ካዛንቺስ አሳፈረኝ!

 

ባለፈው ዓመት በወርሃ ነሐሴ ነው:: በአንድ የግል ጉዳይ ምክንያት ወደ ካዛንቺስ ሄድኩ:: ከቀጠሮዬ ቀድሜ ለመድረስ ብሞክርም፤ እንኳን ቀድሜ መድረስ ይቅርና በሰዓቱ ራሱ የምደርስ አልሆንኩም:: ይህ ሁሉ የሚሆነው ከግቢ ገብርኤል እስከ ቶታል ባለው ርቀት ውስጥ ብቻ ነው:: በእግሬ ብሄድ በ10 ደቂቃ ውስጥ እደርሳለሁ:: መናኸሪያ የሚባለው ቦታ ስደርስ ከታክሲው ወርጄ በእግሬ ለመሄድ ሞከርኩ:: በተለምዶ የእሁድ ገበያ(ሰንደይ ማርኬት) በሚባለው አቋራጭ መንገድ ጉዞ ስጀምር ሰው እና ተሽከርካሪ እየተጋፋ ያልፋል:: አንድ ተሽከርካሪ ለማሳለፍ ብዙ ደቂቃዎችን ቆሞ መጠበቅ የግድ ነው፤ ምክንያቱም ቶሎ አያልፍም:: ግራ ቀኙ ውሃ እና ጭቃ ነው:: ዝናብ ይዘንባል፤ መንገዶች ተዘጋግተዋል:: የእግረኛ መንገድ የሚባል ነገር የለም:: ለዚያውም ያሉት የእግረኛ መንገዶች ኩሬ አጠራቅመው ምናልባትም ጎረምሳ የሆነ ሰው በዝላይ የሚሻገር ከሆነ ነው:: ይሄ ብቻ አይደለም ችግሩ፤ ከወዲህ ማዶ ሲዘል ከወዲያ ማዶ የሚያርፍበት የለውም፤ ከተከማቸው ኩሬ ሥር ሆነው ለመሻገር ወረፋ የሚጠብቁ ሰዎች አሉ::

እንዲህ እንዲህ እያለ የቀጠሮዬ ሰዓት ብዙ ደቂቃዎችን አለፈ:: ግቢ ገብርኤል ደርሻለሁ ያልኩት ሰው ለዚያች መንገድ ነው ያን ያህል የቆየሁ ብለው ሊያምነኝ አይችልም:: ‹‹አልበር እንደ አሞራ›› ሆኗል ነገሩ::

በእነዚያ በተጉላላሁባቸው ሰዓታት ውስጥ አዲስ አበባን ተራገምኩ:: መቼም የማትለወጥ ዕድሜ ዘመኗን ኋላቀር ሆና የምትቀር መስላ ታየችኝ:: እነዚያ መንገዶች በአስማት ካልሆነ በስተቀር በሰው ኃይል፤ ለዚያውም በአጭር ጊዜ ውስጥ እንዲህ አይነት ተዓምራዊ ለውጥ ይኖራቸዋል ብዬ አስቤም አልሜም አላውቅም ነበር::

ባለፈው ሳምንት ወደ ካዛንቺስ ሄድኩ:: ከወራት በፊት የተማረርኩበት መንገድ መቀየሩ አይደለም የገረመኝ፤ የት ጋ እንደነበር ሁሉ ጠፋብኝ:: አስገራሚ የሰርከስ ትርዒቶችን እንደማየት ሆነብኝ:: ‹‹የሰው ልጅ በዚህ ልክ ነገሮችን መለወጥ ይችላል ማለት ነው? ብዬ ተገረምኩ:: ይህን ያልኩት ካዛንቺስ ላይ የተሠራው ሥራ በዓለም ላይ የሌለ የሥራ አይነት ሆኖ አይደለም፤ ከነበረበት ሁኔታ አንፃር ነው:: በጥቂት ወራት ውስጥ እንደዚያ አይነት አካባቢን ወደ እንዲህ አይነት አካባቢ መለወጥ ለማድነቅ ብቻ ሳይሆን በሰው ልጅ ጥበብ ለመገረምም ያስገድዳል::

ትናንት የወቀስኳትን ካዛንቺስ ዛሬ ይቅር በይኝ ብያለሁ:: ትናንት ዕድሜ ዘላለም አትለወጥም ያልኳትን ካዛንቺስ በሰነፍ ግምቴ አፍሬያለሁ:: አዲስ አበባንም ይቅር በይኝ ብያለሁ፤ ምክንያቱም አብዛኞቹ የአዲስ አበባ ቦታዎች በኮሪዶር ልማቱ እያማሩ ነው::

ካዛንቺስን ምሳሌ ያደረኩት የቅርብ ለውጥ ስለሆነ እንጂ ሁሉም የአዲስ አበባ አካባቢዎች የተበላሹ ነበሩ፤ እንዲያውም የባሱ ሁሉ ነበሩ:: ለመሆኑ አዲስ አበባ ትናንት ምን ነበረች? ዛሬ ምን ላይ ናት? በዚህ ከቀጠለች ነገ ምን ትሆናለች?

ከኮሪዶር ልማት በፊት ስለነበረችው አዲስ አበባ ታሪክ ነጋሪ አያስፈልገንም:: የአባቶችና እናቶች ምስክርነት አያስፈልገንም:: ምክንያቱም፤ ይህ አንድ ዓመት እንኳን ያልሞላ ታሪክ ነው:: ከኮሪዶር ልማቱ በፊት የነበረችውን አዲስ አበባ ‹‹ትናንት›› ለማለት ለአቅመ ማገናዘብ መድረስ ብቻ በቂ ነው:: ትንሽ ታሪክ ለማስመሰል ግን ሦስት ዓመት እንኳን ወደኋላ መለስ እንበልና ጥቂት ማሳያዎችን እንውሰድ::

ከፓርላማ መብራት አንስቶ በቤተ መንግሥቱ በኩል ወደ ሸራተን እና ካዛንቺስ ለመሄድ በቀኝ በኩል ያለውን የእግረኛ መንገድ መያዝ ግድ ነው:: ይህ ገና አራት እና አምስት ዓመታት ብቻ የሆነው ታሪክ ነው::

በዚህ መንገድ ላይ ለማለፍ የሰርከስ ልምምድ ሳያስፈልግ አይቀርም ነበር:: አስፋልቱን እና የእግረኛ መንገዱን በምትለየዋ ቀጭን ጠርዝ ላይ እየተንጠለጠሉ ማለፍ የግድ ነበር:: በዚህች ቀጭን ጠርዝ ላይ የሚሄድ ሰው ጉዳይ ኖሮት በችኮላ የሚሄድ ሳይሆን፤ ‹‹በዚህች ጠርዝ ላይ አልፋለሁ አታልፍም›› ውርርድ ተወራርዶ የሚጫወት ነው የሚመስለው:: ምናልባትም ከርቀት ሆኖ የሚያስተውል ሰው ‹‹ትልቁ ሰውዬ ምን ያጃጅለዋል?›› ሊል ይችላል:: ትልቁ ሰውዬ ግን እንደዚያ የሚሄደው ወዶ ሳይሆን ወይም ለጨዋታ ብሎ ሳይሆን የሚረግጠው ስላልነበረው ነው:: ወደ አስፋልቱ መኪና፣ ወደ እግረኛ መንገዱ ደግሞ ኩሬ እና የቆርቆሮ አጥር ስለሆነ ነው::

ይህንንም የሚያደርጉት ወጣትና ጎልማሳ የሆኑ ጤነኛ ሰዎች ናቸው:: በዕድሜ የገፉ ሰዎች የነበራቸው ዕጣ ፋንታ ቀሚሳቸውን ወይም ሱሪያቸውን ከፍ አድርገው ይዘው፤ በውሃ እየተንቦጫረቁ ማለፍ ነው፤ ለዚያውም ለማለፍ ወረፋ ይዘው ማለት ነው:: የነበረው ችግር ውሃና ጭቃ መሆኑ ብቻ ሳይሆን፣ እንደዚያም ሆኖ ጠባብ ነበር:: ወረፋ ይዞ ተራ በተራ የሚታለፍ ነበር::

ዛሬስ?

ዛሬ ከፓርላማ መብራት እስከ ካዛንቺስ ድረስ የሚሄድ ሰው የሚያየው ውብ ነገር ዓይን አዋጅ ሆኖበት ሳያስበው ራሱን ሸራተን ጋ ሊያገኘው ይችላል:: ካዛንቺስ ለመሄድ ትምህርት ሚኒስቴር ጋ ታክሲ ጥበቃ ዝናብ ወይም ፀሐይ ይመታው የነበረ ሰው፤ ዛሬ ግን ‹‹እባክህ ና በነፃ ልውሰድህ›› ቢሉት እሺ አይልም! ምክንያቱም በየመንገዱ የሚያየው ነገር ይበልጥበታል::

አሁን ደግሞ እነሆ ካዛንቺስ ራሷ የምትጎበኝ እና እዩኝ እዩኝ የምትል ሆናለች::

ጠቅላይ ሚንስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) ባለፈው ዓመት በፓርላማ እንደተናገሩት፤ ለአንድ ሚሊዮን ባለመኪና አስፋልት መንገድ ተሠርቶ፣ ለአምስት ሚሊዮን እግረኛ ግን ትኩረት አልተሰጠም ነበር:: በዚያ ላይ መኪና ያለው ሁሉ ለአንድ ኪሎ ሜትር ርቀት ሁሉ ሞተር ሊያስነሳ አይችልም:: ለጤናም ሆነ ለቅልጥፍና በእግር መሄድ ግዴታ የሚሆንባቸው አጋጣሚዎች አሉ:: ለሻይ እና ለምሳ ሲወጣ ሁሉ መኪና ሊያስነሳ አይችልም:: ስለዚህ የእግረኛ መንገዶች ማማራቸው ሊመሰገን የሚገባ ነው::

የዛሬውን የኮሪዶር ልማት ያመሰገንነው፣ ያደነቅነው፤ ከትናንት አንፃር ነው:: ስለዚህ የዛሬው ውበት ለነገው ትውልድ አደራ የሚሰጥ ይሆናል ማለት ነው:: የነገውን ትውልድ የሚያነቃ ይሆናል ማለት ነው:: አንድ ጥሩ ነገር ሲጀመር ትልቁ ጥሩነቱ አርዓያ መሆኑ ነው:: ቢያንስ ቢያንስ ከዚህ የተሻለ እንኳን ባይሠራ፣ ከዚህ የባሰ አይደረግም ማለት ነው:: የትናንቱን አይነት አናይም ማለት ነው:: ዛሬ እንዲህ አይነት ከተሠራ ነገ ደግሞ ከዚህ የተሻለ ይሠራል ማለት ነው::

የነገዋ አዲስ አበባ ከዚህም ትበልጣለች ማለት ነው:: ዛሬ ለናሙና ያህል በአራት ኪሎ፣ ፒያሳ፣ ከመገናኛ እስከ ሲ ኤም ሲ፣ ቦሌ፣ መስቀል አደባባይ፣ ካዛንቺስ … በአጠቃላይ በከተማዋ ዋና ዋና መስመሮች ያየናቸው ውብ ሥራዎች ነገ ደግሞ በመላዋ አዲስ አበባ ይሆናል ማለት ነው:: በአንድ ዓመት ውስጥ ይህ ሁሉ ከተሠራ፣ በሚቀጥሉት ዓመታት የምትሠራው አዲስ አበባ ከዚህም በላይ ትሆናለች ማለት ነው:: አራት ኪሎን ወይም ቦሌን አይቶ ወደ ሰፈሩ ሲሄድ ቅር የሚለው ሰው፤ ነገ ሰፈሩም እንደነ ቦሌና ካዛንቺስ ይሆናል ማለት ነው:: ልጆቹ ከተማ ማለት ምን ማለት እንደሆነ ያውቃሉ ማለት ነው::

ከዓመታት በፊት ስለአዲስ አበባ የነበረውን ትርክት ማስታወስ በጣም ቀላል ነው:: በእንግድነት ብቻ የሚያውቋት የክፍለ ሀገር ሰዎች ሳይቀር ‹‹አዲስ አበባ›› ሲባል ወደ አዕምሯቸው የሚመጣው መጥፎ ሽታ ነበር:: ከተማ ሲባል ከመጥፎ ሽታ እና ከመንገድ መጨናነቅ ጋር የሚያያዝ ምስል ፈጥሮ ነበር:: አሁን ግን አዲስ አበባ ለማየት የምታጓጓ፣ ሌሎች ከተሞችንም ለመሥራት የምታነሳሳ ሆናለች ማለት ነው:: ነገ ለመላው ኢትዮጵያ ከተሞች የንጽህና እና የውበት አርዓያ ትሆናለች ማለት ነው::

የነገዋ አዲስ አበባ ከዛሬዋ በላይ አዲስ እንድትሆን እንሥራ!

ይህ አምድ በተለያዩ ፖለቲካዊ ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ጉዳዮች ዙሪያ ዜጎች ነፃ ሀሳባቸውን የሚሰጡበት ነው።በዓምዱ ላይ የሚወጡ ጽሁፎች የዝግጅት ክፍሉን አቋም አያመለክቱም።

ሚሊዮን ሺበሺ

አዲስ ዘመን ሰኞ ግንቦት 4 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You