
ዜና ሀተታ
አረጋውያን ትውልዱን በማስተማር ሀገሩን የሚወድ እና የታነጸ ትውልድ ለመፍጠር በሕይወት ዘመናቸው የሰበሰቡት እውቀት ትልቅ ነው:: እነዚህ አረጋውያን ለሀገር ለዋሉት ዘርፈ ብዙ ውለታ፤ እነዚህን አረጋውያን መንከባከብም ለትውልዱ የኩራት ምንጭ ነው:: አረጋውያንን ከመንከባከብ ባለፈ ደግሞ ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነታቸውን ማረጋገጥ ትልቁን ድርሻ ይወስዳል::
በቅርቡ በአዲስ አባባ ሴቶች፤ ህጻናት እና ማህበራዊ ጉዳይ ቢሮ በኮልፌ ቀራኒዮ ክፍለ ተከተማ ለተለያዩ አረጋውያን የዶሮ፤ የበግ፤ የእንጀራ መጋገሪያ፤ የዳቦ መጋገሪያ፣ የኤሌክትሪክ ምጣድ እና ሌሎች ድጋፎች ተደርጓል:: የአዲስ አበባ አረጋውያን ማህበር ፕሬዚዳንት አቶ ጌታቸው ክፍሉ እንደሚሉት፤ ከዚህ በፊት አረጋውያን ድጋፍ እንዲደርግላቸው እንደማህበር ብዙ ጉትጎታ ሲያደርግ ቆይቷል:: አሁን ላይ የለውጡ መንግሥት ከመጣ ወዲህ ለአረጋውያን በርካታ እድሎች እየተመቻቹላቸው ይገኛል::
በተለይ እንደ አዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ሴቶች፤ ህጻናት እና ማህበራዊ ጉዳይ ቢሮ በአካታችነት፤ በአሳታፊነት እና ተጠቃሚነት መርህ ከላይ እስከታች ባለው መዋቅር ለአረጋውያን ትልቅ ሥራ እየሠራ ይገኛል:: ከዚህም ሌላ ሌሎች ሴክተር መሥሪያ ቤቶችን በመቀስቀስ መሥሪያ ቤቶቹ አረጋውያንን በእቅዳቸው አካተው እንዲተገብሩ ማስቻሉን ይጠቁማሉ::
የነበሩ አሠራሮችን በመስበር አረጋውያን በማምሻ እድሜያቸው ጎዳና እንዳይወደቁ የሥራ እድል በማመቻቸት ረገድ ቢሮው ትልቅ ሥራ ሠርቷል:: ከዚህ ቀደም ብሎ በቦሌ ክፍለ ከተማ 469 አረጋውያን በዶሮ ርባታ፤ በጓሮ አትክልት፣ በበግ ርባታ እና በሌሎች ሥራዎች እንዲሠማሩ በማድረግ ተጠቃሚ እንዲሆኑ ማድረጉንም ያወሳሉ::
አረጋውያን አይሠሩም የሚለው ሃሳብ ተገቢ አይደለም የሚሉት ፕሬዚዳንቱ፤ ምክንያቱም አረጋውያን በየትኛው እድሜ ውስጥ መሥራት እንደሚችሉ ለማሳየት በተሠራ ጥናት 90 በመቶ የሚሆኑ አረጋውያን እድሜ ሳያግዳቸው መሥራት እንደሚችሉ ለማወቅ ተችሏል ይላሉ::
አረጋውያንነት የእረፍት ጊዜ ሳይሆን፤ ለረጅም ጊዜ የተሰበሰበን እውቀት እና ልምድ ለትውልዱ የማስተላለፊያ ብሎም፤ የበለጠ ጥረት የሚደረግበት እና ለሀገር ሰላም ፤ ለኢኮኖሚ ብልፅግና የሚሠራበት የእድሜ ክልል መሆኑን በመጠቆም፤ ለተደረገው ድጋፍ ለአዲስ አባባ ሴቶች፤ ህጻናት እና ማህበራዊ ጉዳይ ቢሮ ምስጋና አቅርበዋል::
ከኮልፌ ቀራኒዮ ክፍለ ከተማ ወረዳ ሁለት አስርአለቃ ማስረሻ በላይ እንደሚናገሩት፤ “ከዚህ በፊት ድጋፍ እንድወስድ ተጠርቼ ስላልተመቸኝ አልመጣሁም ነበር:: በድጋሚ ዛሬ ጠርተው ድጋፍ ስላደረጉልኝ እጅግ በጣም ደስ ብሎኛል::”
ከዚህ በፊትም በዶሮ ዕርባታ መሰማራታቸው በመግለጽ፤” አሁን የተሰጡኝን ጨምሬ ጡረታም ሆነ ሌላ የሚረዳኝ ወገን ስለሌለኝ በእነሱ እተዳደራለሁ:: ስለተደረገልኝ ድጋፍ በጣም ደስ ብሎኛል:: “ሲሉ ስሜታቸውን ይገልጻሉ::
ይህ ድጋፍ መደረጉ አረጋውያን አልባሌ ቦታ እንዳይውሉ፤ ጎዳና ላይ ወጥተው እንዳይባዝኑ እና ጊዜያቸውን በሥራ እንዲያሳልፉ ይረዳል:: ምክንያቱም መጠጥ ሆነ ሌሎች አልባሌ ነገሮች ጤና ላይ ጉዳት ያመጣሉ፤ ለሌሎች ተጽኖዎችንም ያጋልጣሉ:: ከዚህ አኳያም አረጋውያን መንግሥት ያደረገላቸውን ድጋፍ ተጠቅመው እራሳቸውን ሊቀይሩ ይገባል ይላሉ::
ለተደረገላቸው ድጋፍ ምስጋና የሚያቀርቡት አቶ ሄሩ ጀማል፤ “ከዚህ በኋላ ጥረት ማድረግ ያለብኝ እኔ ነኝ:: የተሰጡኝን ዶሮዎች በእንክብካቤ በማርባት ከእነሱ ተጠቃሚ ከመሆን ባለፈ፤ ሌሎች ዶሮዎች በመጨመር በዶሮ ርባታ ከፍተኛ ውጤት ለማስመዝገብ ጠንክሬ እሠራለሁ ::” ሲሉ ይገልጻሉ::
የተደረገላቸው ድጋፍ ዶሮ፤ የዶሮ መኖ እና የዶሮ ማቆያ (የዶሮ ኬጂ) ሲሆን፤ ከዚህ በፊት በወረዳ ደረጃ ሰዎች ቤት ለቤት መጥተው የተለያዩ ነገሮች ድጋፍ እንዳደረጉላቸው በመግለጽ፤ አሁን የተደረገላቸው ድጋፍ ራስ ለመለወጥ ትልቅ ጥቅም እንዳለው ያስረዳሉ::
ሶስት በጎች ከመኖ ጋር እንደተሰጣቸው የሚናገሩት ወይዘሮ አሰገደች ጋሻው በበኩላቸው፤ ለተደረገላቸው ድጋፍ እያመሰገኑ፤ በጎቹን በመንከባከብ አርብተው ለመጠቀም እንዳሰቡ ይናገራሉ::
ወይዘሮ አሰገደች፤ ከዚህ በፊት ሥራ ያላቸው ቢሆንም፤ አሁን ላይ በአጋጠማቸው የጤና እክል ምክንያት ጡረታ ለመውጣት ተገደዋል:: የልጅ ልጆቻቸውም ከእሳቸው ጋር የሚኖሩ ሲሆን፤ የሚሰጣቸው የጡረታ ገንዘብ አነስተኛ ነው:: ከዚህ አንጻር የተደረገላቸው ድጋፍ ትልቅ ደስታ እንደፈጠረላቸው ይገልጻሉ::
በመርሀ ግብሩ ላይ የአዲስ አበባ ከተማ ሴቶች ህፃናትና ማህበራዊ ጉዳይ ቢሮ ከአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር አርሶ አደርና ከተማ ግብርና ልማት ኮሚሽን ጋር ድጋፉን አጠናክሮ ለማስቀጠል የሚያስችል መግባቢያ ሰነድ ተፈራርመዋል።
ዓመለወርቅ ከበደ
አዲስ ዘመን ሰኞ ግንቦት 4 ቀን 2017 ዓ.ም