የምርምር ውጤቶች ከህትመት ባለፈ ተግባራዊ ለማድረግ በቅንጅት መሥራት እንደሚገባ ተጠቆመ

ወልቂጤ፦ በከፍተኛ ትምህርት ተቋማት የሚሠሩ የምርምር ውጤቶች ከህትመት ባለፈ ተግባራዊ ለማድረግ ከባለድርሻ አካላት ጋር በቅንጅት መሥራት አስፈላጊ መሆኑ ተመላከተ። “እውቀት መር ኢኮኖሚ ለድህነት ቅነሳ እና ለማህበራዊ ዋስትና” በሚል መሪ ቃል 6ኛው ሀገር አቀፍ የጥናትና ምርምር ኮንፍረንስ በወልቂጤ ዩኒቨርሲቲ ሰሞኑን ተካሂዷል።

የወልቂጤ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንት ፋሪስ ደሊል(ዶ/ር)፤ የጥናትና ምርምር ሥራዎች ለህብረተሰቡ ተደራሽ እንዲሆኑና ለፖሊሲ ግብዓትነት እንዲያገለግሉ መሥራት ቀዳሚ ተግባር መሆን አለበት። በጉባዔው የቀረቡ ጥናታዊ ጽሁፎች ከእርስ በእርስ መማማሪያነት ከማዋል ጎን ለጎን በየዩኒቨርሲቲዎች የሚሠሩ የምርምር ሥራዎች ተግባራዊ እንዲደረጉ የመንግሥት አካላት ይበልጥ ማሳተፍ ይገባቸዋል ብለዋል።

ኮንፍረንሱ የአካዳሚውን ዘርፍ ወደ ላቀ ደረጃ ከማሻገር በተጨማሪ ፈጠራን ለማጎልበትና የሀገርን ዘላቂ እድገት ለማረጋገጥ ከፍተኛ ጠቀሜታ እንዳለው ያመለከቱት ፋሪስ ደሊል (ዶ/ር)፤ እውቀት መር ኢኮኖሚ በማጎልበት ድህነትን መቀነስ እንዲሁም የማህበረሰብን ችግር ከመፍታት አኳያ የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ሚና የላቀ እንደሆነ አመልክተዋል ።

ኮንፍረንሱ በተለይ በዩኒቨርሲቲዎች መካከል የእውቀት፣ የልምድ፣ የአዳዲስ ሃሳቦች እንዲሁም የመረጃ ልውውጥ ለማድረግ የሚያግዝ መሆኑን ጠቁመዋል። በኮንፍረንሱ የተመረጡ ከ26 በላይ ጥናታዊ ጽሑፎች ይቀርባሉ ያሉት ሲሆን፤ በጥናቱ የተገኙ ውጤቶችም ለፖሊሲ ግብዓት እንዲውሉ ለማስቻል ከተለያዩ ሴክተር መሥሪያ ቤቶች ጋር እየተሠራ መሆኑን አብራርተዋል። በከፍተኛ ትምህርት ተቋማት የሚደረጉ የምርምር ውጤቶች ማሳደግ እደሚገባም ጠቁመዋል።

እንደ ፋሪስ (ዶ/ር) ገለጻ፤ የወልቂጤ ዩኒቨርሲቲ ከሚሠራቸው የምርምር ሥራዎች በተጨማሪ የተለያዩ የማህበረሰብ አቀፍ አገልግሎት ይሰጣል። በጤናው ዘርፍ፣ በግብርናው ዘርፍ፣ የነጻ የሕግ አገልግሎት፣ እንዲሁም የሥራ እድል ፈጠራ ተጠቃሽ ናቸው። ዩኒቨርሲቲው አፕላይድ ዩኒቨርሲቲ እንደመሆኑ መጠን የአካባቢው ማህበረሰብ የሥርዓተ ምግብ እንዲሻሻል የእጽዋትና የእንስሳት ዝርያ የማሻሻል ሥራ ትኩረት መደረጉን አብራርተዋል።

በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የምጣኔ ሀብት ባለሙያና በቢዝነስና ኢኮኖሚክ ኮሌጅ ተጠባባቂ ዲን አጥናፉ ገ/መስቀል (ዶ/ር) በበኩላቸው፤ በሀገሪቱ የሚደረጉ የምርምር ውጤቶች ከህትመት በዘለለ ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ሀብት ለማድረግ በቅንጅት መሥራት ግንባር ቀደም ተግባር መሆን እንዳለበት አመላክተዋል።

የሚሠሩ አብዛኛው የምርምር ውጤቶች ችግር የለባቸውም ነገር ግን ከጠረጴዛ መዝለል አልቻሉም ያሉት አጥናፉ (ዶ/ር)፤ጥቅም ከመስጠት ይልቅ ሀገሪቱን ለተለያዩ ሀብት ብክነት ሲዳርግ ቆይቷል ብለዋል። እንደ ሀገር የምርምር ሥራዎች መሬት የሚወርዱበት ሥርዓት አለመዘርጋቱን ጠቅሰው፤ ምርምርን የሚደግፍና አካታች በሆነ መልኩ እንዲሠራ የሚያግዝ ተቋማዊ አደረጃጀት እንደሚያስፈግም አስታውቀዋል ። በኮንፍረንሱ የቀረቡ የምርምር ውጤቶች ሀገሪቱ የጀመረችው የዲጂታል ኢኮኖሚ ውጥን እውን ማድረግ የሚችሉ ናቸውም ብለዋል።

በኮንፍረንሱ የተለያዩ ተቋማት የተሳተፉ ሲሆን ጥናታዊ ጽሑፎች ቀርበው ውይይት ተደርጎባቸዋል።

ልጅዓለም ፍቅሬ

አዲስ ዘመን ማክሰኞ ግንቦት 5 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You