል፤ በዚህም በዓለም አቀፍ ደረጃ 229 ገደማ ጂኦፓርኮች መመዝገባቸውን ገልጸዋል።
አፍሪካን የሚያክል በተፈጥሮ እጅግ የታደለ አህጉር ሁለት ጂኦፓርኮች ብቻ ናቸው የተመዘገቡት ያሉት ሚንስትሯ ፤ ይህንን እውነታ ማስቀየር የሚቻለው ስለ ጂኦፓርኮች የተሻለ ግንዛቤ መፍጠር ሲቻል ብቻ እንደሆነም ጠቁመዋል።
ሀብቱን በተለይ ለማህበረሰቡ ጠቀሜታ እንዲሰጡ ለማድረግ ትልቅ የግንዛቤ ማስጨበጫ ሥራ መሥራት እንደሚያስፈልግ ፤ ለዚህም ሚንስቴር መሥሪያ ቤቱ ከዩኔስኮ ጋር በጋራ እየሠራ መሆኑን አስታውቀዋል፡፡
በአፍሪካ በዩኔስኮ ከተመዘገቡ ሁለት ጂኦፓርኮች መካከል አንዱ ታንዛንያ ውስጥ እንደሚገኝ አስታውቀው፤ በመድረኩ ላይ ከታንዛንያ በመጡ ባለሙያዎች የልምድ ልውውጥ እንደሚደረግ ጠቁመዋል፡፡ በቀጣናው የሚገኙ ስድስት ሀገራት ተሳታፊዎች መሆናቸውን ጠቁመዋል።
በሀገራችን ለጂኦፓርክ ምዝገባ ምቹ የሆኑ ቦታዎች አሉ ያሉት ሚንስትሯ፤ ጂኦፓርኮች እንደ ሌላው የፓርክ ዓይነት ተነጥለው የሚጠበቁ ሳይሆን፤ ዋናው መሠረታዊ እሴታቸው ከማህበረሰቡ ጋር መተሳሰራቸው እና ራሱ ማህበረሰቡ የሚያስተዳድራቸው፤ የሥራ ፈጠራ እና የሥራ ዕድል ተጠቃሚ የሚያደርግባቸው እንደሆነ ገልፀዋል፡፡
ሔርሞን ፍቃዱ
አዲስ ዘመን ማክሰኞ ግንቦት 5 ቀን 2017 ዓ.ም