የራስ ምርት ከማናናቅ ለማድነቅ እንነቃነቅ

ብዙዎቻችን የውጭ ምርት የማድነቅና የራስን ምርት የማናናቅ ልማድ ይታይብናል። እንዲህ ዓይነት ሀገርንና ሕዝብን መቀመቅ የሚከት፤ የራስን ምርት የማናናቅ ንቅናቄ በዘመቻ ነቃቅለን መጣል፤ ለራስ ምርት ዋጋ መስጠት አለብን። የሀገር ውስጥ ምርት ባለበት ከውጭ በግዥ በተገኙ ቁሳቁሶች መመካት፣ መኩራራት እንደ እኔ አመለካከት ለሀገር አለማሰብም አላዋቂነት እንደሆነ አምናለሁ። የራስን ምርት እያጣጣሉ የሌላን ምርት ማንጠልጠሉ አይበጀንም ብቻ ሳይሆን ትርፉ ‹‹ዶሮ ብትታማ በሬ አረዱላት›› እንዲሚባለው ብሂል ሀገርን ለከባድ ፈተና መዳረግ ነው።

ሀገርን የምናሳድገው እጅ ለእጅ ተያይዘን የራሳችንን የፋብሪካ ምርቶች በመግዛት መጠቀም ስንጀምር ነው። እኛ የራሳችንን ምርቶች አውቀን በድፍረት ሳናውቅ በስህተት እያናናቅን በኢንዱስትሪ ፓርኮች የሚመረቱ ብዙ ምርቶች ግን ለውጭ ሀገር ለአውሮፓና ለአሜሪካ ጭምር እየተሸጡ ነው። ይህ ምርቶቻችንን እያደነቁ መሆኑንና ለምርቶቻችን የሰጡትን እሴትና ደረጃ የሚያሳይ ነው። ሀገር በቀሉን ዕውቀት ከዘመኑ ቴክኖሎጂ ጋር በማቀናጀት፣ የራስን ሠርቶ ለራስ ወገን መሸጥ መለወጥ፣ በሀገር የተመረተን ምርት በመግዛት፣ ለሀገር ምርት ዋጋ መስጠት እና ማክበር፤ ለራስ ዋጋ መስጠትና ከዘመኑ ጋር እንደ መራመድ መሆኑን መገንዘብ አለብን።

ለአምራች ኢንተርፕራይዞች የገበያ ትስስር በመፍጠር የሀገራችን ዜጎች በሀገራቸው ምርት አንዲኮሩና የሀገር ምርት እንዲሸምቱ፣ ኢትዮጵያም በቀጠናው በምጣኔ-ሀብትና በኢንዱስትሪ ዘርፍ ላይ ያላትን ሚና በዘላቂነት እና በአስተማማኝ ሁኔታ ለማስቀጠል በተለይም ከዘርፉ ማግኘት የሚገባትን ጥቅም ለማረጋገጥ ዐውደ ርዕይና ባዛሮች አሰፈላጊነታቸው የጎላ ነው።

መንግሥት ለሀገር ውስጥ ምርት በሰጠው ትኩረት ‹‹ኢትዮጵያ ታምርት›› የሚል ዐውደ ርዕይና ባዛሮች በተለያዩ ወቅቶች በኢትዮጵያ ኢንተርፕራይዝና በተለያዩ ድርጅቶች በማካሄድ ላይ ይገኛል። ለኅብረተሰቡ ለማንቃት የሚደረግ ንቅናቄ በመሆኑ ሀገር አቀፍ ጠቀሜታው የሚናቅ አይደለም። ይህም ለኅብረተሰቡ ግንዛቤ የሚሰጥ ብቻ ሳይሆን ምርቱን እንዲገዙ እና የሀገር ምርቶቹ በዜጎች ዘንድ ቅቡልነት እንዲኖራቸው የሚረዳ ነው። ኢትዮጵያ ታምርት ኤክስፖ ከሀገር ውስጥ አልፎ በዓለም አቀፍ ደረጃ ተወዳዳሪ ምርት ለማምረት የሚያስችል መነቃቃት የሚፈጥር ነው።

ዘንድሮ 14ኛው ኢትዮ-ቻምበር ዓለም አቀፍ የንግድ ትርዒት ከመጋቢት 4-8/2017 ዓ.ም በኤግዚቢሽን ማዕከል በደማቅ ሁኔታ ተካሂዶ ነበር። በዓለም አቀፍ የንግድ ትርዒት 50 በጨርቃ ጨርቅና አልባሳት፣ በቆዳና ቆዳ ውጤቶች፣ በአግሮ-ፕሮሰሲንግ፣ በኬሚካል ውጤቶች፣ በማዕድንና ጌጣጌጥ ሥራዎች የተሰማሩ አነስተኛና መካከለኛ አምራች ኢንተርፕራይዞች የተሳተፉበት ነው።

ሚያዝያ 25 ቀን 2017 በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) የተከፈተው የኢትዮጵያ ታምርት ኤክስፖ 2017 ሚያዝያ 29 ቀን ተጠናቋል፡ በተጠናቀቀው በኢትዮጵያ ታምርት ኤክስፖ 2017 ደግሞ ከአራት ቢሊዮን ብር በላይ የግብይት ትስስር እንደተፈጸመ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር አቶ ተመስገን ጥሩነህ የኢትዮጵያ ታምርት ኤክስፖ ማጠናቀቂያ ላይ ባደረጉት ንግግር ገልጸዋል። መንግሥት በአስር ዓመቱ የልማት ዕቅድ የአምራች ኢንዱስትሪውን የማምረት አቅም በማሳደግ ገቢ ምርትን ለመተካት የንግድ ሚዛን ጉድለትን ለማመጣጠን የሥራ ዕድልን ለመፍጠር እና የዜጎችን ኑሮ ለማሻሻል እየሠራ ነው።

የኢትዮጵያ ታምርት ንቅናቄ ዓላማ የንግድ ትስስር ለመፍጠር፣ ኢንቨስትመንትን ለመሳብ፣ ፖሊሲና ስትራቴጂ ለማሻሻል የሚጠቅሙ ሃሳቦችን ለማሰባሰብና የሕዝቡን በሀገሩ ምርት የመኩራት ባሕል ለማሳደግ ያለመ ነው። የዜጎችን ኑሮ ለማሻሻል እየተሠራ ነው። የኢትዮጵያ ታምርት ንቅናቄ የዘርፉ ዓመታዊ ዕድገት በ2014 ከነበረበት የአምስት በመቶ ዕድገት በያዝነው በጀት ዓመት የ13 በመቶ ዕድገት ያስመዘግባል ተብሎ ይጠበቃል። በተጨማሪም በተለያዩ ምክንያቶች ተዘግተው የነበሩ 837 ኢንዱስትሪዎች ወደ ሥራ እንዲገቡ መደረጉን እና 325 ከፍተኛ ኢንዱስትሪዎችም ወደ ማምረት መግባታቸውን ምክትል ጠቅላይ ሚንስትር አቶ ተመስገን ጥሩነህ ባደረጉት ንግግር ገልጸው ነበር።

የኢንዱስትሪ ሚንስትር አቶ መላኩ አለበል እንደተናገሩት፤ የኢትዮጵያ ታምርት ኤክስፖ 2017 አምራቾች ካለፈው ዓመት በብዛት፣ በጥራትና በዓይነት ከፍ ያሉ ምርቶችን ያቀረቡበት ነበር። ዜጎችም የሀገራቸውን ምርት የመግዛትና የመጠቀም ባሕላቸው እያደገ እንደመጣ ያየንበት ነው ብለዋል። ኤክስፖውን ከ120 ሺህ በላይ ሰዎች የጎበኙትና፤ ከአራት ቢሊዮን ብር በላይ የግብይት ትስስር የፈጠረም ነው።

በራሳችን ሀገር ፋብሪካ የሚመረቱ ምርቶች ለመግዛት እምብዛም ፍላጎት የሌለው ዜጋ ብዙ ነው። ‹‹ባለቤቱ ያቀለለውን አሞሌ ባለእዳ አይቀበለውም›› እንደሚባለው ብሂል እንዳይሆንብን ለራሳችን ምርት ትኩረት መስጠት ይገባናል። ሀገራችን በአፍሪካ ቀንድ ከብት ብዛት ከቀዳሚዎቹ ተርታ ነች። ሰዎች የቀንድ ከብትን ለእርድ ስጋ ሲጠቀሙት በቆዳው ደግሞ የተለያዩ ምርቶች ይመረታሉ። ከነዚህም መካከል ጫማ፣ ቦርሳ፣ ጃኬት ወዘተ ይገኙበታል ። ነገር ግን ተመሳሳይ ምርቶች ከውጭ መምጣታቸው ለነጋዴዎቹ ፋይዳ ያለው ቢሆንም ለሀገር ግን ፍዳ እንደሚሆን መናገር ለቀባሪ እንደ ማርዳት ነው።

በአሜሪካ ከኮታና ታክስ ነፃ ዕድል (አጎዋ) እገዳ ምክንያት ከኢትዮጵያ ምርት መቀበል ያቆሙ ኩባንያዎች መኖራቸው ይታወቃል። ኩባንያዎቹ ግን እንደገና ለመመለስ እየጠየቁ መሆናቸው ሪፖርት ባወጣ አንድ ዘገባ ያሳያል። የሁጂያን ጫማ ፋብሪካ ምክትል ፕሬዚዳንት አቶ ናሆም ገብረሚካኤልን ጠቅሶ ጋዜጣው እንደዘገበው ፋብሪካው በ8ሺህ ሠራተኞቹ በዓመት 33 ሚሊየን ዶላር ጫማዎችን ለአሜሪካ ያቀርብ ነበር። ያው አሜሪካውያን የኢትዮጵያን የፋብሪካ ምርት እየወሰዱ እንደነበር ማሳያ ነው። ብዙዎቻችን ግን ለራሳችን ዋጋ ስለማንሰጥ የተጠቀሰውን የሀገር ውስጥ ጫማ ምርት ግዙ ብንባል ፍላጎት አይኖረንም፡፡

ከኢንዱስትሪ ፓርኮች ልማት ኮርፖሬሽን ድረ ገጽ ሰሞኑን የተገኘ መረጃ እንደሚያሳየው የተለያዩ ሀገራት ባለሀብቶች በኢትዮጵያ ኢንቨስት ለማድረግ ፍላጎት እያሳዩ ነው። ለአብነት ያህል ከተለያዩ የእስራኤል ኩባንያዎች የተውጣጡ ባለሃብቶች በኢትዮጵያ ልዩ የኢኮኖሚ ዞኖች ገብተው ኢንቨስት የማድረግ ፍላጎት እንዳላቸው ገልጸዋል።

በኢትዮጵያ የቻይና አምባሳደር ቼን ሃይ ደግሞ የጅማ ልዩ የኢኮኖሚ ዞንን አጠቃላይ የሥራ እንቅስቃሴ ተዘዋውረው ጎብኝተው። በጅማና አካባቢው በስፋት የሚመረተውን አቮካዶን በግብዓትነት በመጠቀም የምግብ ዘይትና ቅባት በማምረት ወደ አውሮፓና አሜሪካ ገበያዎች የሚልከውን አክሻይ ጀይ ኩባንያ የምርት ሂደትና አጠቃላይ የሥራ እንቅስቃሴ ተመልክተዋል። በጅማና አካባቢው ያለውን እምቅ የተፈጥሮ ሃብት ለማቀነባበር የሚያስችል የመብራት፣ የውሃ እንዲሁም የመሠረተ ልማት ሥራዎች መኖራቸውን የገለጹት አምባሳደሩ ቻይናውያን ባለሃብቶች በተለያዩ የኢንቨስትመንት ዘርፎች ገብተው ኢንቨስት እንዲያደርጉ ከኮርፖሬሽኑ እና ሌሎችም ባለድርሻ አካላት ጋር በቅንጅት እንደሚሠሩ ገልጸዋል፡፡

በተኪ ምርት የሚገኝ የሥራ ዕድል ሙያ የሚቀሰምበት ከመሆኑ ባሻገር ሀገር አቀፍ ሠፊ ጠቀሜታ አለው:: በኢትዮጵያ ባሉ ኢንዱስትሪ ዞኖች ልዩ ልዩ ምርቶች ይመረታል። ከምርቶቹ መካከል ጨርቃ ጨርቅና አልባሳት፣ ቁሳቁስ፣ የታሸጉ ምግቦች የምግብ ዘይት የመሳሰሉትን ኅብረተሰቡ ዜጋው ሲገዛ ሀገሩን የሚደጉምበት የውጭ ምንዛሪን የሚታድግበት ብቻ ሳይሆን በተመጣጣኝ ዋጋ የሚገዛበት ነው፡፡

እዚህ ላይ ኢትዮጵያ በአፍሪካ የጨርቃ ጨርቅ አልባሳት ኢንዱስትሪ ጥሩ መሠረት ካላቸው ሀገሮች መካከል እንደመሆኗ መጠን ኢንቨስት ለሚያደርጉ ባለሀብቶችም ሆነ ምርቶቹን የሚገዙ ዜጎች የተሻለ ምርት በተመጣጣኝ ዋጋ ሊገዙ እንደሚችሉ ማሳያ ነው። ከላይ የጠቀስናቸው ነጥቦችም የሀገራችን ምርቶች በውጭ ሀገሮች ዘንድ ቅቡልነት እንዳላቸው ማስረጃዎች ነው።

የሀገራችን ኢኮኖሚ ለማሳደግ በመንግሥት ዘርፈ ብዙ ሥራዎች እየተሠሩ ይገኛሉ። በዚህም መሠረት የኢንዱስትሪ ዘርፉ ለሀገሪቱ እድገትና ልማት የሚያበረክተውን ወሳኝ አስተዋጽኦና ከሁሉም የኢኮኖሚና ማኅበራዊ ዘርፎች ጋር ያለውን ቁርኝት ከግምት ውስጥ በማስገባት በሀገሪቱ መሪ የልማት ዕቅድ ልዩ ትኩረት ተሰጥቶታል፡፡

በመሪ የልማት ዕቅዱ ሁለተኛ አምስት ዓመታት (2018-2022) እንደተቀመጠው የማኑፋክቸሪንግ ኢንዱስትሪ አሁን ካለው 6ነጥብ9 በመቶ የኢኮኖሚ ድርሻ በቀጣይ ዓመታት ወደ 17ነጥብ2 በመቶ ለማሳደግ ፤አሁን ያለውን 50 በመቶ አማካይ የአምራች ኢንዱስትሪዎች የማምረት አቅም አጠቃቀም ወደ 85 በመቶ ለማድረስ ታቅዷል፡፡

ይህም ገቢ ምርት የሚተኩ አምራች ኢንዱስትሪዎች በማስፋፋት አሁን ያለው 30 በመቶ የሀገር ውስጥ የገበያ ድርሻ ወደ 60 በመቶ ማሳደግ፤ በማኑፋክቸሪንግ ኢንዱስትሪ ዘርፍ የሚፈጠረውን አዲስ የሥራ ዕድል 5 ሚሊዮን ማድረስ፤ ከማኑፋክቸሪንግ ኢንዱስትሪ ዘርፍ አሁን ካለበት የ405 ነጥብ6 ሚሊዮን የአሜሪካን ዶላር የውጪ ምንዛሬ ግኝት ወደ 9 ቢሊዮን የአሜሪካን ዶላር ማሳደግ፤ አዳዲስ አነስተኛና መካከለኛ ማኑፋክቸሪንግ ኢንዱስትሪዎችን በማበራከት ከተደረሰበት ዓመታዊ የ2ሺህ30 ኢንተርፕራይዞች የመፍጠር አቅም በ 2022 ወደ 10ሺህ806 ለማድረስ ታቅዶ እየተሠራ ነው።

ኢትዮጵያ ውስጥ በአሁኑ ወቅት ከ26 ሺህ በላይ አነስተኛና መካከለኛ አምራች ኢንተርፕራይዞች በመላ ሀገሪቱ ይገኛሉ። በመሪ የልማት ዕቅዱ በግልፅ እንደተቀመጠው ለተልዕኮው በቂ ዝግጅት በማድረግ ከፍተኛ ካፒታልና የሰለጠነ የሰው ኃይል ወደሚጠይቁ የማኑፋክቸሪንግ ንዑስ ዘርፎች በመሸጋገር ኢንዱስትሪ መር ኢኮኖሚን ለመገንባት ጥረት ይደረጋል።

ዝንተ ዓለም ከዘመኑ ጋር ለመራመድ አለመጣርና መንገዳገድ የፈየደው የለም። ባለሀብቶችንም በማንቃት በአክሲዮንም በማደራጀት የፋብሪካ ምርቶች ሊያመርቱ የሚችሉበትን መንገድ መሻት ይገባል። በብዛት ሕንፃ ገንብተው ንግድና መኖሪያ ቤት በብዛት ለማከራየት ነው የሚሞክሩት። ጥቃቅን ፋብሪካዎችን ቢከፍቱ ለብዙ ዜጎች የሥራ ዕድል ይፈጥራሉ። ለምሳሌ የቆዳ ጫማ ቀለም ከኬንያ በውጭ ምንዛሪ የሚገባ ነው።

ባለሀብቶቻችን እና የሕዝብ ብዛታችን ሀብታችንና ገበያችን መሆኑን መገንዘብ አለባቸው። ለምን በሀገራችን አይመረትም ብሎ መጠየቅ ቁጭትና አዎንታዊ ቅናትም ያስፈልጋል። የመንግሥት መሥሪያ ቤቶችም ኢትዮጵያ ታምርት ብለው ሲነቃነቁና ሰውን ሲያነቃቁ እራሳቸው ግን በየመሥሪያ ቤቶቻቸው የውጭ ምርቶችን ሲገዙ ነው የሚታየው። እናም የራስን ምርት በመግዛት የመንግሥት መሥሪያ ቤቶችም ለዜጋው አብነት ሊሆኑት ይገባል። የራስ ምርት ከማናናቅ ለማድነቅ እንነቃነቅ።

በይቤ ከደጃች.ውቤ

አዲስ ዘመን ዓርብ ግንቦት 1 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You