‹‹የሕግና ፖሊሲ ማሻሻያ ርምጃዎች ለውጭ ቀጥታ ኢንቨስትመንት ምቹ ሁኔታ ፈጥረዋል›› – ፕሬዚዳንት ታዬ አፅቀ ሥላሴ

አዲስ አበባ፡- እየተደረጉ ያሉ የሕግና ፖሊሲ ማሻሻያ ርምጃዎች ለውጭ ቀጥታ ኢንቨስትመንት ምቹ ሁኔታ መፍጠራቸውን ፕሬዚዳንት ታዬ አፅቀ ሥላሴ አስታወቁ ፡፡ ለባለሀብቶች ቀልጣፋ አገልግሎት መስጠት የሚያስችል ምቹ አሠራር ሥርዓት ለመፍጠር እየተሠራ መሆኑም ተገለጸ።

“ኢንቨስት ኢትዮጵያ 2025” ዓለም አቀፍ የኢንቨስትመንት ፎረም ትናንት በአዲስ አበባ በተጀመረበት ወቅት ፕሬዚዳንት ታዬ አፅቀ ሥላሴ እንዳመለከቱት፤ በኢትዮጵያ እየተደረጉ ያሉ የሕግና ፖሊሲ ማሻሻያ ርምጃዎች ለውጭ ቀጥታ ኢንቨስትመንት ምቹ ሁኔታ ፈጥረዋል።

የተወሰዱ የኢኮኖሚ ማሻሻያ ርምጃዎች ቀጣይነት ያለው የኢኮኖሚ እድገት ለማስመዝገብ፣ የውጭ ቀጥታ ኢንቨስትመንትን ለመሳብ እና የኢኮኖሚ መዋቅራዊ ሽግግርን ለማሳካት እንደሚያግዙም አመልክተዋል።

ለውጭ ባለሀብቶች ዝግ ሆነው የቆዩ ዘርፎችን የመክፈት ሀገራዊ ሪፎርም፣ የሕግና የፖሊሲ ማሻሻያዎችና በተለያዩ ዘርፎች ኢንቨስትመንትን በመሳብ ረገድ ተጨባጭ ውጤት እያስመዘገቡ ነው፤ ይህም ኢትዮጵያ በትክክለኛው የዕድገት ጎዳና ላይ እንድትገኝ አድርጓታል ብለዋል።

ኢትዮጵያ ያላት የሕዝብ ቁጥር ብዛት፣ ያልተነኩ የኢንቨስትመንት እድሎችና የተዘረጉ ምቹ የአሠራር ሥርዓቶች ለኢንቨስትመንት ምቹ እንደሚያደርጓት አስገንዝበው፤ ፖሊሲዎችን ለኢንቨስትመንት ምቹ ማድረግ፣ መሠረተ ልማቶችን ማስፋፋትና ቀልጣፋ አገልግሎት እንዲኖር ለማስቻል የተለያዩ ሥራዎች እየተከናወኑ መሆኑን አስታውቀዋል፡፡

የተዘረጉ የማበረታቻ ሥርዓቶች ባለሀብቶች ኢንቨስትመንታቸውን እንዲያስፋፉና ዘላቂነትን እንዲያረጋግጡ የሚያግዙ መሆናቸውንም ጠቁመዋል።

ፎረሙ ኢትዮጵያ ያላትን የኢንቨስትመንት አቅም ለማሳየት ትልቅ ዕድል መሆኑን ያመለከቱት ፕሬዚዳንቱ፤ በዘርፉ ያሉ ተግዳሮቶች እና የመፍትሔ ሃሳቦች የሚቀርቡበት እንደሚሆን ያላቸውን እምነት ገልጸዋል፡፡

የገንዘብ ሚንስትሩ አህመድ ሽዴ በበኩላቸው፤ ኢትዮጵያ ሰፊ መሬት፣ ከፍተኛ የውሃ ሀብት፣ ወጣትና የተማረ የሰው ኃይል ብሎም የተሟላ መሠረተ ልማት ያላት መሆኗ ለኢንቨስትመንት ምቹ አድርጓታል ብለዋል።

ለባለሀብቶች ቀልጣፋ አገልግሎት መስጠት የሚያስችል ምቹ የአሠራር ሥርዓት ለመፍጠር እየተሠራ መሆኑን አመልክተው፤ ለዚህም በዲጂታል ቴክኖሎጂ የታገዘ የአንድ መስኮት አገልግሎት መጀመሩን ጠቁመዋል።

መንግሥት የተረጋጋ ማክሮ ኢኮኖሚ እና ቀጣይነት ያለው የምጣኔ ሀብት እድገት ለመገንባት የሀገር በቀል የምጣኔ ሀብት ማሻሻያ መተግበሩን አስታውሰው፤ በማሻሻያው የግሉ ዘርፍ ተሳትፎ ቅድሚያ እንደተሰጠው ጠቅሰዋል፡፡

ባለሀብቶች በምጣኔ ሀብት ማሻሻያው ለግሉ ዘርፍ የተሰጠውን ትኩረት በአግባቡ ተረድተው ኢንቨስት እንዲያደርጉ ጥሪ አቅርበዋል።

ኢትዮጵያ የተገበረችው የተሟላ የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያ፣ ተቋማዊ እና መዋቅራዊ ችግሮችን የሚፈቱ ሪፎርሞች ዘላቂ ሀገራዊ ዕድገትን የሚያመጡ መሆናቸውንም አስረድተው፤ የሕግና የፖሊሲ ማሻሻያዎች እንዲሁም የንግድና ኢንቨስትመንት ምህዳሩን የመክፈት ርምጃዎችም ትልቅ ውጤት እያመጡ ነው ብለዋል፡፡ የኢትዮጵያ ካፒታል ገበያ ወደ ሥራ መግባቱም ተወዳዳሪ እና በግሉ ዘርፍ የሚመራ ኢኮኖሚ ለመገንባት ጉልህ አስተዋጽኦ እንዳለውም አመላክተዋል፡፡

የኢንቨስትመንት ኮሚሽን ኮሚሽነር ዘለቀ ተመስገን (ዶ/ር)፤ የኢትዮጵያን የኢንቨስትመንት እምቅ አቅም ለማስተዋወቅ ሲሠራ ቆይቷል። በፎረሙ ላይ ከ59 ሀገራት የተውጣጡ ተሳታፊዎች እየተካፈሉ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

በዘርፉ የተሻሻሉ ሕጎች፣ አዋጆችና ደንቦች ዘርፉን በማነቃቃት ከፍተኛ ለውጥ እያመጡ መሆኑን ጠቅሰው፤ ባለሀብቶች መንግሥት ትኩረት በሰጠባቸው የግብርና፣ ማዕድን፣ ቱሪዝም፣ ማኑፋክቸሪንግ እና አይሲቲ ዘርፎች ኢንቨስት እንዲያደርጉ እየተሠራ መሆኑንም ገልጸዋል፡፡

“ኢንቨስት ኢትዮጵያ 2025” ዓለም አቀፍ የኢንቨስትመንት ፎረም በዛሬው ዕለትም ቀጥሎ እንደሚካሄድ የወጣው መርሐግብር ያመለክታል፡፡

ፋንታነሽ ክንዴ

አዲስ ዘመን ማክሰኞ ግንቦት 5 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You